>

 ታሪክን እንደባቡር፡- የዘመን ወጎች፤ ከዘመን ጉዞዎች!!  (አሰፋ ሀይሉ)

ጨዋታ አንድ፡- 
ታሪክን እንደባቡር፡- የዘመን ወጎች፤ ከዘመን ጉዞዎች!! 
አሰፋ ሀይሉ
ዘመን እንደ ትልቅ ባቡር ነው ይባላል – ባለብዙ ፉርጎ ባቡር፡፡ ሁላችንም በዚያ ባቡር በጊዜ ሂደት እንሣፈራለን፡፡ ያንድ ሃገር ሕዝቦች ታሪክ በተለያዩ ሃዲዶች ላይ እያሳበረ እንደሚጓዝ ባለረዥም ጉዞ፤ ባለብዙ ፉርጎ ባቡር ነው፡፡ ሁላችንም ባንዱ ፉርጎ ውስጥ ባንድላይ ባንገኝ በሌላው ውስጥ ግን አለን፡፡ ታሪካችን ቅጥልጥል ነው፡፡ የኛን ባቡር ከሌሎች የሚለየው የራሱ ጎዳና አቀበትና ቁልቁለት አለ፡፡ በተረፈ ሁሉም ሕዝብ የየራሱ የታሪክ ሂደትና ጉዞ.. በሂደት የተቀጠሉም የተቆረጡም ፉርጎዎች.. የተሣፈሩም፤ የወረዱም፤ ደግመው የተጫኑም ልዩ ልዩና ተመሣሣይ ተሣፋሪዎች አሉት፡፡ ያጋጣሚ ሆኖ.. ባንዱ ሃገር ለአብነት የሚጠቀን ታሪካዊ ጉዞ.. የሌላም ሃገር ሕዝቦች በሌላ ሃዲድ በመሠል ሁኔታ ተጉዘውበት መገኘቱ የተለመደ ነው፡፡ በያንዳንዱ የታሪክ ገጾችና ምዕራፎች እየተሳፈርን በቅጥልጥል ፉርጎዎች አብረን ስንጓዝ ያለፍን ሕዝቦች ነንና – እስቲ አንዳንዶቹን ያለፍንባቸውን  – ሌሎችም ያለፉትን – መንገዶችና ታሪኮች ለትውስታ ወደኋላ ዞር ብለን እንመልከት፡፡
ጨዋታ ሁለት፡- 
ካለፉ የታሪክ አሻራዎች.. እርስ-በርሥ መማማር??!!! ወይስ እርስ-በርሥ ጣት-መቀሣሰር??!!!
ምናልባት በሃገራችን ታሪክ እንደ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ያለ በሥራዎቹ ብዙዎችን ያነጋገረ መሪ ዳግም አናገኝ ይሆናል፡፡ በተለይ ብዙ የታሪክ ሂደቶችን አብረው የተጓዙትን የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦችን የሚመለከቱ ግንኙነቶችን፣ ፖለቲካዊ ምልከታዎችና ታሪካዊ ግንኙነቶችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሆነው በሚያቀነቅኑ ‹‹አንዳንድ›› ምሁራንና ፖለቲከኞች (አሊያም በደጋፊ-ነቃፊው) መካከልም ለከረሩ ክርክሮች መነሻ መሆናቸውም አይዘነጋም፡፡ ሆኖም ገና ለገና እሰጣገባዎች አሉ ስለተባለም ደግሞ.. ‹‹ህልም ተፈርቶ›› እንደሚባለው.. ከመሸሽ ይልቅ.. በትክክል የሆኑትን ነገሮችና መንስዔዎቹን ጭምር.. አነጋጋሪነታቸው ውጤቱ ማነጋገር ሆኖ… ፊት ለፊት እያነሱ መነጋገሩና መከራከሩ ጥቅሙ ያመዝናል ባዩ ብዙ ነው፡፡
