>

ለዓድዋ ጦርነት ጉዞ የተጀመረበት ቀን 123ኛ ዓመት መታሰቢያ! (ልዑል ዓምደ ጽዮን ሠርፀድንግል)

ለዓድዋ ጦርነት ጉዞ የተጀመረበት ቀን 123ኛ ዓመት መታሰቢያ!
ልዑል ዓምደ ጽዮን ሠርፀድንግል
ከታሪካዊው የክተት አዋጅ አንፃር የዳግማዊ አጤ ምኒልክን ባህርያት የተመለከትኩበት አጠር ያለ ዳሰሳ
(ልዑል ዓምደጽዮን ሰርፀድንግል)
ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም የውጫሌ ውል (‹‹Wuchale Treaty››)ን እንደማይቀበሉና ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከወራሪ ጠላት እንዲካለከሉ የሚያሳስብ ታሪካዊ አዋጅ ካስነገሩ በኋላ፣ ጦራቸውን ይዘው ከአዲስ አበባ ወደ ዓድዋ ጉዞ የጀመሩት ከዛሬ 123 ዓመታት በፊት (ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም) ነበር፡፡
ንጉሰ ነገሥቱ ዙፋናቸውን ለአጎታቸው ለርዕሰ-መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ (የአባታቸው የንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ ወንድም) አደራ ሰጥተው ወደማይቀረው የነፃነት ፍልሚያ ጉዞ ጀመሩ፡፡ ከአዲስ አበባ ሲነሱም እቴጌ ጣይቱም አብረው ተነሱ፡፡
ይህንን የዓድዋ ዘመቻ ጉዞ የተመለከተው አንድ የባህር ማዶ የታሪክ ፀሐፊ ‹‹ … ሲጓዙ በደንብ ተመልክቻለሁ፤ ዳገቱን ሲወጡ ቁልቁለቱን ሲወርዱ ሸለቆውን ሞልተው ሲሄዱ እየተጯጯሁ ነው፤ ለውጊያ የሚሄዱ አይመስሉም፡፡ ሴቶች፣ ሽማግሌዎች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ሕጻናትና ቄሶች ሁሉ ሳይቀሩ አብረው በአንድነት ይጓዛሉ፤ እኔ እንዳሰብኩት ለጦርነት የሚሄዱ የጦር ወታደሮች አይመስሉም ፡፡ ሕዝቡ በሙሉ ተነቅሎ ለወረራ የሚሄድ ይመስላል›› በማለት በግርምት ጽፏል፡፡
በሌላ በኩል ለዘመቻው የሄደው ሰው ለጉዞ የሚሆን ደንበኛ ልብስ ስለሌለው ሐሩር እያቃጠለው እንደነበር፣ ሲታመምም የባህል መድኃኒት እንጂ ሌላ የተሻለ ህክምና እንደማያገኝ፣ የረባ መሳሪያ እንዳልታጠቀ … ሌሎች የታሪክ ፀሐፍት ጽፈዋል፡፡
ዳግማዊ አጤ ምኒልክ የሰው ደም በከንቱ እንዳይፈስ ደጋግመው ሰላማዊ የመፍትሄ አማራጭ ቢያቀርቡም ‹‹አሻፈረኝ›› ያለውን የጣሊያንን መንግሥት አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት ጎዞ የጀመሩበትን ታሪካዊ ቀን ምክንያት በማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከወራሪ ጠላት እንዲካለከሉ ያሳሰቡትን ታሪካዊ አዋጅ ይዘቱንና የንጉሰ ነገሥቱን ባህርያት ለመመልከት የሞከርኩበት ጽሑፍ (የግል ምልከታ) እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
በቅድሚያ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም የታወጀውን አዋጅ እንደወረደ እናስቀምጠውና እንመልከተው፡፡
‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፤ እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም፤ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁን ግን ሀገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚያስለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፤ እኔም ያገሬን ከብት ማለቅና የሰውን መድከም ዐይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፤ ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ! ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህና ለሀይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ! ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ! አልተውህም! ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም! ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ!›› ይላል፡፡
የክተት አዋጁ የንጉሰ ነገሥቱን ባህርያት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው አዋጁ ንጉሰ ነገሥቱ ጎበዝ የፖለቲካ ሰው፣ ቆራጥ፣ ሀገር ወዳድ፣ … እንደነበሩ ያሳየናል፡፡ ‹‹የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፤አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡›› ሲሉ ‹‹የበደልኩህ አልመሰለኝም››ነው እንጂ ‹‹አልበደልኩህም›› አላሉም፡፡ ንጉሱ ራሳቸውን ፍፁም አድርገው አላቀረቡም፡፡ ሕዝቡን ግን ‹‹አልበደልከኝም›› ሲሉት ሕዝብ ተበዳይ እንጂ በዳይ እንደማይሆን ዐሳይተዋል፡፡ ሌላውደግሞ ህዝብ እንዳላስቸገራቸው እርሳቸው ግን ህዝቡን አስቀይመውት ሊሆን እንደሚችል ሲጠራጠሩ በፖለቲካ ዓለም ፖለቲከኞች ፍፁም (መቶ በመቶ) ሊወደዱ እንደማይችሉ አመላክተዋል (እኛ በዘመናችን እንደሰማነው መቶ ፐርሰንት ምናምን የሚባል ነገር የለም) … ይህ ደግሞ የንጉሱን ዴሞክራሲያዊነታቸውንና ፖለቲካ አዋቂነታቸውን ጭምር ያሳያል፡፡ ለዚያም ነው አንጋፋውና ዝነኛው ዓለም አቀፉ The Washington Times ጋዜጣ ንጉሰ ነገሥቱ በታመሙበት ወቅት ‹‹Menelik of Abyssinia, The Most Democratic of All Monarchs ›› ብሎ የገለፃቸው!
በአዋጁ ውስጥ የእግዚአብሔር ስም ደጋግሞ ተነስቷል፡፡ ይህ ደግሞ ንጉሱ በእግዚአብሔር እንጂ በጠመንጃቸው ብዛት እንዳልተመኩ ያሳያል፡፡ ይህን የምለው ክርስቲያን ስለሆንኩ አይደለም፡፡ መሪ ስትሆን በስራህ ጥሩነት እንጂ በጠመንጃ ብዛት መመካት ተገቢ አይደለም ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ንጉሱም ‹‹እግዚአብሄር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ … እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል … እግዚአብሔር እስካሁን አላሳፈረኝም፤ ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አላምንም … በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም›› ያሉት ለኢትዮጵያ የሰሩት ጥሩ ስራ መተማመኛ ስለሆናቸው ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ የአሜሪካ መሪዎች እንኳ ንግግሮቻቸውን የሚያሳርጉት ‹‹God Bless You. God Bless the United States of America. /ፈጣሪ ይባርካችሁ … ፈጣሪ አሜሪካን ይባርክ›› ብለው ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአሜሪካ ሕገ-መንግሥትና በምክር ቤቶቹ ውስጥ እንኳ ጎላ ብሎ የሚታየው ‹‹In God We Trust›› የሚለው ጽሑፍ ነው፡፡ መተማመኛህ መልካም ስራህና ፈጣሪ ሲሆኑ ውጤቱ ድል ነው! ምኒልክም ለዚህ ማስረጃ ናቸው!
