>
3:49 am - Friday February 3, 2023

ዛሬም ሌላ የማስጠንቀቂያ ደወል ተሰማ! (አፈንዲ ሙተቂ)

ዛሬም ሌላ የማስጠንቀቂያ ደወል ተሰማ!
አፈንዲ ሙተቂ
አዎን! ልብ ብላችሁ ስሙኝ! ልብ ብላችሁ አድምጡኝ!
 
“ኢትዮጵያ ድንቅ ሀገር” ብለን ሀገራችንን እናሞካሻለን። ነገር ግን ዓለም የረሃብ፣ የድህነት እና የኀላቀርነት ተምሳሌት አድርጎ ነው የሚወስደን። “የኮራሁ ኦሮሞ” “ቀብራራው አማራ” “ልበ ኩሩው አፋር” እያልን በብሄራችን እንኩራራለን። ነገር ግን አብዛኛው የዓለም ህዝብ እንዲህ የሚባሉ ብሄሮች መኖራቸውን እንኳ አያውቅም። ሌላው ቀርቶ የበርካታ ሀገራት ዜጎች ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ስፍራ እንኳ አናውቅም። በኬኒያ ሁለት ተማሪዎች ቢገደሉ ወሬው ወዲያውኑ የዓለም ዜና ይሆናል። በህንድ አንዲት ወጣት ስትደፈር ዓለም በሙሉ ይንጫጫል። በኢትዮጵያ አንድ መቶ ሰዎች በፖሊስ ከተገደሉ ግን ወሬውን ዞር ብሎ የሚያይ የለም።
—–
ይህ ህዝብ ብዙ ተበድሏል። ተጨቁኗል። ነፃነቱን አጥቶ ታፍኖ ተገዝቷል። በተበላሸ ፖሊሲ ተቀፍድዶ በድህነት ማቅቋል። ጥቂቶች እንዳሻቸው እየፈነጩ ብዙሃኑን በዝብዘውታል።
ህዝቡ ነፃነቱን ለመቀዳጀት ለዓመታት ያልተቋረጠ ትግል አድርጓል። ትግሉ ፈር ይዞ ፍሬ ማሳየት የጀመረው ባለፉት ስድስት ወራት ነው። ህዝቡ ነፃነቱን ለመቀዳጀት ባደረገው ትግል ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሏል። ዘንድሮ የታየው ለውጥ ግን እጅግ ተአምራዊ ነው። “ቲም ለማ” የሚባለው የለውጥ ፈላጊዎች ቡድን በኢህአዴግ ውስጥ መከሰቱ ነው ትግሉ ውጤት እንዲያሳይ ያደረገው።
—–
እኛ ግን ፈጣሪያችንን አመስግነን ለውጡን ማስጠበቅ አልቻልንበትም። አብዛኛው ፖለቲከኛ፣ አክቲቪስት፣ ጦማሪ፣ የሚዲያ ተቋም ወዘተ ለውጡን በሚቀለብሱ ተግባራት ነው የተሰማራው። በውዝግብ፣ በንትርክ እና በጭቅጭቅ የለውጡን ፋና ያበራውን ቡድን አታከተነዋል። መቻቻልና መተሳሰብ የሚባል ነገር ከመሃላችን ጠፍቶ መበላላት ሰፍኗል። በዚህም የተነሳ ለውጡን ለመቀልበስ ለሚፈልጉ ኃይሎች የሚፈልጉትን ነገር እንዲሰሩ ሁኔታዎችን አመቻችተናል። በብሄርና በሃይማኖት እየተከፋፈልን፣ በባንዲራና በአርማ እየተጨቃጨቅን፣ በሃውልትና በፈረስ እየተናቆርን ማጅራት መቺዎቹ ለውጥ ፈላጊውን መንግስት በቀላሉ የሚያጠቁበትን መንገድ ከፈትንላቸው።
ባለፈው ጊዜ ቅጥረኞችን ገዝተው የብዙዎች ተስፋ ለመሆን የበቃውን ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ለመግደል ሙከራ አደረጉ። በዛሬው ዕለት ደግሞ “ጥቅማ ጥቅሞቻችን አልተከበሩም፣ ዶ/ር ዐቢይን ማናገር እንፈልጋለን” የሚል ተልካሻ ጥያቄ ያነገቡ ኃይሎች እስከ ቤተ መንግስቱ ድረስ ዘለቁ። ከዚህ በኋላ የሚደረገው ሙከራ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ ይቀፋል።
—–
ለመሆኑ እነዚህ ጡንቻቸውን እያሳዩ የሚንጎማለሉ ኮማንዶዎች መሳሪያቸውን ይዘው እስከ ቤተ መንግስቱ ድረስ ዘልቀው የሄዱት የደመወዝ ጭማሪ ለመጠየቅ ነው ሲባል አምናችሁ ነበርን??? ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ጉዳዩን ለማቃለል የተሰጠ ምክንያት ይመስላል።
—-
ጎበዝ! ይህ የመጨረሻ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው። በብዙዎች መስዋእትነት የመጣውን የለውጥ ጉዞ መጠበቁን ትታችሁ የምትናቆሩ ከሆነ ለሚቀጥለው ዓመት እንደዚህ በነፃነት ማውራታችን ያጠራጥራል። ስለሆነም ተቻቻሉ! ተደማመጡ! ነቆራና ጭቅጭቁን ተውት! በጊዜያዊ ክስተቶች ተጠምዳችሁ የሩቅ ጉዞአችንን አታሰናክሉ።
Filed in: Amharic