>
4:42 pm - Friday January 18, 7061

" ለውጥን እየመራን ያለነው በህይወታችን ተወራርደን ነው!" (ጠ/ሚ አብይ አህመድ)

” ለውጥን እየመራን ያለነው በህይወታችን ተወራርደን ነው!”

 

ጠ/ሚ አብይ አህመድ

 

በወንጀል የተጠረጠሩ ባለሥልጣናት በመጪው ሣምንት ይፋ ይሆናሉ
· ህግን ማስከበር፤ ጡንቻን ከማሳየት ጋር አንድ አድርጎ ማየት ተገቢ አይገለም
· የታጠቀና የተቆጣ ወታደርን ስሜት አብርዶ መመለስ ትልቅ ፈተና ነበር
       

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከትናንት በስቲያ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች  ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው የምክር ቤቱ የመክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ  ባደረጉት ንግግር ላይ ተመስርቶ ከምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ የሰጡት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤የምክር ቤቱ አባላት የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማስቀጠል ከፍተኛ ስራ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ አሁን አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ከፍተኛ ጥንቃቄና እርጋታን የሚፈልግና የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ወቅት መሆኑን ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የሥርዓት አልበኝነት ዳፋ 

በተለያዩ አካባቢዎች ሁከት በመቀስቀስ የዘር ማጥፋት በፈፀሙ ወንጀለኞች ላይ የተወሰደ አስተማሪ እርምጃ ካለ እንዲገለፅና ህዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ ላይ ቦንብ በማፈንዳት በሰዎች ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙ ወንጀለኞች ጉዳይ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ ማድረግ ያልተቻለበት ምክንያት እንዲብራራ ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ቀርቧል፡፡

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለነዚህ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያም፣ በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙትን ሁከቶችና የደረሱትን ጉዳቶች ወደ ዘር ማጥፋት ወንጀል ሃሳብ ወስዶ በምክር ቤቱ መነሳቱ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው፣ የጉዳዩ አስከፊነትና አሳሳቢነት ግን ሃቅ ነው ብለዋል። ስርዓት አልበኝነት የወቅቱ የአገሪቱ ችግር ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ይህንን ችግር ለመፍታት መንግስት በ3 ደረጃ ከፍሎ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “ይህም ግጭትን ማስቆም፣ የግጭት ሁኔታ የሚታይባቸውን አካባቢዎች መከላከልና ዘላቂ ሰላም ማስፈን” ብለዋል፡፡

አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከፅንስ መቋረጥ ጋር ያመሳሰሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤”አንዲት ሴት ፅንስ መቋረጥ ሲያጋጥማት ደም መፍሰሱ አይቀርም፤ ሃኪሙ የፈሰሰውን ደም አይቶ በመደንገጥ ስራውን ቢያቋርጥ ሴትየዋ አደጋ ላይ ትወድቃለች፤ ደሙን እያየ ሆዷ ውስጥ ቀርቶ ያስጨነቃትን ፅንስ ሊያወጣላት ከጣረ ግን ህይወቷን ያተርፋል፤ የእኛም ጉዳይ እንዲሁ ነው፤ በሚፈጠሩ እንቅፋቶች ሳንደናቀፍ የጀመርነውን የለውጥ ሂደት ከዳር ማድረስ ይጠበቅብናል” ብለዋል፡፡

ህግን ማስከበር ጡንቻን ከማሳየት ጋር አንድ አድርጎ ማየቱ ተገቢ አለመሆኑን የገለፁት ዶ/ር ዐቢይ፤ ህዝብን በጉልበት መግዛት፣ ህግን በጡንቻ ማስከበር ቢቻል ኖሮ፣ ደርግ አይወድቅም ነበር ይላሉ፡፡ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ግን የኃይል እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነና ባለፉት ጥቂት ወራት ከ1700 በላይ ሰዎች ተይዘው ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉን አብራርተዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተያዙትን ወጣቶች አስመልክቶ ማብራሪያ ሲሰጡም፤ የተያዙት ወጣቶች ሁሉ ወንጀለኞች ናቸው፣ አጣርተን ነው ያሰርነው የሚል ትምክህት እንደሌላቸውና ዜጎች ባልተገባ ሁኔታ ሊታሰሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ጉዳዩን የማጣራት ሥራ ለመስራት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶች ተይዘው በታሰሩ ማግስት ከታሰሩት ወጣቶች መካከል በወንጀል ድርጊት ውስጥ ያልተሳተፉ ንፁሃን ዜጎች መኖራቸውን ሰምቼ፣ እስረኞቹን ከተያዙበት ቦታ አስመጥቼ አነጋግሬ ነበር ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ያለ አግባብ ለእስር የተዳረጉትን ወጣቶች በዛችው ቅፅበት ከእስር እንዲለቀቁና እንደነሱ ሁሉ ያለ አግባብ የታሰሩ ካሉም፣ እየጠቆሙ እንዲያስፈቱ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ ለውጡን እየመራን ያለነው በየቀኑ በህይወታችን ተወራርደን ነው ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ከአዲስ አበባ ወጣቶች መሃል ያለ አግባብ ለእስር የተዳረጉና የተቀጡ ወጣቶች ካሉ፣ የተቀበሉትን መከራ ለለውጡ እንደከፈሉት ዋጋ ሊያዩት ይገባል ብለዋል፡፡
ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ፣ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦንብ በማፈንዳት በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስና ህይወት እንዲጠፋ ያደረጉትን ወንጀለኞች ጉዳይ በማጣራት ለህዝብ ይፋ ማድረግ ያልተቻለበትን ምክንያት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያም፤ “የድርጊቱ ፈፃሚዎች ስልጡን ወንጀለኞች በመሆናቸው መረጃዎች እንዳይገኙ በማድረግ ተግባር የተካኑ ናቸው፤ እናም በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃዎችን የማሰባሰብና የማጥራት ጉዳይ ብዙ ስራ የሚፈልግ ነው፡፡ ህግ የማስከበሩ ጉዳይ በነቢብ እንደሚታወቀው ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡— የሆኖ ሆኖ በመጪው ሳምንት በወንጀል የተጠረጠሩ ባለሥልጣናት ለህዝብ ይፋ ይሆናሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

