መሳይ መኮንን
አፋሮችና ጋምቤላዎች የመንግስት ያለህ ጩሀት ማሰማት ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል። በዶ/ር አብይ አህመድ የተጀመረው የለውጥ ሂደት እኛ ዘንድ አልደረሰም የሚለው የህዝብ ድምጽ በተለይ ከአፋርና ከጋምቤላ ያለማቋረጥ ይሰማ ነበር። የለውጥ ሽታ ይድረሰን፡ አመራሮቹ ከህወህት እቅፍ አልወጡም፡ ለሌላው ኢትዮጵያዊ የደረሰው ተስፋ ለእኛ ለምን ይነፈገናል የሚለው መልዕክት ለአራት ኪሎው ቤተመንግስት ምነው ራቀ አሰኝቶ ነበር የሰነበተው። በሁለቱ ክልሎች ህዝቡ ላለፉት አራት ወራት በተቃውሞ ቆይቷል።
በእርግጥ በሁለቱ ክልሎች የህወሀት እጅ አልተቆረጠም። ህወሀት ማዕከላዊ መንግስቱን ከተነጠቀ በኋላ ጓዙን ጠቅልሎ መቀሌ ቢገባም በአራቱ ታዳጊና ወደኋላ የቀሩ ክልሎች ላይ የበላይነቱን የሚነጥቀው አልነበረም። መቀሌ ከዮሀንስ ቤተመንግስት ተቀምጦ የጥፋት ተልዕኮውን ያለአንዳች ከልካይ ማስፈጸም የቀጠለባቸው በተለይ በአራቱ ክልሎች ነው። በሶማሌ፡ በአፋር፡ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል።
በሌሎች ክልሎች አንጻራዊ በሆነ መልኩ የለውጥ ሂደት ተጀምሯል። የህወሀት የበላይነትን ቀብረዋል። በሌሎች አዳዲስ ከለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ቢከሰቱም የ27 ዓመቱ የህወሀት ዘረኛ አገዛዝ ከነሰንኮፉ ተነቅሎላቸዋል። በአራቱ ክልሎች ግን ህወሀት አልሞተም ነበር። ከነመርዙ እየተናደፈ ቀጥሏል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ላይ ከሚቀርቡ ወቀሳዎች አንዱ በእነዚህም ክልሎች ላይ ምነው አቅም አጡ የሚል ነበር።
አብዲ ዒሌ የሶማሌ ህዝብ ከለውጡ ጋ እንዳይገናኝ እንቅፋት ሆኖ ለአራት ወራት ተንገታገተ። የሶማሌ ኢትዮጵያዊው ለሁለት ወራት ሲተናነቅ፡ እስከአዲስ አበባ የተዘረጋ ተቃውሞ ሲያሰማ ቆየ። ቢዘገይም መልስ ማግኘቱ አልቀረም። የጠ/ሚር አብይ አስተዳደር በብልሃትና ጥበብ የህወሀትን እጅ በመቁረጥ፡ አብዲ ዒሌን እጆቹ በሰንሰለት ታስረው ወደ ከርቸሌ እንዲገባ አደረገው። የሶማሌ ክልል ህዝብ እፎይ አለ። አዲሱ የክልሉ ፕሬዝዳንት ከዘር ቆጠራ ወጥተው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አመራር ከጀመሩ ሁለተኛ ወራቸውን ይዘዋል።አሁን ጂጂጋ ላይ ” ሶማሌነቴ ከኢትዮጵያዊነቴ ጋር አይጋጭብኝም” የሚል አመራር ተቀምጧል።
የእኛም ጩሀት የነበረው ጠ/ሚር አብይ እንደሶማሌ ክልል ሁሉ ለአፋሮች እሮሮና ከጋምቤላ ለሚሰማው የድረሱልን ጥሪ መልስ እንዲሰጥ ነበር። ያልተረጋጋ አስተዳደር፡ ሙሉ በሙሉ ስልጣኑን ያልጨበጠ አመራር፡ በሽግግር ላይ ያለ ስርዓት መሆኑ ባይጠፋንም ባለች ውሱን አቅምም ቢሆን የሆነ መፍትሔ እንዲፈለግ ከአፋሮችና ጋምቤላዎች ጋር አብረን ስንጮህ ቆይተናል። ህወሀት ከጂጂጋ እጁ ሲቆረጥ አፋር፡ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ላይ ግን ስር ይዞ ቀጥሏል። የእነዚህ ክልሎችን አመራሮች በመቆጣጠር ከመቀሌ በሪሞት ኮንትሮል እንዳሻው መጠምዘዙን አላቆመም። ሀብትና መሬታቸው ላይ ተቀምጦ መቦጥቦጡን የሚያስጥለው ሊገኝ አልቻለም ነበር። የህዝብ ተቃውሞ ሳይቋረጥ እየተሰማ ነው። ዶ/ር አብይ ከወዴት አሉ?