የሆነ ሆኖ ሃገራችንና የሃገራችን ሕዝቦች (እንደማንኛውም ሌላ ሕዝብ ሁሉ) ካሳለፍናቸው ቀላል ያልሆኑ የታሪክ ጉዞዎች አንፃር በአዎንታዊም በአሉታዊም መልኩ የምናነሳቸው የታሪክ ምዕራፎች አሉ፡፡ ሊጠፉም አይችሉም፡፡ በዚህ በኩል በተለይ የአጤ ምኒልክ ስምና ሚና ከሁሉ ገዝፎ ለጨዋውም ላዋቂውም የሚታይ መሆኑ አይካድም፡፡ በአጤ ምኒልክ ላይ ከሚቀርቡባቸው ስሞታዎች መካከል በተለይም ‹‹ኦሮሞዎችን የወጉና ያስገበሩ አብይ ‹‹ነፍጠኛ›› ነበሩ›› የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ታሪክ መዝግቦ ያቆየው ሃቅስ… ምናልባት.. ከነዚህ መነሻ ያላቸውም የሌላቸውም ስሞታዎች ባሻገር የሚያሳየን ነገሮች ይኖሩ ይሆን?? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ መልሱም ቀላል ነው፡፡ አዎ፡፡ ብዙ ነገር ያለ ይመስላል፡፡
ጨዋታ ሦስት፡-
ሐረር – እምባቦ – ራስ መኮንን – አጤ ምኒልክ – ራስ ጎበና – ደጃች ገረሡ-ዱኪ – ንጉሥ ተክለሐይማኖት – አባ ወልደጊዮርጊስ – አጤ ዮሐንስ!!!
የምኒልክን የጦር ዘመቻዎች ተመልከት፡፡ ምኒልክ ወደ ሐረር ባደረጉት ዘመቻ እና ከዚያም በኋላ በሐረርጌ ምድር ግምባር ቀደሙ ገዢ ማን ነበሩ? ራሳቸው ከኦሮሞ ወገን የሚወለዱት የተፈሪ መኮንን (የቀ.ኃ.ሥ.) አባት ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ ናቸው፡፡ እምባቦ ተብሎ በሚታወቀው ከሸዋ አማራ ወገን የሆኑት ምኒልክ ከጎጃም አማራ ወገን ከሆኑት ተክለሐይማኖት ጋር ባደረጉት የእርስ-በርስ ጦርነት… በምኒልክ በኩል ከሁሉ በላይ ሥልጣን የነበራቸው፤ በጦሩም ላይ ተሾመው ወገናቸውንም አሠልፈው ጎጃሞችን ተዋግተው ድል ያደረጉት የምኒልክ የጦር አበጋዞች እነማን ነበሩ?? አሁንም ከኦሮሞ ወገን የሚወለዱት እነ ራስ ጎበና እና ደጃች ገረሱ ዱኪ ነበሩ፡፡
እና በቃ.. የእነ አፄ ምኒልክን አንዱ አማራ ከሌላ አማራ ጋር የሚዋጋበትን፤ ኦሮሞው ከኦሮሞ የሚዋጋበትን፣ ኦሮሞው ከአማራ ወገን ተሰልፎ ሌላውን አማራ የሚወጋበትን፤ ከትግራይ ወገን የሚወለዱት አፄ ዮሐንስ ብዙ እልቂት ያስከተለን የሁለት አማራ ሕዝቦች ጦርነት አርግበው በአስታራቂ ዳኝነት ገሥግሰው የሚዳኙበትን እና ሌሎች ሌሎች ብዙ መሰል የታሪክ ሃቆችን ስታይ… ብዙ ሥሞታዎች እና በብዛትም በአደናጋሪ መልኩ ሲተረኩ የሚታዩ የታሪክ አቀራረቦችና ድርሳኖች ምን ያህል ከእውነታው የራቁ አሊያም የቀረቡ መሆናቸውን መገምገም የትውልዶች ከባድ ኃላፊነት መሆኑን አበክረህ ትረዳለህ፡፡ በቀድሞ ነገስታትና ሕዝቦች መካከል ጦርነትም ፍቅርም ከነበረ.. ዘርን እየቆጠሩ የሚዋጉና የሚዋደዱ ሳይሆኑ.. በሐገር አስተዳደርና ግዛት፣ እንዲሁም ለየራሳቸው ስምና ህልም እንዲሁም የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑ.. ከምንም በላይ ሊዘከር የሚገባው እውነታ መሆኑንም ጭምር የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡ ፍርጥርጥ ያሉት የታሪክ ሃቆች በግላጭ ሲታዩ ዝርዝሮቹ ውስጥ ከነበሩ ክንዋኔዎች የምንረዳው ይህንኑ ነውና፡፡
ጨዋታ አራት፡- 
አጤ ምኒልክ እና የእምባቦ አብነት!!
