>
5:31 pm - Thursday November 13, 7670

ከፓርቲ ሴቶች አልፎ…. 50 ሚሊዮን የሀገራችን ሴቶች ጾታዊና ኢኮኖሚያዊ እኩልነትም ይረጋገጥ ?!!!  (አሰፋ ሀይሉ)

ከፓርቲ ሴቶች አልፎ…. 50 ሚሊዮን የሀገራችን ሴቶች ጾታዊና ኢኮኖሚያዊ እኩልነትም ይረጋገጥ ?!!! 
አሰፋ ሀይሉ
 
 
* የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆኑ የሚገቡት – ከእነዚህ ዘመናዊ ሴቶች በቅርብ ኪሎሜትሮች ርቀት በመከራ አዘቅት ውስጥ ተከበው ኑሮአቸውን እየገፉ ያሉት – በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት የሀገሪቱ ምስኪን የገጠርና የከተማ ሴቶች ናቸው!!!
ላለፉት 27 ዓመታት በተለያየ አምሳል ኢትዮጵያን ሲገዛ የቆየው ገዢ ፓርቲ የኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ውጤት መሆኑን የሚናገረው የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግሥት በሥልጣን ባለቤትነት በኩል የሴቶችን ጾታዊ እኩልነት በማስጠበቅ በአፍሪካ ተስተካካይ የተገኘለት አይመስልም፡፡
የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግሥት ከሚኒስትሮቹ ግማሹን ሴቶች በማድረግ ጀመረ፣ አሁን ደግሞ የሀገሪቱን ፕሬዚደንት (ወይም ርዕሰ-ብሔር) ጾታ ከዘመነ ዘውዲቱ በመቀጠል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሴት ጾታ ቀይሮታል፡፡ በእርግጥ ይህ በራሱ ድንቅ ተሰኝቶ ሊበረታታ የሚገባ ድርጊት ሊሆን ይችላል፡፡
ነገር ግን እንኳን በዛሬ ዘመን ይቅርና ያኔ ሴቶች በእኩልነት በማይታዩበት ዘመን እንኳ ሃገራችን ብዙ በፖለቲካው ቁልፍ ሚና የተጫወቱ፣ በሥራቸው ስመ-ጥር ሆነው እስከዛሬም በአንቱታ የሚጠቀሱ ብዙ የሴት ከዋክብትን ያስተናገደች ሃገር ናት – ሀገራችን ኢትዮጵያ፡፡ ከንግሥተ ሣባ እስከ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ድረስ በሴቶች የመመራት ታሪክ ላላት ኢትዮጵያ ሀገራችን ይሄ የአሁኑ የሴት መሪ በመንግሥት መንበረ ሥልጣን ላይ ከፍ ብሎ መታየት አዲስ ክስተት አይደለም፡፡
ሀሳቤን ለማጠቃለል ያህል በሀገራችን ድሮም ሆነ ዘንድሮ በአኗኗርና በትምህርት ደረጃ፣ በሙያና ማህበራዊ ግልጋሎታቸው፣ በበጎ አድራጎታቸው፣ በአርበኝነታቸው ከወንዶች ሁሉ በላይ ልቀው፣ ለትውልድ ታላቅ ሰብዕናን ተክለው ያለፉ በርካታ ሴቶች ኢትዮጵያውያት ድሮም ነበሩ፣ ዘንድሮም አሉ፣ ወደፊትም እንደሚኖሩ አይጠረጠርም፡፡
ነገር ግን ከዚህ ሴቶችን የአመራር ተሣትፎ ከፍ የማድረግ በጎ ሥራ ጎን ለጎን ግን – የሴቶችን ፆታዊ እኩልነት ለማስጠበቅ ቆርጦ የተነሣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መንግሥት – ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን የሚገባው – በመንግሥት የፖለቲካና ኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ ያሉ ሴቶችን – አሁን ባላቸው ሥልጣን ላይ – ወደ ተጨማሪ  ከፍ ወዳለ የሥልጣን ማማ ላይ ማውጣት ብቻ አይደለም፡፡
ከእነ ወ/ሮ ፈትለወርቅ(ማንጆሩ) እና ከእነ ወ/ሮ ሣህለወርቅ የሥልጣን ፆታዊ እኩልነት በላይ..
