>
3:49 pm - Sunday August 7, 2022

ጀሮ ያለው ይስማ የመጀመሪያውን መጨረሻ ደወል (መንገሻ ዘውዱ ተፈራ)

 

ጀሮ ያለው ይስማ የመጀመሪያውን መጨረሻ ደወል

 

መንገሻ ዘውዱ ተፈራ

 

አባቶች ጠንካራ ምክራቸውን ሲያስተላልፉ “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነህ ብለው ይወረውሩሃል“ ይላሉ። ዛሬ በ18/02/2011 የኢትዮጵያን ህዝብ አፍኖና ደቁሶ የገዛውን የህወሀት ዘረኛ፣አፋኝ፣ገዳይና፣ወራሪ ቡድን ለማስወገድ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ሰለማዊ ሰልፍ ተካሂዶአል። የሰልፉ ዓላማ አሁንም የበላይነቱ የሚታየውን ህወሃት ለመሽከም ያልቻለው የአማራ ክልል ህዝብ ሳይወድ በግድ ሊገባበት ወደ አልፈለገው የትግል አማራጮች ለመግባት መገደዱን በዚህ የመጨረሻ የሆነው ሰላማዊ ሰልፍ በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት አካላት ለማሳወቅ ነው።  

ምንም እንኳን ትግሉ ህወሀት ከተመሰረተበት ከ1967 ዓ/ም በወጣ ገባ እየተካሄደ ቢኖርም ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ ግን  በሐገር ውስጥና በወጭ አንዲሁም በስልጣን ላይ በነበሩ መላው ኢትዮጵያዊያን በተደረገው ወሳኝ ትግል ህወሀት ተወግዶአል በሚል አምነት ለለውጡ መቀጠል የየድርሻችን እያበረከትን ነበር። ነገር ግን ህወሀት አሁንም አለባበሱን በመቀየር በሌላ ካባ ተሸፍኖ የተመሰረተበትን በተለይ የአማራን ዘር ማጥፋት ህልም በአዲስ ዙር የማሳደድና የዘር ማጥፋት ዘመቻ እያከናወነ ይገኛል። አማራን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያዊያን ተካሂዶ የነበረው ትግል ግን ቢቻል ሙለ ለውጥ ካልተቻለ ደግሞ ቢያንስ የህወሀትን የበላይነት ወሳኝነትና ገዥነት ያጠፋ አስተዳደር ለማግኘት ነበር።

ነገር ግን አሁንም የህወሃት ወሳኝነት ሰለመኖሩ ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል እንደሚባለው ዘር ማጥፋቱ ማሳደዱ ሲነቃበት ለምን ይህን አነሳችሁ ይቅርታ ጠይቁኝ፤በፌደሬሽን ምክር ቤት ስም የተቀመጡት የህወሀት ተወካይ ወ/ሮ ኬሪያ ጥያቄ አልቀረበልንም ጥያቄም ካለ መቅረብ ያለበት ለትግራይ ክልል መንግሥት ነው ብለው የሰጡትን የንቀት መልሳቸው። ሌላኛው የራያ ተወላጅ እራሳቸውን ለጥቅም መሸጥ አልበቃቸው በሎ ታላቅና ከቡሩን የራያ ህዝብ የትግሬ ነው ብለው ምስክርነት ከመስጠት በተጨማሪ አማራና ኦሮሚያ የሚባል ክልል አልነበረም እኛ ህወሀተቶች የፈጠረንው ነው ብለው መልስ መስጠታቸው ሁሉ የሚያስረዳው የበላይነታቸው ለመኖሩ የሚያጠራጥር ሆኖ አይታይም።

አሁን ደግሞ በአስፈፃሚያቸው ኢህአድግ ህዝብን እንደ አላዋቂ የመቁጠርና በተለመደ ቃላቸውና ተግባራቸው ተገናኝቶ በማያወቀው የማጭበርበሪያ ባህላቸው ይህን ተነሳሽነትና ሰሜት አበርዶ ጊዜ ለመግዛት የወልቃይት ጠገዴና ራያ ጥያቄ በህግ ይፈታል የሚል ማለዘቢያ ይዘው ብቅ ብለዋል።

በአጠቃላይ ኢህአድግ በተለይ ከአዴፓ የአማራ ህዝብ የሚጠበቀው አማራን አንወክልሃለን ካሉ ጠጋ ብሎ አበሮ መርቶ ማታገልና መታገል አንወክልህም ካላችሁና ህወሀትን ከፈራችሁ ደግሞ ከመሃል መውጣት አንጅ አሁንም አንደተለመደው 27 ዓመታት አንደመጣንበት እያጭበረበርን እንቀጥላልን ብሎ ማሰብ ቱኒዚያና ግብፅ ትልቅ ምሳሌዎች ናቸው።

ስለዚህ ይህን ጊዜ የማይሰጥ ከፊት ለፊት አፍጦ ለመጣ ጥያቄ የሚጠበቀው መልስ፦

  1. ከዘር ማጥፋት ግድያ ጋር ለተያያዘው የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ራያና መተከል በእውነት በህግ ይፈታል የሚል አስተዳደራዊ ውሳኔ ካለ ከህዝብ ወኪሎች እንዲሁም ከአማራና ትግራይ ክልል ገለልተኛ ወገኖች የተገኙበትና የተስማሙበት የፌደራል የሰላምና ፀጥታ አስከባሪዎች በመመደብ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሰርተው የሚኖሩበት አከባቢና ሁኔታ መፍጠር በሂደትም አነዚህን ቦታዎች ለባለቤቱ አማራ ክልል መልቀቅ።
  2. ከተፈጠሮ ሀብት (ጣና፣ ጭስ ዓባይ) እና የቅረስ ሀብቶች (ላሊበላ፣ፋሲል ግንብና ሌሌችም) በሐገሪቱ በችግር ላይ ላሉ ሀብቶች ለማስጠበቅ ለማቆየትና ተጠቃሚ ለመሆን ከሁሉ ቅድሚያ የችግራቸው መነሻ በባለሙያ ባለመመራታቸው ስለሆነ በዚህ ዙሪያ አንዳይቀርቡ ተከልክለው በሐገር ውስጥና በውጭ ያሉ ባለሙያዎችንና በጡረታ ተገልለው ለሚገኙትም ጥሪ በማድረግ ከአደራጃጀት ጀምሮ መፍትሔ ሃሳቦች አንዲቀርቡና ወደ ተግባር በመግባት የመታደግ ስራውን በቀናት ውስጥ ማስጀመር ናቸው።

አለበለዚያ ግን አቅምን መሰረት ያላደረግ የተለመደውን የቃል ሽንገላ መልስ ለመስጠት መሞከር ጀሮ ያለው ይስማን አለመስማትና የመጀመሪያውን መጨረሻ ደወል ነክቶ አደጋ መጥራት መሆኑን መረዳት ይጠይቃል።

 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር

 

Filed in: Amharic