>
3:12 pm - Tuesday July 5, 2022

ፕሬዝዳንት ሙስጠፋ ሙሁመድ ኡመር ማን ናቸው?  (የመጨረሻ ክፍል)

ፕሬዝዳንት ሙስጠፋ ሙሁመድ ኡመር ማን ናቸው?  (የመጨረሻ ክፍል)
በሙክታሮቪች ኡስማኖቭ
አቶ ሙስጠፋ ኡመር በሶማሌ ክልል ፖለቲካ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሙት እሙን ነው። የሶማሌ ህዝብን ያለ ገጭጓ ፈሰስ ባለ ቅንጡ መንገድ አይነት ለመምራት መዘጋጀት ከባድ ነው። ሶማሌ ከውጭ ለሚመለከተው አንድ ቋንቋ አንድ ሃይማኖት ይኑረው እንጂ ይህ የአርብቶ አደርነት የኑሮ ጣጣ በሚያመጣበት የተፈጥሮ ሁኔታዎች እና በውስጥም ማህበረሰባዊ መዋቅሩ በተለያዩ ጎሳዎችና ንዑስ ጎሳዎች የተከፋፈለ በመሆኑ ወደ ፖለቲካና አስተዳደር ሲመጣ የተለያዩ ልዩነቶች ይንፀባረቃሉ። (በዚህ አርእስት ላይ ሌላ ጊዜ እመለሳለሁ፣ ኢትዮጵያውያን ማወቅ ያለብን ጉዳይ ስለሆነ) እና ሙስጠፋ የሚገጥመው ችግር ይህን ልዩነት የሚያቻችል፣ በስልጣንና ፍትሃዊ የሀብት እና የልማት ጥያቄን የሚመልስ፣ ብቃት ያላቸውን የክልሉም ሆነ በሞያቸው ክልሉን ለማገልገል የሚሹ ኢትዮጵያውያንን በእኩል ለማስተናገድ ከፍተኛ ፈተና ይገጥመዋል።
እስካሁን ባሳየው አፈፃፀም ተስፋን አጭሮአል። በአብዲሌ የተገፉ የተማሩ የክልሉ ተወላጆችን በብቃትና በትምህርት ዝግጁነት ላይ መሰረት በማድረግ፣ በተለይም በተማሩበት ሞያ ብዙ ሰዎችን ወደ ሀላፊነት አምጥቷል። ይህ እርምጃው ብዙ ሰዎችን ወደ ትምህርት ፊታቸውን እንዲያዞሩ በማድረጉ በዩኒቨርሲትያችን ማስተርስ ለመማር የሚያመለክቱ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቧል። ይህ ከዚህ ቀደም ያልታየ ዝንባሌ ነው።
በአብዲሌ የሀምሌ 28 የተከሰተውን ከባድ ችግር ማህበረሰቡ ወደ እርቅ እና መግባባት በመመለስ የተሰነጠቀው እንዲገጥም፣ የተጣመመው እንዲቀና፣ የሻከረው ስሜት እንዲለዝብ ከፍተኛ ስራ እየሰራ ነው። ስራው ከነጉድለቱ በጣም የሚበረታታ እና ተስፋን የሚያጭር ነው።
አቶ ሙስጠፋ ነን—ሶማሌው በተለይ አማርኛ ተናገሪው የተለያየ ብሄር ብሄረሰብ በክልሉ ምክርቤት ውክልና እንዲያገኝ፣ በቀበሌው እራሱን እንዲመራ፣ በክልሉ የመንግስት ስራ መዋቅር እንዲካፈል ፅኑ ፍላጎት እንዳለው ገልፇል። ይህ በክልሉ የ27 አመት ጉዞ አዲስ ሀሳብና ደፋር ቁርጠኛ ውሳኔ ነው።
ሌላው ተስፋ ሰጪ ወጋገን ከአብይ መንግስት ጋር ያለው የተናበበ አሰራርና ክልላዊ ነፃነትና የጋራ ሀላፊነትን ሚዛን ያልሳተ አቀራረብ ሙስጠፋ ያሰበውን ለውጥ ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችለው ሁኔታዊ መመቸት የሚፈጥርለት መሆኑ ነው። ከዚህ ቀደም የነበሩ አስተዳዳሪዎች የወያኔ አሸከርና የጄኔራሎች መጫወቻ የነበሩ መሆናቸውን ስናስበው መቼም ሙስጠፋ ነፃነቱን ለጥቅም አሳልፎ ይሰጣል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ለዚህ ሀላፊነት ዳጎስ ያለ የተባበሩት መንግስታት የደሞዝና ጥቅማጥቅሞችን ትቶ መምጣቱ የሆነ የሚናገረው ነገር አለው። ዘውትር በአክቲቪስት ዘመኑ ሲሞግት የነበረውን ሀሳብ ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ሀላፊነትን ተቀብሎ ለማገልገል እንደመጣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተናግራዋል።
አቶ ሙስጠፋ የአለምን የጊዜው መንፈስ የተረዳ ሰው ነው። መደመር እንጂ በመገንጠል የማህበረሰቡ ችግር እንደማይፈታ ጠንቅቆ የገባው ነው። ለኢቲቪ በሰጠው ቃለምልልስ “መገንጠል ፋሽን ያለፈበት፣ ከአለማችን የወቅቱ እሳቤ ወደሃላ የቀረ ” መሆኑን አበክሮ ገልፇል።
መግባባትን ያቀለለት የአማርኛና የኦሮምኛ ችሎታው ለሀገር ውስጥ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጠዋል። ወደ ህዝ ለመቅረብም ቀለል ያለ ባህሪው ያግዟል።
ባንድ አጋጣሚ መሰናዶ ትምህርት ቤት ሄዶ ተማሪዎችን በመጎብኘት ሰርፕራስ ሲያደርጋቸው የአማርኛ ቅኔ ጥቁር ሰሌዳ ላይ በመፃፍ ቅኔውን እንዲፈቱለት ተማሪዎችን ጠይቋቸው አዝናንቶ መልሶላቸዋል።
አቶ ሙስጠፋ ምንም ተቃውሞ አያስተናግድም ማለት አይቻለም። ጥቅማቸው የጎደለባቸው አካላት “እንቦጭ” ሊሆኑበት እንደሚችሉ መቸም ይጠበቃል። አስካሁን ባለው አጭር ቆይታ የጎላ ችግር አልታየም።
ፈተናው ከፊት አለ፣ እድሉም ከፊት አለ።
ክቡር ፕሬዝዳንት መልካም የስራ ዘመን እየተመኘሁላቸው፣ ቃልአቃባይ ከፈለጉ፣ የህግ ምክር ከፈለጉ፣ በፕሬዝዳንት ፅቤት ፐሬስሰክረቴሪ የማህበረሰብ ሚዲያ ዋና ቡድን መሪ በተለይ የፌስቡክ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ከፈለጉ እኔ ሙክታሮቪች አለሁ ለማለት እወዳለሁ
Filed in: Amharic