‹አጤ ምኒልክ› በተሰኘው የዛሬ መቶ ሰባት ዓመት በአፈወርቅ ገብረየሱስ በሮማ በታተመ መጽሐፍ.. በታሪክ ‹‹የእምባቦ ጦርነት›› ተብሎ ስለሚታወቀው ጦርነት ተጽፎ የተገኘው ታሪክ ጉድ ያሰኛል፡፡ የእምባቦ ጦርነት በሸዋው ወጣት ንጉስ ምኒልክ እና በጎጃሙ አዛውንት ንጉስ ተክለሃይማኖት መካከል የተደረገ ጦርነት ነበር፡፡ ተክለሃይማኖት ‹‹በግላጭ ሜዳ እንገናኝና ይዋጣልን›› ብለው ለምኒልክ መልክተኞች መላካቸውን ተከትሎ… ወጣቱ ምኒልክ እነ ራስ ጎበናንና ገረሱ ዱኪን እነ ወሌ ብጡልን አስከትለው… አዛውንቱ ተክለሃይማኖትም እነ አባ ወልደጊዮርጊስና ደጃች ስዩምን አስከትለው… በግንቦት ወር 1874 ዓ.ም. አሰቃቂ የሚባል የወገን ጦርነት ተካሄደ… በጎጃሞች በኩል ከተሰለፉት… ከምኒልክም በኩል ከተሰለፉት… ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ጎበዛዝት… ባንድ ጀንበር ህይወታቸውን አጡ!! በእምባቦ ምኒልክ አሸነፉ፤ አፄ ዮሐንስም ‹‹ምን ሲደረግ!›› ብለው ከደብረታቦር ገስግሰው መጡ፤ ዳኝነትም ተቀመጡ፤ እርቀሰላምም ወረደ፡፡
/በነገራችን ላይ፡- ይህ እንግዲህ በጎጃምና ሸዋ መካከል የተካሄደ የከፋ ጦርነት ነው፡፡ ምኒልክ ታዲያ የወጉት ኦሮሞን ብቻ መርጠው ነውን?? ደግሞስ ጭራሽ እነገረሱ ዱኪና ራስ ጎበና ወይም ምኒልክ ያሰለፉት ከኦሮሞ ወገንም የተውጣጣ ታማኝ ጦር-ሠራዊታቸው ተባብረው በአማራ ወገን ላይ ሲዘምቱ ሲታይ – ለእርስ በርስ መጫረሳችን ከማዘን በቀር ምን ተብሎ ወይም በምን አይነት መልኩ ይሆን ይህ የሚነገረው???/
ጨዋታ አምስት፡-
የምኒልክ የዶሮ ላባዎች!!