ትላንት ስለሁለቱ ክልሎች የሰማነው ተስፋ የሚሰጥ ነገር ነው። ይዘገያል እንጂ አይቀርም። ጋምቤላ ላይ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረው፡ ለውጡን ሲያደናቅፍ የሰነበተው፡ ከህወሀት እቅፍ መውጣት ያልቻለው የጋትሉዋክ ቱት አመራር ከስልጣን መልቀቁ ተነገር። ጠ/ሚር አብይ አህመድ በተገኙበት በአዲስ አበባ በተደረገ ግምገማ የጋት ሉዋክ አመራር በገዛ ፍቃዱ ስልጣን መልቀቁ ታውቋል። ለጋምቤላዎች ትልቅ ዜና ነው። ጩሀታቸው ተሰምቷል። ዘግይቶም ቢሆን መልስ አግኝቷል። ህወሀት በጋምቤላም እጁ ይቆረጥ ዘንድ ውሳኔ አግኝቷል።
በአፋርም ሂደቱ ተጀምሯል። የክልሉ ገዢ ፓርቲ ለሁለት ተሰንጥቋል። ለውጡን የሚደግፉ ሃይሎች ዝምታውን ሰብረዋል። የአቶ ስዩም አወል አመራር ክሀወህት ጋር መቆየትን በመምረጥ ለውጥ በጠየቁ የፓርቲው አመራሮች ላይ እገዳ አስተላልፈዋል። የአፋር ህዝብ ከለውጥ ፈላጊ አመራሮች ጎን በመሆኑ የአቶ ስዩም እገዳ ዋጋ እንደማይኖረው ይታመናል። ከመቀሌ ትዕዛዝ እየተቀበሉ አፋርን የሚመሩት አቶ ስዩም የመጨረሻ ሙከራቸውን ለማድረግ ከህወሀት ጋር እየመከሩ እንዳለ ይሰማል። የዶ/ር አብይ መንግስት በብልሃት የህወሀትን እጅ ከአፋር ላይ ለመቁረጥ መንገዱን ተያዞታል። በቅርቡ የለውጥ እንቅፋት የሆነው የአቶ ስዩም አወል አመራር እንደጋትሉዋክ ቱት በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን ይለቃል አልያም እንደአብዲ ዒሌ መጨረሻው ከርቸሌ ሆኖ ያበቃለታል።
ሁሉም በጊዜው መሆኑ አይቀርም። ጂጂጋ፡ ጋምቤላና ሰመራ ላይ አቅሙን ያሳየው የጠ/ሚር አብይ መንግስት መቀሌ ላይም እንደሚመሰከር እንጠብቃለን። ጠ/ሚር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው ሳምንታት ቀደም ብሎ ለውጡ አይቀሬ መሆኑን የተረዱት ህወሀቶች በድብቅ ባደረጉት ስብሰባ፡ አዲስ አበባን ብንነጠቅ፡ ትግራይን ግን አናስነካም፡ የሚል አቋም ላይ ደርሰው ተማምለው ነበር። ባለፉት ስድስት ወራት መሀላቸውን ጠብቀው ቆይተዋል። ሆኖ ትግራይን ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ለይተው ለብቻቸው እንደዘመነ መሳፍንት ሊያቆዩ አይችሉም። በሂደት የመቀሌውንም ቁልፍ ይነጠቃሉ። የጠ/ሚር አብይ አህመድ የብልሃት አካሄድ ጊዜ ሊወስድ ይችል ይሆናል እንጂ መቀሌም የለውጡ ሂደት አካል መሆኗ አይቀርም።