>

ኢህአዴግ - ኢህአዴግ ነው!!! (መሳይ መኮንን)

ኢህአዴግ – ኢህአዴግ ነው!!!
መሳይ መኮንን
የካቢኔ መዋቅሩ የሴቶችን ቁጥር መጨመሩ መልካም ነው። ሆኖም የአብይ አስተዳደር እንደህወሀት ዘመን ካቢኔ ከኮታ መላቀቅ አልቻለም። ሹመቱ በሜሪት(ብቃት) ላይ ያተኩራል የሚል እምነት ነበረኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ የፓርቲና የብሄር ኮታ ብቸኛው መስፈርት አይሆንም ብዬ ጠብቄ ነበር። ያው ነው። መለስ ዜናዊ እንዳለው ”ለሚኒስትር የፓርቲ ታማኝነት በቂ ነው። ሌላውን ከታች ባለሙያ ይሰራዋል።” ዶ/ር አብይ ይህን አዙሪት ይቀይረዋል የሚለው ግምት የእኔ ብቻ አልነበረም። ግምቱ ዛሬ ፈረሰ እንጂ።
የአብይ ካቢኔ የሴቶችን ቁጥር ከማሳደግ ያለፈ አዲስ ነገር የለውም። ገና ያልጠራ የውስጥ ፍትጊያ እንዳለ የሚያመለክት ነው። ዶ/ር አብይ በሀዋሳው ጉባዔ የኢህአዴግን ሙሉዕ የሆነ ስልጣን ይዘዋል። ይህ ያልተሸረፈ አቅም ካቢኔውን በብቃት ለማዋቀር እድል ይሰጣቸዋል የሚል ተስፋ ውስጤ ነበር።
ግን ኢህአዴግ – ኢህአዴግ ነው። ዶ/ር አብይ የፓርቲውን ሙሉ ድምጽ ቢያገኙም በፓርቲ መስመር እንጂ እንዳስለመዱን በራሳቸው የሚወስኑ አልሆኑም። የኮታው ነገር ቀጥሏል። ሁሉም በኮታ ደርሶታል። ብቃት ብዙም ቦታ እንዳልተሰጠው ከካቢኔው ስብስብ መረዳት ይቻላል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥሎ ጉልበት ያለው የሚኒስትር ቦታ ለወ/ሮ ሙፈሪያት መሰጠቱ አስገራሚ ነው። የሰላም ሚኒስትር ብዙዎቹን የጸጥታና ደህንነት ጉዳዮችን ጠቅልሎ የያዘ ነው።
አዲስ ነገር የለም። የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በካቢኔያቸው አዲስ ነገር አሳይተውናል። እነብ/ጄ ከማል ገልቹን ቁልፍ ቦታ የሰጡ ጊዜ ዶ/ር አብይም እንዲህ ዓይነት ከኢህ አዴግ ስብስብ ወጣ ያለ ሹመት ያሳዩናል ብለን ነበር። ለማንኛውም የአዲስ አበባ ወጣቶችን በዚህ ሳምንት ውስጥ ይፈታሉ የተባለው ቃል እንዳይቀለበስ ነቅተን እንጠብቅ!
Filed in: Amharic