ይልቁንም – የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆኑ የሚገቡት – ከእነዚህ ዘመናዊ ሴቶች በቅርብ ኪሎሜትሮች ርቀት በመከራ አዘቅት ውስጥ ተከበው ኑሮአቸውን እየገፉ ያሉት – በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት የሀገሪቱ ምስኪን የገጠርና የከተማ ሴቶች ናቸው፡፡ ዛሬ እዚህ አዲስ አበባ ላይ መኪናቸውን እያሽከረከሩ በነፃነት ከሚያማልሉን ሴቶች ይልቅ፣ ከመዲናይቱ በጥቂት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ሆነው – በመዓት ህጻናት ተከበው፣ የኑሮን ጫና ተሸክመው፣ ባዘመመች ደሳሳ ጎጆ ውስጥ የሚኖሩት ሴቶች ናቸው – የመንግሥት ዋነኛ የሴቶች እኩልነት ትኩረት መሆን ያለባቸው፡፡
እነዚህ በሀገሪቱ በስምንቱም አቅጣጫ ቢኬድ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ በእናትነታቸው፣ በሙያቸው፣ በስነምግባራቸው፣ በሁለነገራቸው ቀጥ አድርገው ያቆሙ ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን እናቶች እኩልነት፣ ነጻነት፣ የሀብትና የዕድል እኩል ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው – ሀገሪቱ የሴቶች እኩልነትን ልታረጋግጥ የምትችለው፡፡
እነዚህን የሀገሪቱን ከባድ የኑሮ ሸክም በሁለመናቸው ያዘሉ ስማቸው በአደባባይ የማይጠራላቸው ኢትዮጵያውያት እናቶችና እህቶቻችን የፆታ እኩልነት ጉዳይ – ከእነ ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ ሹማምንት ከእነ ወይዘሮ ሞንጆሪኖ (ወ/ሮ ፈትለወርቅ) እና ከእነ ወ/ሮ ሣህለወርቅ የፆታዊ ሥልጣን እኩልነት በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያሳስበው ጉዳይ ነው፡፡
ዛሬ በ“ጥልቅ ተሃድሶ”አቸው ማግሥት በኢህአዴግ የፓርቲ ፖለቲካ ተዋንያን አማካይነት በፓርቲዎችና በመንግሥት የሥልጣን መዋቅር ውስጥ በተዘረጉት የሥልጣን እርከኖች ላይ እየተደረገ ባለው የሥልጣን ክፍፍል የሴቶችን ጾታዊ እኩልነት የማስጠበቁ ጉዳይ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ “ይስጣቸው፣ ያድርግላቸው፣ ይበልላቸው!” የሚያሰኝ ዜና ከመሆን ያለፈ ብዙም መሬት ላይ የወረደ ፋይዳ የሚያመጣ ነው ብሎ መውሰድ በበኩሌ ይከብደኛል፡፡
በቁጥር የሀገሪቱን ሕዝብ ግማሸ በላይ ለሚሆኑትና፣ ከድህነት ወለል በታች የሆነ ኋላቀር ኑሮን እየገፉ ለሚገኙት፣ የያዳንዱን ምስኪን ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ምሰሶና ማገር ሆነው በየጎጆው ሥር ለሚኖሩ፣ ለእነዚያ 50 ሚልዮን ፅኑ እና መከረኛ ኢትዮጵያውያት ሴቶች ግን ይሄ የኢህአዴግ ሴቶች መሿሿም ጠብ የሚያደርግላቸው ነገር እምብዛም ነው፡፡
ነገር ግን የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ በነካ እጁ…. ወደእነዚህ ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያት እናቶችና እህቶች ቢዞር ግን … በሀገሪቱ ላይ የሚታየው ለውጥ ተጨባጭ እና ታላቅን ለውጥ የሚያመጣ መሆኑ ምንም አጠያያቂነት የለውም፡፡ እና … ባጭሩ…. የመንግሥት ትኩረት ከራሱ ፓርቲ ሴቶች አልፎ…. ለ50 ሚሊየኑ የሀገራችን ሴቶች ጾታዊና ኢኮኖሚያዊ እኩልነት መረጋገጥም ቢሆን…?!!!
ለክቡር ኢትዮጵያዊት ተሿሚ ፕሬዚደንት ወ/ሮ ሣህለወርቅ ዘውዴ መልካም የሥልጣን ዘመንን ተመኘን፡፡ ለመላው ኢትዮጵያውያን ሴቶችም አንድ ቀን የከበደ ሸክማቸው የሚቀልበትን ደግ ዘመን ተመኘን፡፡
አምላክ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን አብዝቶ ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ 
Filed in: Amharic