>

ከኢትዮጵያ የመንግሥት ሰራተኞች 500 ሺሕ ያክሉ ውጤታማ አይደሉም ተባለ

ከኢትዮጵያ የመንግሥት ሰራተኞች 500 ሺሕ ያክሉ ውጤታማ አይደሉም ተባለ

ዶይቼቬሌ አማርኛ

ኢትዮጵያ ለመንግሥት ሰራተኞች ከምትመድበው 18 ቢሊዮን ብር ውስጥ ስድስት ቢሊዮን የሚሆነው ውጤታማ ላልሆኑ ሰራተኞች የሚከፈል መሆኑን የኢትዮጵያ የሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት አስታውቋል። ማዕከሉ የመንግሥት ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በስብሰባ እና በደራሽ ሥራዎች ተጠምደው ውጤታማ መሆን እንደተሳናቸው በጥናት ማረጋገጡን ገልጿል።

በኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማት 1.5 ሚሊዮን ገደማ ሰራተኞች እንደሚገኙ የገለጹት የኢትዮጵያ የሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት ዋና የሥራ አማካሪ አቶ አሸናፊ አበራ “ከዚህ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ብቻ ውጤታማ የሆነ ተግባር ላይ የተሰማራ ሲሆን 500 ሺሕ ያክሉ ግን ምንም አይነት ውጤታማ የሆነ ሥራ ሳይሰራ የሚከፈለው” መሆኑን ተቋማቸው በሰራው ጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል። በዚህም መንግሥት ለመንግሥት ሰራተኞች ደሞዝ ከሚበጅተው 18 ቢሊዮን ብር ስድስት ቢሊዮን ገደማ የሚሆነው ውጤታማ ላልሆነ ሥራ የሚከፈል ወይንም የባከነ መሆኑን አቶ አሸናፊ ጨምረው ተናግረዋል። ዋና አማካሪው በመንግሥት ላይ የሚደርሰው የስድስት ቢሊዮን ብር አመታዊ ኪሳራ “በፕሮጀክቶች መዘግየት እና በዋጋ መጋሸብ የሚመጣውን የገንዘብ ኪሳራ፤ በተገልጋዮች ላይ የሚደርሰውን መጉላላት እና የእርካታ ማጣት” እንደማይጨምር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማትን እና የመንግሥት ሰራተኞችን ለጊዜ አጠቃቀም ብኩንነት ከዳረጓቸው አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ ስብሰባ መሆኑን ይኸው ጥናት ጠቁሟል። ጥናቱን ዋቢ አድርገው ማብራሪያ የሰጡት አቶ አሸናፊ እንደሚሉት “በፐብሊክ ሰርቪሱ ውስጥ የተንዛዛ ስብሰባ፣ አጀንዳ የሌለው ስብሰባ ውሳኔ የማይወሰንባቸው ስብሰባዎች” ተበራክተዋል። አቶ አሸናፊ እንደሚሉት ሰራተኞች እና ከፍተኛ አመራሮች “ስብሰባዎቻቸውን ከአቅማ ማነስ የተነሳ መደበቂያ” አድርገዋቸዋል።

የመንግሥት ሰራተኞች ከበላይ ሹማምንቶቻቸው በሚሰጧቸው ደራሽ ሥራዎች መጠመዳቸው ለጊዜ ብክነት ከዳረጓቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት ባለሙያው ገልጸዋል። አቶ አሸናፊ “ከበላይ አካል፤ ከበላይ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚመጡ ድንገተኛ የፖለቲካ እና የኮሚቴ ሥራዎች ሰራተኞች እና አመራሩ በተቋሞቻቸው ሥራ ላይ እንዳያተኩሩ አድርጓቸዋል” ሲሉ ያብራራሉ።

Filed in: Amharic