በታጠቁ ወታደሮች የለውጡ ሂደቱን ማደናቀፍ 

በቅርቡ የታጠቁ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ቤተ መንግስት በማምራት ያቀረቡት ጥያቄ እጅግ አደገኛ እንደነበር የተናገሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ዓላማው የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ማደናቀፍ እንደነበረም ገልፀዋል፡፡ ወደ ቤተ መንግስት ያመራውን የታጠቀና የተቆጣ ወታደር አብርዶ ለመመለስ ከፍተኛ ማስተዋልና ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ መውሰድ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ያንን በማድረግ ሊፈጠር ይችል የነበረውን ከፍተኛ ችግር ለማስቀረትና ከዚህ ጉዳይ ጀርባ ያሉትን ሰዎች ማንነት ለማወቅ ተችሏል ብለዋል፡፡

ወታደር ሲቆጣ እንዴት ቁጣውን ማብረድ እንደሚቻል፣ ሲፈራ ደግሞ እንዴት ማጀገን እንደሚቻል የራሱ ጥበብና ሳይንስ ያለው ጉዳይ ነው ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ ይህንኑ ሳይንስ በመጠቀም ተቆጥቶ የመጣውን ወታደር አብርዶ ራሱን እንዲገዛና ወደ ራሱ እንዲመለስ በማድረግ፣ ከመመለስም ባሻገር ከኋላ ሆኖ ያደራጀውንና ለዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ እንዲነሳ ያደረገውን አካል ማንነት እንዲናገር ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡ ከሰራዊቱ አባላት ጋር ፑሽአፕ መስራቴና በዛ ሁኔታ መቀራረቤ ያልተዋጠላቸው በርካታ ሰዎች ብዙ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ ፑሽአፕ ማሰራት አንዱ የቁጣ ማስተንፈሽያ ነው፤የተቆጣ ወታደርን እንዴት መያዝ እንዳለብን ስለምናውቅ አድርገነዋል። “ግን አሁን ያለው ጠ/ሚኒስትር ወታደር ባይሆንና ሲቪል ቢሆን ኖሮ፣ በዛች ዕለት ይደርስ የነበረውን ነገር ማሰቡ ከባድ ነው ብለዋል፡፡ እኔ ኢንተርቪው ስሰጥ በጣም የተዝናናሁ መስዬ ነው፤ ውስጤ ግን እርር ድብን እያለ፤ ህዝቡን አረጋግቼ፣ ህይወት መታደግ ደግሞ  የሰጣችሁኝ ሃላፊነት ነው” ሲሉም ተናግረዋል። ይህንን በማድረጋቸውም ህይወትን ከጥፋት መታደግ ከመቻላቸውም በላይ የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ፣ ለዚህ እንቅስቃሴ ያደራጃቸው ማን እንደሆነ፣ አንድም ጥይት ሳይተኮስ፣ እየተናገሩና መረጃ እየሰጡ ነው ብለዋል፡፡