‹‹እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም›› ሲሉ፣ በአንድ በኩል የሀገራቸው በጠላት መወረር እንደሚያስጨንቃቸውና የእርሳቸው ሞት ከሀገራቸው መደፈር ጋር ፈፅሞ ሊወዳደር እንደማይችል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሞት የሁሉም ሰው ዕጣ ፈንታ በመሆኑ እንኳን መሪ የሆነ ሰው ይቅርና ሌላውም ሰው በሕይወት ዘመኑ ለራሱና ለሀገሩ ቢያንስ አንድ መልካም ተግባር አከናውኖ ማለፍ እንዳለበት ያስገነዝባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ይህ ንግግራቸው ሞት መኖሩን  ‹‹እኔም ያገሬን ከብት ማለቅና የሰውን መድከም ዐይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር›› ሲሉ ንጉሰ ነገሥቱ ወራሪው የጣሊያን ጦር ወደሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየዘለቀ ሲገባ ወዲያውኑ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አልፈለጉም፡፡ አቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያን ጨምሮ ሌሎች አንጋፋ የታሪክ ፀሐፍት እንደፃፉት፣ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ከነገሱ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የከብት በሽታ ወደኢትዮጵያ ገብቶ ከብቱ ሁሉ አልቆ፣ ሰውም በረሃና በችግር ተፈትኖ ነበር፡፡የወላይታው ገዢ ካዎ ጦና ‹‹አልገብርም›› ብሎ ሸፍቶም ስለነበር እርሱን እስኪያስገብሩና የወላይታ ሕዝብም ለዘመቻው ድጋፍ እንዲሰጣቸው መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ ኢትዮጵያም ከኢጣሊያ የተበደረችው ገንዘብ ነበርና ንጉሰ ነገሥቱ እዳውን ሳይከፍሉ ከኢጣሊያ ጦርነት መግጠም ስላልፈለጉ የተወሰነ ጊዜ በብልሃት አገኙ፤ እርሳቸውም ይህን ሁሉ ችግር ዕያዩ በረሀብና በችግር በደከመ ጦር ሊዋጉ አልፈለጉም፡፡
በሽታውና ረሀቡም እየቀነሰ መጣ፤ ካዎ ጦናም በተደጋጋሚ ቢለመን ‹አሻፈረኝ› ብሎ በጦርነት ተሸንፎ ገበረ፤ ብድሩም ተከፈለ፡፡ እነዚህን ሁሉ ችግሮች በብልሃትና አማራጭ ነው ባሉት ዘዴ ሁሉ አለፉና ሙሉ ትኩረታቸውን ወደማይቀረው የነፃነት ዘመቻ አደረጉ፡፡ ይህ በዋጋ የማይተመን ተግባር ደግሞ ምን ያህል ብልሃትና ታጋሽነት እንደሚጠይቅ ማሰብ ቀላል ነው፡፡ በእርግጥም ንጉሰ ነገሥቱ ብልህ፣ ታጋሽ፣ … ናቸው!
ንጉሰ ነገሥቱ ‹‹ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ›› ሲሉ ሁሉንም እንደየችሎታውና እንደየአቅሙ የማገዝና የመሰማራት ነፃነት ሰጥተውታል፡፡ ሁሉም በሚችለው እንዲረዳና እንዲሳተፍ በሩን ከፈቱለት እንጂ ‹‹My Way or No Way/ ከእኔ ውጭ ወደ ውጭ/እኔን ምሰል አለበለዚያ መንገድ የለህም›› እንደሚባለው የፖለቲካ (ዕቃ ዕቃ) ጨዋታ ማላገጥ አልፈለጉም፡፡ … ለዚያም ነው አንጋፋውና ዝነኛው ዓለም አቀፉ The Washington Times ጋዜጣ ንጉሰ ነገሥቱ በታመሙበት ወቅት ‹‹Menelik of Abyssinia, The Most Democratic of All Monarchs ›› ብሎ የገለፃቸው!
‹‹ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም›› ሲሉ ደግሞ በሀገራቸው እንደማይደራደሩና ቆራጥ እንደነበሩ ያሳያል፡፡ ‹‹ወስልተህ የቀረህ›› ሲሉ ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች በዘመቻው የማይሳተፍ ሰው ምንም ቅጣት እንዳይደርስበት ዋስትና ሰጥተዋል፡፡
ወደ ዓድዋ ሲሄድ ምኒልክ ኑ ካለ፣
ኧረ አይቀርም በማርያም ስለማለ!
Filed in: Amharic