>
5:18 pm - Thursday June 16, 7436

ኦነግ ትጥቅ አልፈታም ሲል ምን ማለቱ ነው?

by Mengistu D. Assefa

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከሽግግር መንግሥት ተገፍቶ ከወጣ ከ27 ዓመታት በኋላ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ ተስማምቶ ወደ ሃገር ከገባ አንድ ወር ገደማ ይሆነዋል።

ነሐሴ 1, 2010 ዓ.ም. በኦነግ እና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሠ መስተዳድር ለማ መገርሳ እና በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኑስትር ወርቅነህ ገበየሁ የሚመራ ቡድን መካከል በኤርትራ መንግሥት አደራዳሪነት የእርቅ ሥምምነት መፈራረማቸውን በ East African Policy Research Institute ላይ ባወጠሁት ጽሁፍ መግለጼ ይታወሳል።

የድርድሩ አጀንዳዎች እና በኋላም የተደረሰው የእርቅ ሥምምነት ዝርዝር ጉዳይ ምን እንደሆነ ግልፅ ባይደረግም የእርቅ ሥምምነቱ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩት።

በሁለቱም መካከል የነበሩው ጥል መብቃቱን ማብሰር

ኦነግ በኢትዮጵያ ውስጥ የትግል ስልቱን ሰላማዊ ለማድረግ መስማማቱን እና ይህንን ድርድር ለማስቀጠል እና ለመተገበር የሚያስችል የጋራ ኮሚቴ እንደሚቋቋም ነበር የተስማሙት። ሰሞኑን የኦነግ መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከጀርመን ድምፅ ራዲዮ እና ትላንት ደግሞ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለመልልሶች ኦነግ ትጥቅ እንደማይፈታ፣ ትጥቅ መፍታት በስምምነቱ ውስጥ እንደሌለ እና “ትጥቅ አስፈቺም ፈቺም የለም” የሚል ዐንደምታ ያለው ነገር ተናግረዋል።

ምን እየተደረገ ነው?

ኦነግ በ1983/4 ወደ ሽግግር መንግሥቱ ሲገባ ወታደሮቹም ወደ ካምፕ እንዲገቡ ተደረገ። ብዙም ውሎ ሳያድር በሀገራችን ታሪክ ተደርጎ በማይታወቅ መልኩ ወታደሮቹ ተጨፈጨፉ፣ መሪዎቹም መታሠር ጀመሩ። በሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ እና የፖለቲካ መሪዎቹን ማሰር እና ማፈን እንዲሁም መግደል ተጀመረ። አብዛኞቹ እስከዛሬ ድረስ የት እንዳሉ የሚያውቁት የወያኔ ሽማግሌዎችና እና እነ አባዱላ ገመዳ ናቸው። ኦነግ ከሽግግር መንግሥቱ ከወጣ በኋላም በስሙ የተፈጸሙ እሥራቶችና አፈናዎች ነበሩ። እነሱም አልተፈቱም፤ የት እንዳሉም አይታወቅም። በሥምምነታቸው ላይ እንዴት እንደተነጋገሩ ባለውቅም ግን ትልቅ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል አልጠራጠርም። ይህን በተመለከተ ሌላ ጽሁፍ አዘጋጃለሁ። ኦነግ ይሄንን አይረሳም። ኦዴፓም ይሄ ይጠፋዋል ብሎ ማሰብ ይክብዳል።

ጓድ Nadhii Gammadaa, በ1984 ዓ.ም. በመንግሥት ከታገቱ የኦነግ ወጣት አመራር መካከል አንዱና እስካሁን ድረስ የት እንዳለ የማይታወቅ

ለዚህም ነው ኦነግ ከድሮም ጀምሮ (ከአቶ መለስ ጊዜ ጀምሮ) ለድርድር ዝግጁ እንደሆነ እና ድርድሩ ግን “ሦስተኛ ወገን በተገኘበት ይሁን ” ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብ የነበረው። በዚህም መሠረት የኤርትራ መንግሥት በተገኘበት አስመራ ላይ ሥምምነቱን የተፈራረሙት።

አሁን ችግሩ ምንድር ነው?