የዶሮ ላባ – ቀድሞ ባገራችን ዘመናዊ ጥጥ ለህክምና አገልግሎት ሳይውል ጥቅም ላይ የዋለ ሃገር-በቀል መላ ይመስለኛል፡፡ ደግሞም ብናኝ ስለሌለውና ብናኙም በአካል ላይ ስለማይቀር እብስ እያደረገም እንደናት እጅ ስለሚያክክ የዶሮ ላባ ተመራጭነቱ የላቀ ነበር፡፡ ታዲያ የእምባቦ ጦርነት ሲታወስ… የእምባቦ ጦርነት አብቅቶ… ገላጋይ ከመድረሱ በፊትም ቢሆን… እምዬ ምኒልክ አሸናፊ ሆነው ሳለ… ለተዋጓቸው የጎጃሙ ንጉስ ተክለሐይማኖት ያሳዩት መልካምነት ሲታይ… በተለይ በሃሳባችን የምትመጣብን – በእውነት ተምሳሌተ-ክርስቶስ የሞላባት ቸር ድርጊት አለች – በዶሮ ላባ አምሳል ሆና የተገለጠች!!!!! ይህች የዶሮ ላባ የምኒልክን ሆደ-ሰፊነትና አርቆ አስተዋይነት ያለማወላወል ታሳየናለች፡፡
ስለዚሁ ከነርዕሱ በደጃች አፈወርቅ ገብረየሱስ መጽሃፍ የተዘከረው እንደወረደ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የምባቦ፡ ጦርነት፡፡ […] በግንቦት፡ ፲፰፻፸፬ [1874] ዓመተ፡ ምሕረት›› ይልና ስለዚሁ የሚከተለው ተጽፎ እናገኛለን፡፡
‹‹[…] ንጉሥ፡ ተክለ፡ ሃይማኖትም፡ ከዚያው፡ ላይ፡ ከብዙ፡ ስፍራ፡ ቆስለው፡ ተያዙ፡፡ ወዲያው፡ ተይዘው፡ ካጤ፡ ምኒልክ፡ ፊት፡ እንደ፡ ደረሱ፡ […] ይማሩኝ፡ ብሎ፡ ተግር፡ ወደቀ፡፡ አጤ፡ ምኒልክ፡ ግን፡ እንኳን፡ ቂም፡ ይይዙባቸው፡ አይዞህ፡ ምንም፡ አላደርግህ፡ ተነሥና፡ ሳመኝ፡ ብለው፡ ዝቅ፡ ብለው፡ ደግፈው፡ አንሥተው፡ ሁለቱ፡ ተሳሳሙ፡፡ አጤ፡ ምኒልክ፡ ንጉሥ፡ ተክለ፡ ሃይማኖትን፡ ከብዙ፡ ላይ፡ ቆስለው፡ ባዩ፡ ጊዜ፡ አዝነው፡ በንጉሥ፡ እጀዎ፡ እንደ፡ ወጌሳ፡ አረሩን፡ ፈልፍለው፡ አውጥተው፡ ቁስሉን፡ በዶሮ፡ ላባ፡ እያጠቡ፡ መድኃኒት፡ እያደረጉ፡ አዳኑ፡፡ […] የእምባቦ፡ ጦርነት፡ ነገር፡ ባጭሩ፡ አደረግሁት፡ እንጂ፡ ብዙ፡ ነበረ፡፡ ከድሉ፡ በኋላ፡ አጤ፡ ምኒልክና፡ ንጉሥ፡ ተክለ፡ ሃይማኖት፡ ሲጨዋወቱ፡- እውነቱን፡ ንገረኝ፡ እስቲ፡ አንተ፡ አሸንፈህ፡ ቢሆን፡ ኖሮ፡ ምን፡ ታደርገኝ፡ ኖሯል? ብለው በጨዋታ ቢጠይቋቸው፡- እውነቱን፡ ልናገረው፡ እኔ፡ ድል፡ አድርጌ፡ ቢሆን፡ ቶሎ፡ አስገድለዎ፡ ነበር፡ አሉ፡፡ ነገሩም፡ በሳቅ፡ ተከተተ፡፡››
(– አፈወርቅ፡ ገብረ፡ ኢየሱስ፡ ዘብሔረ፡ ዘጌ፡፡ ዳግማዊ፡ ምኒልክ፡ ንጉሠ፡ ነገሥት፡ ዘኢትዮጵያ፡፡ ከገጽ 32-37፡፡ በሽህ፡ ተ፱፻፩፡ [1901] ዓመተ፡ ምሕረት፡ ሮማ፡ ከተማ፡ ታተመ፡፡)
አንድዬ ከዳግም የርስ-በርስ ጭርርስና ፍጅት ይሰውረን፡፡ ሣንፈልገው ለሚመጣብን መቆሳሰል ደግሞ አንድዬ ፈፅሞ.. ፈፅሞ.. የዶሮ ላባዎችን አያሳጣን ማለትም ትልቅ ምርቃት ነው፡፡ ባሁን ጊዜ ያጣነው የዶሮ ላባን ተዓምር ነው!!!! ብዙ የዶሮ ላባዎች ያስፈልጉናል!!! መልካም የይቅርታና የእርቀ-ሠላም ጊዜ ለሁላችን ይሆንልን ዘንድ በረዥሙ ተመኘሁ፡፡ አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic