>
5:22 pm - Wednesday November 30, 2022

ዶ/ር ዐቢይ በፈረንሳዊው ምሁር ዓይን  (በተፈሪ መኮንን)

ዶ/ር ዐቢይ በፈረንሳዊው ምሁር ዓይን

 በተፈሪ መኮንን
ዶ/ር ዐቢይ ብዥታ፤ ግልጽ ያለመሆንና ተቃርኖም እንደሚታይባቸው ያትታል፡፡ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንባታ ተጨባጭ ዕቅዳቸውንም አላሳወቁም ይላል፡፡ አቅጣጫም ሆነ የጊዜ ሰሌዳ አላስቀመጡም በማለት ይተቻል፡፡ ደርግ ኢትዮጵያ ትቅደም እንዳለ፤ ዶ/ር አቢይም ‹‹መደመር›› የሚል መፈክር እንዳላቸው ከገለጸ በኋላ፤ ‹‹ግን መደመር ወይም አንድነት ለምን?” ሲል ጥያቄ ያነሳል፡

አሁን በሐገራችን የሚታየው ችግር ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ በተለያየ ዘርፍ የሚገኙ የውጭ እና የሐገር ቤት ምሁራን  ጥናቶችን እያደረጉ አስተያየታቸውን እያቀረቡ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ፖለቲካና ታሪክ በመከታተል የሚታወቀው  ፈረንሳያዊው አጥኚ ረኔ ለፎርት RENÉ LEFORT) ከአንድ ወር በፊት ‹‹የሰከነ ሰላማዊ ፖለቲካ ወይስ የመበታተን አደጋ? ከጊዜ ጋር ሸቅድድም በኢትዮጵያ›› (21 August 2018) በሚል ርዕስ በጻፈው ጽሑፍ፤ ወቅታዊውን የሐገራችንን ሁኔታ በተመለከተ  አስተያየቱን አስፍሯል፡፡ እንዲህ፤ ‹‹የአዲስ አበባ የታክሲ ባለንብረቶች፤ በየካቲት 1966 ዓ.ም  የነዳጅ ዋጋ ተመን ጭማሪን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ወይም አድማ አካሂደው ነበር፡፡ ይህ አድማ ለምዕተ ዓመታት የቆየውን ዘውዳዊ ስርዓት ለውድቀት የሚዳርግ ሁነት ይሆናል ብሎ የገመተ ሰው ግን አልነበረም፡፡  በርግጥ ዘውዳዊው ስርዓት በስብሶ ወደቀ እንጂ በፖለቲካ ኃይሎች ግፊት ተገረሰሰ ለማለት አይቻልም፡፡ ዘውዳዊውን ስርዓት የተካውና ‹ሶሻሊስታዊ› መርህ እከተላለሁ ይል የነበረው ደርግ የተሰኘው ወታደራዊ ጁንታ፤ ውሎ ሳያድር የመገንጠል ጥያቄ ካነገበው የኤርትራና የትግራይ ነጻ አውጪ ቡድኖች ጋር ግጭት ውስጥ ገባ፡፡ በ1970ዎቹ አጋማሽ እነዚህ ታጣቂ ቡድኖች ደርግን ሊያሸንፉ ይችላሉ ብሎ መገመት የሚችል ሰው አልነበረም፡፡ ታዲያ እነዚህ ቡድኖች ቁርጠኝነት ያላቸው፣ በዲስፕሊን የታነጹና በማስተዋል የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መሆናቸው ባይካድም፤ ደርግ የወደቀው በእነርሱ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን፤ በራሱ ድክመት ጭምር ነበር›› በሚል ገለጻ፤ ጽሑፉን የከፈተው ረኔ ለፎርት፤ ‹‹በጥቅሉ፤ የአጼ ኃይለ ሥላሴም ሆነ የደርግ መንግስታት አወዳደቅ አስገራሚ ነበር፡፡ ምክንያቱም በተመልካች ዘንድ ጠንካራ ተደርገው የሚታዩ መንግስታት ስለነበሩ›› ይላል፡፡