አክቲቪስትነትና ጋዜጠኝነትን አለማደባለቅ

በአገሪቱ እያገጠመ ላለው የፀጥታ መደፍረስ፣ አንዳንድ የግል ሚዲያዎችና ማህበራዊ ሚዲያዎች በተለይም ፌስ ቡክ ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፣ እነዚህን ሚዲያዎች ከጥፋታቸው ለመቆጣጠር የታሰበ ጉዳይ አለ ወይ? በሚል የተጠየቁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የሚዲያ ነፃነቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው፣ የመንግስት ሚዲያዎች ከማህበራዊ ሚዲያውና ከግል ሚዲያው ባልተናነሰ ሁኔታ በርካታ ነገሮች አሉበት ብለዋል፡፡ የግል ሚዲያዎች እያልን የምንተቻቸው ሚዲያዎች ውስጥ ያሉ አንዳንድ ጋዜጠኞች፣ መንግስትን አቅጣጫ ሊያሳዩ የሚችሉ፣ በሚገባ ያነበቡና ራሳቸውን የገነቡ ናቸው፤ ከእነዚህ ጋዜጠኞች ጋር ለአንድ ሰዓት ያህል ማውራት ሊታመን የማይችል ዕውቀትና አቅም ለማግኘት ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል። ሚዲያዎች የሚያጠፉትን ጥፋት ብቻ ከማየት ጥፋታቸውን መግራትና ቀናውን መንገድ ማመላከት ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመንግስት የተቋቋሙ ሚዲያዎች የተደራጀ የገንዘብ አቅም ስለሚኖራቸው ስራቸውን ያለ ችግር ሊሰሩ ይችላሉ፤ የግሎቹ ግን ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረትም አለባቸው፤ እነዚህን በአቅም እንዲጎለብቱ ማገዙ ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ ባለሀብቶችም ማስታወቂያዎችንና አንዳንድ ድጋፎችን እንደ ኢቲቪና ፋና ባሉ የመንግስት ሚዲያዎች ላይ ብቻ ለማድረግ ከመሽቀዳደም፣ ወደ ግል ሚዲያዎች ፊታቸውን ቢያዞሩ በአቅም እንዲጎለብቱ ያግዟቸዋል፡፡ በዚህ መንገድም ሚዲያዎቹ ነፃ ሆነው ሙያዊ ሥነምግባራቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ ማድረግ ይቻላል፤ ብለዋል፡፡

ፌስ ቡክን በተመለከተም፤ ስማቸውና ማንነታቸውን ለማወቅ በማይቻልበት ሁኔታ አካውንት ከፍተው፣ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨትና ሁከት ለመፍጠር የሚሰሩ ከ100 የማያንሱ ደመወዝ እየተከፈላቸው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ በእነዚህ ግለሰቦች የሃሰት መረጃ እንዳይረበሽና የክፋት ሥራቸው ተባባሪ እንዳይሆን መክረዋል፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትችት የሚፅፉ አክቲቪስቶችም መኖራቸውን ጠቁመው፤ እነዚህ አክቲቪስቶች የምንሰራቸውን ስራዎች እየተከታተሉ የሚተቹ በመሆናቸው ያስፈልጉናል፡፡ ዋናው ነገር ግን አክቲቪስትነትና ጋዜጠኝነት ሊለያይና መስመር ሊበጅለት ይገባል፡፡ ጋዜጠኝት የራሱ ስርዓትና የሙያ ስነ ምግባር ያለው ሙያ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮ ሱዳን ድንበር ውዝግብ 

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ ሳይቋጭ በታሪክ እየተንከባለለ የመጣ ሲሆን አሁንም ለመልካም ጉርብትና ጠንቅ የሆነውን ችግር ለመፍታት እየተጠና ባለው የድንበር ማካለል ጥናት፣ የሁለቱን አገራት ጥቅም በማይጎዳና ህዝብን ባሳተፈ መንገድ የሚፈታ እንዲሆን ለማድረግ ምን እየተደረገ ነው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ጠ/ሚኒስትሩ ሲመልሱ፤ የድንበሩ ጉዳይ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ዝም ብለን ተነስተን የምንወስነው ጉዳይም አይደለም፤ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ እ.ኤ.አ በ1972 ዓ.ም የተደረገ ስምምነት አለ፡፡ ከዚህ ስምምነት ውጪ ያሉ ስምምነቶች ካሉ ተግባራዊ አይደረጉም፡፡ የድንበር ጉዳይ ከህዝቡ ጋር ተወያይተን የምንወስነው ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት በዚህ ማብራሪያቸው፣ ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን ያስረዱና ምላሽ የሰጡ ሲሆን ለቀጣዮቹ ሦስት ቀናት ከአዲሶቹ የካቢኔ አባላት ጋር በተቋም አወቃቀር ላይ የስልጠና ፕሮግራም እንዳላቸው ጠቁመው፤ የመረጧቸው የካቢኔ አባላትም የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በማስቀጠል ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአራተኛ አመት የስራ ዘመኑ፣ ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባው፣ ስልጣናቸውን በለቀቁት የቀድሞ አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ምትክ፣ አቶ ታደሰ ጫፎን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አድርጎ መርጧል፡፡ አዲስ አድማስ

Filed in: Amharic