ኦነግ ሰላማዊ ትግል አካሄዳለሁ ብሎ ወደ ሀገር ሲገባ 1500 የሚጠጉ ወታደሮቹም ገቡ። እነዚህ ወታደሮች ካምፕ ናቸው። በሀገር ውስጥ የነበረው ወታደር ግን አሁንም ወደ ካምፕ አልገባም። ትጥቅም አልፈታም እያለ ነው። በሥሙ ተደራጁ የሚባሉ ታጣቂዎችም የተለያዩ ጥቃቶችን እያደረሱ እንደሆነ እያየን ነው።

ባዚሁ ሳምንት የኦዴፓ ከፍተኛ አመራር እና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አዲስ አረጋ ቂጤሳ በፌስቡክ ገፃቸው “በሥምምነቱ መሠረት የኦነግ ወታደር ወደ ካምፕ እንዲገባ/ ትጥቅ እንዲፈታ” ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

እዚህ ጋር ግልፅ መደረግ ጉዳይ አለ።

ገና ድርድሩ ሲደረግ በሥምምነቱ መሠረት ሲባል ዝርዝር ጉዳዩ ትጥቅ መፍታትን ማካተቱ እና የመፍታት ሂደቱ ምን መምሰል እንዳለበት የሚገልፅ ግልፅ መረጃ አልተሰጠም ነበር። ይህ ባልሆነበት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚደረግ ትዕዛዝ አዘል ጥሪ አግበብነቱ አጠያያቂ ነው። ምክንያቱም የሥምምነቱ አካል የነበረው “ከሁለቱ ወገን በተወጣጣ ቡድን ይቋቋማል” የተባለው የጋራ ኮሚቴ ነበር ይሄንን ጉዳይ የሚያስፈፅመውና የሚቄጣጣረው። ሰላምን የማስከበር ሙሉ ኃላፊነት (monopoly of state over means of violence) የመንግሥት ብቻ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ለገቡት ሥምምነት ሁለቱም ቡድን (ኦነግ እና መንግሥት) እኩል ተጠያቂናነት አለባቸው። መንግሥት ኦነግን የማዘዝ አይነት ጫወታ ሊዳዳው አይገባም። በውይይት እና ድርድር እንዲሁም ይህንን ተከትሎ ለሚደረሱ ሥምምነቶች መገዛት የሁለቱም አካላት ድርሻ ነውና። እኔ እስከማውቀው ድረስ በኦነግ እና መንግሥት መካከል የሚደረግን ድርድርና የደርድሮቹ ውጤት ትግበራን በበላይ ይመራል የተባለው የጋራ ኮሚቴ አልተቋቋመም ወይም ሥራ አልጀመረም።

አቶ አዲሱ ቀጥለውም “ትጥቅ ፈተው ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ” የሚል ጥሪም አቅርበዋል። ይህ በሁለት ምክንያቶች አደገኛ አዝማሚያ አለው። ይህን ያህል ብዛት ያለው ወጣት ወታደር፣ ሥራ አጥ እንዴት ወደ ሕዝብረተሰቡ ግቡ ይባላል? ለሰላም ዋስትና ሊሆን ይችላል? ሁለተኛ ደግሞ አስመራ ድረስ ሄደው የተስማሙበትን ሥምምነት መጣስ ይምስላል። የጋራ ኮሚቴ አያስፈልግም ዝም ብለህ ፍታ ዓይነት ትዕዛዝ ይመስላል። ይህ ኦነግን Undermine ማድረግም ተደርጎ እንዳይወሰድ ሥጋት አለኝ። አቶ ዳውድ “ትጥቅ ፈቺ እና አስፈቺ የሚባል ነገር የለም” ማለታቸው ይህንን ማመላከታቸው ይመስለኛል።

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወርቅነህ ገበየሁ፣ ዳውድ ኢብሳ እና ለማ መገርሳ የእርቅ ሥምምነቱን በአስመራ የተፈራረሙበት ነሐሴ 1, 2018

በሌላ የፖለቲካ ጨዋታ ደግሞ ይህ ኮሚቴ እንዳይቋቋም የሚፈልግ አካል ማን ነው? ለምን? ኦዴፓ አስመራ ድረስ ሄዶ ከኦነግ ጋር ሥምምነት ማድረጉ መሉ በሙሉ እንድናምነው ዋስትና ይሆናል ወይ? የሰኔ 16 የቦንብ ፍንዳታን በተመለከተ ይፋ ይደረጋል የተባለው በዚህ ሳምንት ነው። ከሱ ጋር በተያያዘ መጠርጠር ያለበት ነገር አለ?

ሰሞኑን በኦነግ ሥም የተደራጁ የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት እያደረሱ ስናይ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ጉዳዩ ኦነግን ማስበላቱን መጠርጠርም አይከፋም። በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በጉጂ እና የተለያዩ ቦታዎች ድሮም የታጠቁ ኃይሎች እንደነበሩ ይታወቃል። እነዚህ አካላት ጉዳት ሲያደርሱ የኦነግ ሥም በአንድም በሌላም መነሳቱ አይቀሬ ነውና ዞሮ ዞሮ ፖለቲካል ካፒታሉን ይጎዳል። ኦዴፓ ይህንን ክፍተት ተጠቅሞ ኦነግን ከጫወታ ውጪ የማድረጉም ነገር ግልጽ ይመስላል። ምክንያቱም አሁን በሚታየው አዝማሚያ ኦሮሚያ ላይ በምርጫ ኦዴፓ ከኦነግ ጋር ቢወዳደር የማሸነፉ ጉዳይ አጠያያቂ ነውና።

ነገሩ ሲጠቃለል ኦነግ እና መንግሥት መካከል የተደረገው ሥምምነት ግልፅነት አለመኖሩ ችግር ፈጥሯል። ሲቀጥል ደግሞ በመጀመሪው ሥምምነት መሠረት አፈጻጸሙ እክል እንደገጠመው መገመት አይከብድም። ለዚህም ማሳያ የድርድሩ ቀጣይ ሂደት እና የተደረሰውን ሥምምነት ገቢራዊ የሚያደርግ የጋራ ኮሚቴ አለመቋቋሙ (ከተቋቋመ ደግሞ በይፋ ሥራ አለመጀመሩ) ማንሳት ይቻላል። መንግሥት ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ላሰራቸው እና ደብዛቸው ለጠፋ የኦነግ መሪዎች እና አባላት ጉዳይ ምን መፍትሄ አለው? ሥምምነቱ ስለዚህ ምን ይላል?

በነገራችን ላይ ይህ የደርጅት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ጥያቄ መሆን አለበት። በብዙ ሺህ የሚቆጠር ዜጎች የት እንዳሉ ደብዛቸው ሲጠፋ የአንድ ድርጅት ጉዳይ ማድረግ አግባብነት የለውም። መምግሥት ይሄንን ለኦነግ ብቻ ሳይሆን ለሕዝቡ ግልፅ ማድረግ አለበት። በዚህ ሰዓት እኔ እስከማውቀው ድረስ ይሄንን ጉዳይ ከነ ሌንጮ ለታ ኦዴግ እና ከነ ዳውድ ኢብሳ ኦነግ ውጪ እየጠየቀ ያለ አካል አላየሁም። ከኦነግ ርዕዮተ ዓለም ጋር የማይስማማ ብዙ ዜጋ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ሁሉም አጀንዳዎቹ ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ማሰብም ሌላ ችግር ነው።

በኢትዮ ኤርትራ ወቅት እንኳን መንግሥት ተዋግተውኛል ያለቸውን የኦነግ ወታደሮች ማርካለሁ ብሎ ሲያስወራ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ በሬዲዮ ሰምቻለሁ። በአንድ ቀም ብቻ 1300 ወታደሮቹን መያዙን መንግሥት ሲናገር ነበር። የነዚህ ሰዎች ዕጣ ፈንታ ምንድነው? ይሄ ከኤርትራ ጋርም የሚነካካ ጉዳይ ስለሆነ ውስብስብ መሆኑን እረዳለሁ።

በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተደረገው የሰላም ሥምምነትም ልክ ከኦነግ ጋር እንደነበረው ግልጽነት ይጎድለዋል። የምግድ እና ኢንቭስትመንት፣ የድንበር እከላለል ጉዳይ፣ ስለተማረኩ እና ስለታሰሩ ዜጎች እና ወታደሮች የተቀመጠ ወይም ግልጽ የተደረገ ነገር የለም። ስምምነቱን ሁለት ጊዜ (አንዴ በአስመራ ልላ ጊዜ በሳዑዲ ዐረቢያ) ከመፈራረማቸው ውጪ።

ትንሽ የሚያስተዛዝበን ጉዳይ ከሁለት ወራት በፊት በአማራ ክልል ያሉ ገበሬዎች ትጥቅ ይፍቱ ሲባል “አማራውን የመስዋዕት በግ ሊያደርጉት ነው”፣ “በጭራሽ የማይሆን ጉዳይ ነው” ፣ ሲሉ የነበሩ ወገኖች ኦነግ “ትጥቅ አልፋታም” ሲል ጉራ ካራዩ ማለታቸው ነው። የሀገር ሰላም መረጋገጥ ካለበት ከመንግሥት ውጪ የታጠቀ ኃይል መኖር እንደሌለበት ቢታወቅም አንዱ ታጥቆ ሌላው መፍታት ትክክል አይደለም።

ኦነግም ሆነ ሌላ ኃይል ሠላማዊ ትግል ማድረግ ካለበት ጦሩ ወደ ካምፕ ገብቶ reindoctrinate ተደርጎ ወደ መከላከያ reintegrate የሚደረግበት ሂደት መኖር እንዳለበት ከማንም የሚጠፋ ጉዳይ አይመስለኝም። ዋናው ችግር ሁለቱ አካላት በትግል ሜዳው አለመስማማታቸው ካልሆነ ሌላ ምክንያት አይታየኝም። ኦነግ ኦዴፓን ለማመን ዋስትና ይፈልጋል። የ1984ቱን ስህተት ላለመድገም ማለት ነው። በሰላማዊ መንገድ የሚታገል ድርጅት ማንን ሊዋጋ፣ ለምንስ ሊዋጋ ጦር ያስፈልገዋል? የሥምምነታቸው ግልፅነት ማጣት ወይም ለሥምምነቱ ትገዥ ለመሆን ያለመዘጋጀት ችግር ካልሆነ እንዲህ ዓይነት እስጥ አገባ እንወክላለን ለሚሉት ሕዝብም ሆነ ለሃገሪቱም አደጋነቱ ይከፋል። ይህ ችግር ግን የአንድ ወገን ችግር ይሆናል ብዬም አላስብም። በሁለቱ መካከል ያለው ታሪካዊ “ጠላትነት” እና አለመተማመን፣ እንዲሁም በሥልጣንም ሆነ በኃይል ያለመመጣጠን፣ የሕዝቡ ድጋፍ ለማገኘት ለማግኘት የሚደረግ ፍትጊያ ነው ይህንን ሁሉ ችግር ያስከተለው ብዬ አስባለሁ።

እንደ መፍትሔ የመስቀምጠው ኦዴፓ እና ኦነግ መካከል በሥምምነታቸው መሠረት እንቆምለታለን የሚሉትን የሕዝብ ጥቅም እና የሀገር አንድነትን መሠረት ያደረገ ተከታታይ ሥራ መሠራት አለበት። የሠለጠነ ፖለቲካ በትጥቅም በአሻጥርም አይመጣምና።

አስተያየታችሁን በፌስቡክ ገፄ Mengistu D. Assefa ላይ ያድርሱኝ።

Filed in: Amharic