አጼ ኃይለ ሥላሴም ሆኑ የደርጉ መሪ ወደ ሥልጣን ሲመጡ፤ ሐገሪቱን ወዴት ሊወስዷት እንዳሰቡ ግልጽ ነገር ባያስቀምጡም፤ ሰፊ የህዝብ ድጋፍ እንደ ነበራቸው የሚገልፁት ሬኔ ለፎርት፤ ‹‹ከአንዳንድ ሁኔታዎች አንጻር የአሁኑ መንግስትም ተመሳሳይ ሁኔታ አለው፡፡ ድንገት የተፈጠረው ሥር ነቀልና ፈጣን የአመራር ለውጥ፤ ለውጡን ተከትሎ የተፈጠረው ከፍተኛ የህዝብ ተስፋና ለመገመት አስቸጋሪ የሆነ የወደፊት ሁኔታ ተመሳሳይ ስሜት ይፈጥራሉ፡፡” ይላል፡፡
ወታደራዊ መዋቅሩን፣ የጸጥታ አገልግሎት መስሪያ ቤቱን፣ መንግስታዊ እና ከፊል መንግስታዊ  የንግድ ዘርፉን (para-public business sector)  ህወሓት እንደ ተቆጣጠረ የሚገልጹትና ሌሎቹን የግንባሩ አባል ድርጅቶች የህወሓት ተላላኪ አድርጎ የሚያቀርበው ረኔ ለፎርት፤ ‹‹የግንባሩም ጥንካሬ የሚመነጨው፤ ድርጅቱ ከነደፈው ግልጽ ስትራተጂ፣ እንደ ብረት ከጠነከረው የፓርቲ ዲስፕሊንና ከትግራይ ህዝብን ሰፊ ድጋፍ ነው›› ይላል፡፡
አያይዞም፤ ‹‹ይሁንና ግንባሩ አድራጊ ፈጣሪ ኃይል የነበራቸውን አቶ መለስ ዜናዊን በድንገተኛ ሞት በማጣቱ ዛሬም ከደረሰበት ጉዳት ማገገም አልቻለም›› የሚለው ለፎርት፤ ‹‹የሥልጣኑ ፒራሚድ በእርሳቸው ልክና ለእርሳቸው የተገነባ በመሆኑ፤ አቶ መለስ ከቦታው ሲጠፉ፤ ስርዓቱ በቅጽበት ተንገዳገደ፡፡ ግንባሩ (ህወሓት) አቶ መለስ በዙሪያቸው የፈጠሩትን የስልጣን ቫክዩም፤ እንደ እርሳቸው ቆንጥጦ የሚገዛ ሌላ ጠንካራ መሪ ፈጥሮ መተካት ወይም በትግሉ የመጀመሪያ ዓመታት ድርጅቱን ውጤታማ ወዳደረገው የጋራ አመራር ለመመለስ ባለመቻሉ፣ በእርሳቸው ሞት ከደረሰበት ጉዳት ለማገገም አልቻለም›› ሲል ጽፏል፡፡
በ2006 ዓ.ም የጸደይ ወራት አንጋፋዎቹ የግንባሩ አባላት (መሪዎቹ)፣ ከትግራይ ህዝብ ጋር ውይይት ለማድረግ ወደ ክልሉ በሄዱ ጊዜ ጊዜ አስደንጋጭ ነገር ነበር የገጠማቸው የሚለው ጸሐፊው፤ በወቅቱ በዳዴ የሚሄድ ለውጥ መፈጠር ጀምሮ እንደነበር እና ‹‹በባለሥልጣናቱ ለከት የለሽ አምባገነናዊና ከበርቴያዊ ዝንባሌ (authoritarian and oligarchic excesses) የተንገሸገሸው፤ በአዳዲስ መሪዎች አለመፈጠር ቅር የተሰኘውና ከሌሎች ክልሎች ጋር በንጽጽር ሲታይ ወደ ኋላ በቀረው የኢኮኖሚ ዕድገቱ የተከፋው፤ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር የነበረው ግንኙነት ‹ሰላም የለሽ-ጦርነት የለሽ› ሆኖ ለዓመታት በመዝለቁ የተበሳጨው የትግራይ ህዝብ፤ በዚያን ወቅት ፊቱን ከግንባሩ ማዞረ እንደ ጀመረ ገልጧል፡፡
‹‹ይህ በእንዲህ እንዳለ ህወሓት በገዢ ፓርቲ ዘንድ የነበረው የበላይነት በድንገት ፈራረሰ›› ያለው ረኔ ለፎርት፤ ‹‹የመዲናዋን የአዲስ አበባን የፖለቲካ ተጽዕኖ ወደ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የማስፋት ዓላማ ያለው›› በሚል የጠቀሰው የአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን፤ የህዝባዊ የተቃውሞ ማቀጣጠያ መሣሪያ ሆኖ እንዳገለገለና ከፊሉ የኦህዴድ አካልም ይህን መነሻ አድርጎ ለአመጽ እንደ ተነሳሳ ያትታል። በአጠቃላይ ለኦሮሚያ ወጣቶች፤ በተለይም ቄሮ በሚል ለሚጠሩት ተማሪዎች፤ ማስተር ፕላኑ፣ ስፔን ከጎሽ ጋር ግብግብ የሚገጥሙ ሰዎች እንደሚይዙት ቀይ ጨርቅ ሆነ ይላል፡፡
