>
5:14 pm - Friday April 20, 5736

የጎሳ ፌዴሬሽንና የዋና ከተማ ውዝግብ !!! (አቻምየለህ ታምሩ)

የጎሳ ፌዴሬሽንና የዋና ከተማ ውዝግብ !!!
አቻምየለህ ታምሩ
አዲስ አበባን አስመልክቶ ዋልታ ቴሌቭዥን ያቀረበው   ጥያቄና አቶ ይልቃል ጌትነት የሰጠው  ያልተሟላ ምላሽ!
አቶ ይልቃል ጌትነት ከዋልታ  ቴሌቭዥን ጋር በነበረው ቆይታ በአዲስ አበባ ዙሪያ የቀረበለትን ጥያቄ ኮስተር ብሎ  ለመመለስ ሞክሯል። «የኦሮምያ ክልል ሕገ መንግሥት ፊንፊኔን የኦሮምያ ዋና ከተማ ያደርጋታል፤ እንዴት ታየዋለህ?» ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ግን በቂ መልስ የሰጠበት አልመሰለኝም።
ጠያቂው ጋዜጠኛ አዲስ አበባን «የኦሮምያ ክልል» ዋና ከተማ አድርጎ ያቀረበው  «የኦሮምያ ክልል» የሚባለውን ክልል  ሕገ መንግሥት በመጥቀስ ነው። ይልቃል ጌትነት ኦሮምያ የተባለው ክልል ሕገ መንግሥት ተጠቅሶ የቀረበለትን ጥያቄ   ገዢውን የፌዴራል  መንግሥቱን «ሕገ መንግሥት» አንቀጽ  49(5) እና አንቀጽ 9  ጠቅሶ አዲስ አበባ የኦሮምያ ዋና ከተማ ናት የሚለውን የኦሮምያ ክልል ሕገ መንግሥት ድንጋጌ  ውድቅ ማድረግ ይችል ነበር።
አምስቱ የነ ኦቦ በቀለ ገርባ ድርጅቶች ካላስከበርነው ሞተን እንገኛለን የሚሉት የፌድራሉ  ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49(5) አዲስ አበባ  በኦሮሚያ ክልል መሀል እንደሚገኝ እንጂ የኦሮምያ አካልና ዋና ከተማ ናት አይልም።
 ከዚህ በተጨማሪ እነ ኦቦ በቀለ  ሌሎችን አክብሩት  እያሉ የሚመኩበት ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9  እንዲህ ይላል፤ «ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው። ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም»!  ይህ ማለት በሕገ መንግሥቱ መሰረት  አዲስ አበባን ኦሮምያ የሚባለው ክልል  ዋና ከተማ ያደረገው  «የኦሮምያ ክልል ሕገ መንግሥት»
የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕገ ከሆነው ከሕገ መንግሥቱ ጋር   ስለሚቃረን ተፈጻሚነት የለውም  ማለት ነው።
ስለዚህ ጠያቂው ጋዜጠኛ  «የኦሮምያ ክልል ሕገ መንግሥት ፊንፊኔን የኦሮምያ ዋና ከተማ ያደርጋታል፤ እንዴት ታየዋለህ?»ሲል ያቀረበው ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ስላለበት የኦሮምያ ክልል ባለሥልጣናትንና እነ ኦቦ በቀለ ገርባን ሕገ መንግሥት ጥሳችኋል ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል!
ባጭሩ  ኦሮምያ ክልል የሚባለው ክልል ሕገ መንግሥት አዲስ አበባን የኦሮምያ ክልል ዋና ከተማ ማድረጉ እነ በቀለ  ገርባ እንዲከበር ዘብ የቆሙልትን  ሕገ መንግሥት ስለሚቃረንና  ኢሕገመንግሥታዊ ስለሆነ  አዲስ አበባን የኦሮምያ ዋና ከተማ ያደረገው የኦሮምያ ክልል ሕገ መንግሥት ባስቸኳይ  መታረም ይኖርበታል። ሕገ መንግሥቱ ይከበር ብለው መግለጫ ያወጡት እነ ኦቦ በቀለም አዲስ አበባን የኦሮምያ ክልል ዋና ከተማ በማድረግ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነውን ሕገ መንግሥቱን የጣሰው የኦሮምያ ክልል ሕገ መንግሥት ባስቸኳይ እንዲስተካከል መግለጫ ማውጣት ይኖርባቸዋል።
በነገራችን ላይ ይኽንን የጎሳ ፌዴሬሽንና የዋና ከተማ ውዝግብ ያማከሩት ቤልጅየሞች ናቸው። በሽግግር መንግሥት ምስረታ ወቅት ከወያኔ መሪወች ጋር ከፍተኛ ግንኙነት የነበራቸው በተለይም የቤልጅየም ደች ተናጋሪ ምሁራን ነበሩ። ከነሱም ውስጥ ሬንቸትስ የተባለ የአፍሪካ የሕግ ባለሙያ የሚባል የዩኒቨርስቲ አስተማሪ አንዱ ሲሆን አዲስ አበባ በመመላለስ የሕገመንግሥቱን ረቂቅ ሲያማክር ነበር።
ቤልጅየም በሶስት ቋንቋ የተከፈሉ እርስበርስ ስምምነት የሌላቸው ክልሎች ያሉባት (ደች፣ ፈረንሳይኛና ጀርመንኛ) ትንሽ አገር ነች። በተለይም እነዚህ የወያኔ ወዳጅ የሆኑት ደች ተናጋሪወች ፈረንሳይኛ ተናጋሪወች ሲጨቁኑን ነበር ነፃ መውጣት አለብን በማለት ንቅናቄ ጀምረው ነው አገሪቱን ለዚህ አይነት ሥርዓት ያበቋት። ለፈረንሳይኛ ተናጋሪወቹ ያላቸው ጥላቻ ወሰን የለውም። የሚገርመው የወያኔን የአማራ ጭቆና ትርክት ተከትለው የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚረዱትም በዚያው በተንሸዋረረ መንገድ ነው። ለትግሬወቹ የሚያሳዩት አድላዊ ውገና ይገርማል። ስኮላርሽፕ እየሰጡ በዩኒቨርስቲወቻቸው የሚያመጧቸው አብዛኛወቹ ትግሬወች ናቸው። ትግራይ ውስጥ በብዙ ፕሮጀክቶች ይሳተፋሉ። እንደሚታወቀው መለስ ሲታከም የነበረውና በመጨረሻም ያሸለበው በነሱ የዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ነው።
እነዚህ ደች/ፍሌሚሽ ተናጋሪወች እንቅስቃሴያቸው ሁሉ የመገንጠል ፕሮጀክት ነው። ግን ተገንጥለው ሌላ ሚጢጢ አገር ለመፍጠር ያዳገታቸው የዋና ከተማዋ የብራስልስ ጉዳይ ብቻ ነው። የአውሮፓ አንድነት ዋና ከተማ የሆነችውን ብራስልስን ጥለው መገንጠል አይፈልጉም። ብራስልስ የኛ መሬት ነው ይላሉ። ሕዝቡ ግን ከዘጠና ፐርሰንት በላይ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ስለሆነ አይፈልጋቸውም። እነሱም ሰወቻቸውን በማስፈር ዴሞግራፊውን ለመለወጥ፣ የመንገድና የሰፈር ስሞች በደች ቋንቋም እንዲፃፍ በመታገል ወዘተ ባጠቃላይ እየተወዛገቡ መንግሥቱን የጎሳ ሽኩቻና ጭቅጭቅ ማዕከል አድርገውት ይገኛሉ።

Filed in: Amharic