‹‹ስለዚህ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ የበላይነት የተሰነካከለውን የፌዴራል ስርዓት የሚቃወም የአመጽ ማዕበል ተነሳ፡፡ መንግስትም ማስተር ፕላኑን ትቼለሁ አለ፡፡ በአመጽ የተሳተፉት ወገኖች በዚህ እርምጃ ይበልጥ ተደፋፈሩ፡፡ ሁለት ዓመት ቆይቶ (በ2008 ዓ.ም ክረምት ወራት) የተወሰነ የአማራ ክልል አካባቢ አመፁን ተቀላቀለ፡፡ በመጀመሪያ፤ ኦህዴድ እና ብአዴን ይህን ግብታዊና ያልተደራጀ ህዝባዊ አመጽ፤ ህወሓት በግንባሩ የያዘውን የበላይነትን በመጠኑ ለማዳከም የሚያስችል ዕድል አድርገው ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ተረዱ፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ድርጅቶች የአመጽ እንቅስቃሴው የራሱን ጎዳና እንዲከተል ፈቀዱለት። እንዲያውም በእጅ አዙር አመፁን ያበረታቱ ነበር›› የሚለው ረኔ ለፎርት፤ የመንግስት ባለሥልጣናት ለችግሩ ይሰጡት የነበረው ምላሽ በኃይል ብቻ የተመሠረተ እንደ ነበር እና የኃይል እርምጃው የፈየደው ነገር እንዳልነበረ ጠቅሶ፤ ‹‹አመራሩ በተደጋጋሚ ጉባዔ እየተቀመጠ ቢመክርም፤ ሁከቱ ከመባባስ በቀር ሊገታ የማይችል ሆነና አመፁ እየተጋጋለ ሄደ›› ይላል፡፡
ህወሓት ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሔ መፍጠር እንደ ተሳነው በግልጽ ታየ፡፡ ጉዳዩን የሚከታተሉ ታዛቢዎችም ኢትዮጵያ ወደ አደገኛ ሁኔታ እያመራች መሆኑን ማሰብ ጀመሩ፡፡ የብሔር ግጭቱም ተባብሶ የሐገሪቱ ህልውና ሊያበቃለት ወይም ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሊካሄድ ይችላል የሚል እምነት ያዙ፡፡ ህወሓት ወደ ዋሻው ገባ፡፡ ኦህዴድ እና ብአዴንም ህብረት እንዳይፈጥሩ ማድረግ አልቻለም፡፡ የሁለቱ ድርጅቶች ህብረትም ኦህዴድን የግንባሩ ግንባር ቀደም ኃይል ሆኖ የመውጣት ዕድል ፈጥሮለት፤ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጠ/ሚ ለመሆን እንደበቁ ለፎርት ያስረዳል፡፡
አክሎም ‹‹ዶ/ር ዐቢይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳዎችን ማዥጎድጎድ ጀመረ፡፡ የለውጡ ፍጥነትና ክረት ጨርሶ ሊታሰብ የሚችል አልነበረም። የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሊበራላይዜሽን እርምጃ ወሰደ፡፡  ….. በዚህ መጠን የሚከንፍ የለውጥ ነፋስ ይነፍሳል ብሎ ለመገመት የሚችል ማንም ሰው አልነበረም›› የሚለውና ህወሓት የተከፋፈለ ድርጅት መሆኑን የሚጠቁመው ለፎርት፤ በሌላ ምክንያትም ባይሆን ተጨባጭ ሁኔታው የሚፈልገውን ለማድረግ ወይም መዳን የሚችለውን ነገር ሁሉ ለማዳን በማሰብ ህወሓት ራሱን መልሶ ለማደራጀት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሶ፤ የማይናቅ ቁጥር ያላቸው፤ ምናልባትም አብዛኛው የህወሓት አባላት የሥልጣን ሽግግሩን የሚደግፉ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ በጥቅሉ ትግራይ የዶ/ር ዐቢይን መምጣት፤ የሊበራላይዜሽን እርምጃውንና ዶ/ር ዐቢይ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ያሳዩትን ቁርጠኝነት እንደተቀበለው ያትታል፡፡
አያይዞም፤ ‹‹ህወሓት እንደ አንድ በህብረት የቆመ አካል የፀና፤ ኃይሉን አስተባብሮ የተደራጀ፤ እንዲሁም አንዳንዶች እንደሚሉት ሁሉን ማድረግ የማይሳነው፤ የትግራይን ህዝብ ልባዊ ድጋፍ ያገኘ እና ዶ/ር ዐቢይን ለማጥፋት ቁርጠኛ አቋም የያዘ ድርጅት ቢሆን ኖሮ፤ ዶ/ር ዐቢይ ግንባሩ እንደ ጽላት ይመለከታቸው የነበሩ ቀኖናዎችን እንዲህ በቀላሉ እየነቀለ ለመጣልና በከፍተኛ የወታደራዊ፣ የጸጥታና የፖለቲካ ሥልጣን ኮርቻ ላይ የተቀመጡትን የህወሓት አባላት እንዲህ በአጭር ጊዜ መገንደስ ባልቻለ ነበር›› ይላል፡፡ እንዲሁም ‹‹ማጉረምረም ባልተለየው ሁኔታም ቢሆን ዶ/ር ዐቢይ ወሳኝ የለውጥና የሹመት እርምጃዎችን ሲወስድ የግንባሩን ስምምነት ለማግኘት ባልቻለ ነበር››  ይላል ሬኔ ለፎርት፡፡
‹‹ታዲያ ይህን ስንል፤ ለዶ/ር ዐቢይ መንገዱ ሁሉ ወለል ብሎ ተከፍቶለታል ማለት ነው?›› የሚል ጥያቄ የሚያነሳው ለፎርት፤ መልሱ  በፍፁም የሚል ነው፡፡ በህወሓትም ሆነ በሌሎች የግንባሩ አባል ድርጅቶች፤ እንዲሁም በወታደራዊ፣ በፀጥታና በሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የሁሉም ብሔሮች አባላት የሆኑ ጥቅማቸውና ሥልጣናቸው የተነካባቸው ወይም ለውጡ ሥጋት የፈጠረባቸው ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ግለሰቦች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል የቻሉትን መጥፎ ነገር በማድረግ ዐቢይን ከሥልጣን ለማውረድ ዝግጁ የሆኑ ሰዎች ያለ ጥርጥር ይኖራሉ ይላል፡፡ በመስቀል አደባባይ እንደታየው የሰኔ 16ቱ ያለ በቀቢጸ ተስፋ የተገፋ አደገኛ የማጥቃት እርምጃም ሊከሰት መቻሉ አያጠራጥም የሚለው ሬኔ ለፎርት፤ ‹‹ነገር ግን እነዚህ ‹የጨለማ ኃይሎች› የሚደራጁትና በመላ ሐገሪቱ የሚታዩትን ግጭቶች ሁሉ የሚሸርቡት፤ ‹በአክራሪው› የህወሓት ስውር እጆች ነው የሚል ክስ፤ እስካሁን እንደታየው የተጨባጭ እውነታ ድጋፍ የሌለውና ህወሓትን ዓላማ ያለው፤ በደንብ የተደራጀና ምንም ማድረግ የማይሳነው ድርጅት አድርጎ መሳል ነው›› ሲል ጽፏል፡፡
አዲሱ የአመራር ቡድን አዘውትሮ ስለ ‹‹መደመር›› እና ‹‹ይቅርታ›› የሚናገር ቢሆንም በትግራይ ልሂቃን ላይ ከበድ ያለ ጡጫ የሚያሳርፍና ለኦሮሞ ልሂቃን ደግሞ ለየት ያለ አቀባበል የሚያደርግ አመራር ሆኖ መታየቱን  አመልክቷል፡፡ ምንም እንኳን አተገባበሩ እንከን የለሽ ባይሆንም፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ሊቀለበስ የማይገባው አወቃቀር አድርገው የሚመለከቱትን የፌዴራል ስርዓት እውን በማድረግ ረገድ እና ደርግን በመገርሰስ ሂደት ህወሓት ያደረገውን ጥረት አዲሱ የአመራር ቡድን የሚያኪያኪስ ሆኖ ይታያል፡፡ ትልልቆቹን ባለሥልጣናት የማውረድ እርምጃ መውሰድ ብቻ ሳይሆን፤ ተራ የመንግስት ሠራተኞችም ከብሔር ፍላጎት ውጪ አይሆኑም ከሚል እሳቤ ደመወዝና ሥልጣናቸውን እንደያዙ ወደ ጎን ገፋ የተደረጉበት ሁኔታ መስተዋሉንም ይገልጻል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ በሐገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከተከሰቱ ግጭቶች ጀርባ ያሉ ‹‹የፖለቲካ ነጋዴዎች›› ሲሉ፤ ‹‹በአጥፊ ተግባራት›› የተሰማሩ ‹‹ሁከት ቀስቃሾች›› ሲሉ፤ እንዲሁም  በሰኔ 16ቱ ጥቃት ኃላፊነት የሚወስዱት ኢትዮጵያ አንድ ሆና ማየት የማይሹ ኃይሎች ናቸው›› በሚል የተናገሯቸው ቃላት፤ በዘወርዋራ መንገድ በትግራይ ልሂቃን ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው፡፡ እነዚያ ንግግሮች በህዝብ አስተያየት ያገኙት ትርጉም ከዚህ የተለየ አልነበረም የሚለው ፀሐፊው፤ ዶ/ር ዐቢይ እና የቅርብ አጋሮቹ፤ ቀደም ሲል ‹‹አሸባሪ›› በሚል ይታሰቡ የነበሩትንና ባለፉት ሁለት አስርት ህወሓትን በማራከስ የጋራ አስተሳሰብ ሲያራምዱ የቆዩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ሞቅ ባለ ዝግጅትና ስነ ስርዓት፣ በፈገግታና በማቀፍ ሲቀበሉ፤ በአማራና በኦሮሞ የተለያዩ ክበቦች ነጥብ ማስመዝገብ ቢያስችላቸውም፤ በህወሓት እና በትግራይ ተወላጆች ዘንድ የመገፋት ስሜት መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡ ይህ እርምጃ ለኋለኞቹ ከስድብ የሚቆጠር ነው፡፡ እንደ ጠላት እንዲታዩ በማድረግ ወደ መጨረሻው ጠርዝ እንዲሄዱ የመግፋት አደጋን የሚፈጥር ነው፡፡ ለአንዳንድ አክራሪዎችም የመጨረሻው ጠርዝ መገንጠል ነው፡፡ ምንም እንኳን ከውሱን ክበቦች አልፎ የሄደ አጀንዳ ባይሆንም፤ በአንዳንድ ተጋሩዎች ዘንድ መገንጠል እንደ አንድ አማራጭ እየተነሳ ውይይት ሲደረግበት የነበረ አጀንዳ ነው ይላል፡፡
ለወትሮው ህውሓትን በጽኑ በመተቸት የምናውቀው ረኔ ለፎርት አክሎ፤ አብዛኛዎቹ ሰዎች አሁን ያለው መድረክ በቀድሞ ባለሥልጣናትና ከበርቴ ሊሂቃን (old governing and oligarchic elite በዋናነት የትግራ ተወላጆች በሆኑ) እና በዶ/ር ዐቢይ አህመድ በሚመሩ ‹‹ለውጥ አራማጆች›› (reformists) መካከል ግብግብ የሚካሄድበት መድረክ አድርገው ይወስዱታል። ‹‹ጠ/ሚኒስትሩ የማዘዝ ሥልጣን የያዙበት፤ ነገር ግን እና ህውሓት የሚቆጣጠርበት›› (The Prime Minister commands but the TPLF controls) መድረክ ያደርጉታል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች ሐገሪቱ በሁለት ባለሥልጣናት አገዛዝ ሥር ነች እስከ ማለት ይሄዳሉ፡፡ አንዳንዶች ‹‹ጠ/ሚኒስትሩ መተካከል የማይችሉት የሥልጣን መዋቅር በህወሓት እጅ አለ›› እንደሚሉ የሚገልጸው ለፎርት፤  ‹‹በእነሱ አስተያየት ይህ ‹ጥልቅ መንግስት› ወይም ‹ወደረኛ መንግስት› አሁንም የበላይነቱን እንደያዘ ነው፤ በተለይ በመከላከያና በጸጥታ ኃይሉ ውስጥ›› ሲል ያክላል፡፡
‹‹የሆነ ሆኖ ህወሓት በፖለቲካው ጨዋታ ራሷን ለማጠናከር እየሰራች መሆኑ ግልጽ ነው›› የሚለው ፀሐፊው፤ ለመሆኑ ዐቢይ አህመድ ማናቸው? ወዴት ለመሄድስ ይፈልጋሉ? የሚል ጥያቄ ያነሳል፡፡ ላነሳው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥም፤ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የአገዛዝ መዋቅሩ ውጤት መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ ነገር ግን በባህርይ፣ በቃልም ሆነ በተግባር ከምንጫቸው ርቀው የኮበለሉ፤ ከ1983 ጀምሮ የተገነባውን የአምባገነን ስርዓት ጡብ አንድ በአንድ እያነሱ የሚያፈራርሱ ሰው ናቸው ይላል፡፡ ይህም ሰፊ ህዝባዊ ተቀባይነት እንዳስገኘላቸውና አብረቅራቂ የሰብእና አምልኮ ጭምር የፈጠረላቸው መሆኑን ይገልፃል፡፡ ዶ/ር አቢይ ያለመታከት የሥነ ምግባር እሴቶችን እንደሚሰብኩና እንደ አብነት በሰኔ 16ቱ መድረክ ለ18 ደቂቃ ንግግር ሲያደርጉ 22 ጊዜ ‹‹ፍቅር›› የሚል ቃል እንደተናገሩ ጠቅሷል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ዴሞክራሲንና ከፈት ያለ (ሊበራል) ኢኮኖሚ የመፍጠር ፍላጎታቸው እውነተኛ መሆኑን ገልጾ፤ ግን ‹‹ዴሞክራሲንና ሊበራል ኢኮኖሚ›› ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ይጠይቃል፡፡ ከእነሱ ለመድረስም የሚከተሉት መንገድ ግልጽ አለመሆኑን ይናገራል፡፡ በዚህ ረገድ ዶ/ር ዐቢይ ብዥታ፤ ግልጽ ያለመሆንና ተቃርኖም እንደሚታይባቸው ያትታል፡፡ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንባታ ተጨባጭ ዕቅዳቸውንም አላሳወቁም ይላል፡፡ አቅጣጫም ሆነ የጊዜ ሰሌዳ አላስቀመጡም በማለት ይተቻል፡፡ ደርግ ኢትዮጵያ ትቅደም እንዳለ፤ ዶ/ር አቢይም ‹‹መደመር›› የሚል መፈክር እንዳላቸው ከገለጸ በኋላ፤ ‹‹ግን መደመር ወይም አንድነት ለምን?” ሲል ጥያቄ ያነሳል፡፡ ይህስ ነገር የራዕይ አለመኖር፣ ታክቲካዊ ብልጠት ወይስ የአቅም ችግር ነው?
ለፎርት የአቢይ የሥልጣን መሠረት ከሁሉ በላይ በህዝብ ዘንድ ያላቸው ተወዳጅነት መሆኑን ይናገራል። ቀደም ሲል የተገፉና የተጨቆኑ የፖለቲካ ኃይሎች፤ አምባገነናዊ ስርዓቱን በማፈራረሳቸው ከፍተኛ ደጋፍ እንደሰጧቸው ገልፆ፤ የግንባታ ዕቅዳቸውን በተጨባጭ ሲያስቀምጡ፤ ይህ ድጋፍ ሊቀጥል ይችል ይሆን በማለት ጥያቄውን ያስከትላል፡፡ ጠቅላላ የፖለቲካ አሰላለፉን የሚወስኑ ሁለት አጀንዳዎች መኖራቸውንና ከእነዚህ አጀንዳዎች አንዱ ፌዴራሊዝም መሆኑን በመጥቀስ፤ በዚህ ረገድ የዶ/ር አቢይን አቋም ያሳያል ብሎ ያመነበትን የኢትዮጵያ-ሶማሌን ጉዳይ በመጥቀስ ይተነትናል፡፡ ሁለተኛው ነጥብ የኢኮኖሚ ሊበራላይዜሽንን የሚመለከት ሲሆን፤ ይህንም ከአነስተኛ ባለሀብቶች አንጻር እና ድርጅታቸው ኦህዴድ (ኦዴፓ) ከዚህ በፊት ከመሬት ጋር ተያይዞ በወሰዳቸው አቋሞች ሚዛን እያዩ፣ የፖሊሲ ለውጥ እርምጃቸውን ተገቢነት ይመዝናል፡፡ ዶ/ር አቢይ የተለያዩ የሥልጣን አካላትን ገሸሽ እያደረጉ ብቻቸውን የሚወስኑ ‹‹ትልቅ ሰው›› (ግን ለስላሳ) ሆነው መታየታቸውን በመጥቀስ፤ ምናልባት የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ ካልሆነ በቀር ሌላ የሚገድባቸው ኃይል የሌላቸው መሪ አድርጎ ያቀርባቸዋል፡፡
ይህም አካሄድ ዶ/ር ዐቢይ ሊፈጥሩ የሚመኙትን ዴሞክራሲ ሊያጠፋባቸው እንደሚችል ያስረዳል። ረኔ ለፎርት፤ ‹‹ህዝቡም በዚህ አካሄድ ምንም ችግር እንደማይሰማውና ዶ/ር ዐቢይን ከቃል ኪዳን ምድር የሚያደርሱ መሲህ አድርጎ በመመልከት ዝም ብሎ መከተሉን መርጧል ይላል፡፡ በመጨረሻም የወደፊቱን ጎዳና ዛሬ መተንበይ አስቸጋሪ እንደሚሆን የጠቀሰው ረኔ ለፎርት፤ ‹‹ባለፈት ጥቂት ወራት የታዩት አስደናቂ የለውጥ እርምጃዎች ኢትዮጵያን ከሲዖል በር እንድትርቅ ያደረጋት ቢሆንም፤ አሁንም ሁሉም አማራጮች በጠረጴዛው ላይ አሉ – ከእጅግ በጣም መጥፎው እስከ እጅግ በጣም ጥሩው›› በማለት ይደመድማል፡፡  ረኔ ለፎርት የተማመነበት ጠቅላላ ጉባዔ ምን እንደወሰነ አላወቅኩም፡፡
ፈረንጆቹ ዜሮ ሰዓት የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ 1945 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ለጀርመኖች ‹‹ዜሮ ሰዓት›› ነበር፡፡ ከዚያ ነጥብ ጀምረው በአዲስ መንፈስና ጎዳና ጉዞአቸውን እንደ አዲስ ቀጠሉ፡፡ የዌመር ሪፐብሊክ የፈፀማቸውን ስህተቶች ላለመድገም በብርቱ ተጠነቀቁ፡፡ አዲስ ሀገርና ህብረተሰብ ለመፍጠር ጉዞ ጀመሩ፡፡ በአጭር ጊዜ ከግባቸው ደረሱ፡፡ 2011 የኢትዮጵያ ዜሮ ሰዐት ይሆናል፡፡

Filed in: Amharic