>

ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል!!! (ሀይለ ገብርኤል አያሌው)

ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል!!!
ሀይለ ገብርኤል አያሌው
ያልታደለ ግራ የተጋባ ትውልድ የነጻነት ትርጉም የሃገርን ዋጋ ተሰዶ እንኳ ይጠፋዋል:: በጀርመን የታየው የድርጅት አርማ ብዛት ምንን ለመግለጽ ነው:: የሌለን ሃገር ፍለጋ ሊገኝ የማይችል የህልም አለምን ከመዞር እንዴት ቆም ብሎ ማሰብ ያቅታል:: እንዴት የሃገር  ትርጉምና ዋጋ ይጠፋዋል:: የሂትለር የዘር ማጽዳት ታሪክ : የአርዐያን ዘር የበላይነት ስብከት ምን ያህል ሰብዐዊ ውድመት እንዳስከተለ ጀርመን ሃገር ላለ ስደተኛ እንዴት ይጠፋዋል::
በጥቁር ዓለም ብቸኛውና አንጸባራቂው የነጻነት ሰንደቅ የሆነው የኢትዮጵያ ባንዲራ ይህን ያህል መጥላት ምን የሚሉት ተቃውሞ እንደሆነ ሊገባን አልቻለም:: እንግዳውን ጠቅላይ ሚንስትር እየደገፉ መቃወም : እያከበሩ መናቅ መሆኑን አለመረዳታቸው ያሳዝናል::  ጎበዝ ሃገር በጀብራሬዎች ቀረርቶና በቁጭበሉ ሕልመኞች ተረት አልተገነባም:: በደምና አጥንት በውዴታ ሳይሆን በግዴታ ነው:: ባለ ልዩ ባንዲራ ወንድሞች የዛሬይቷ ታላቋ ጀርመን እንዴት እንደተመሰረተች ጠይቃችሁም ይሁን አንብባችሁ ብታውቁት ይረዳችሁ ይሆናል::
እንደ ብረት ጠንካራው መሪ የሚል መጠሪያ የነበረው ቢስማርክ በ 25 ግዛቶች ተበታትና የነበረችውን ጀርመንን አንድ አድርጎ ለረጅም አመታት ያስተዳደረ የመጀመሪያው መሪ ነው:: የተበታተነውን የጀርመን ግዛት አንድ ለማድረግ የተጠቀመበት ዘዴ ደግሞ  (blood and Iron) የሚል ሃይልን ብቻ መሰረት ያደረገ መርሆ ነው:: ይህው ዛሬ ሃገራቸው ጀርመን ከራሷ አልፋ ለዓለም ሁሉ የምትበቃ ሃይለኛና ባለጸጋ ሆናለች:: ይህው ለኛም ተርፉ ከነልዩነታችን ከነተምታታ ማንነታችንና ኢኮኖሚያዊ ችግራችን አቅፋ ይዛናለች::
ትላንት በሃገራችንም የተደረገውና የሆነው ከዚህ ብዙም አይርቅም:: ልፉ ብሎን እንደክማለን:: ቢያድለንማ የተገኘውን ለውጥ ጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም መጣር :: መሪውን  በሞራልና በገንቢ ሂስ ማገዝን ነበር:: በውጭ ስደት ላይ ያለንው በመረጃም በኢኮኖሚም ሆነ በነጻነት ሃገር ውስጥ ካለው የምንሻል በመሆኑ በሃገር ውስጥ ለሚካሄደው እንቅስቃሴ አርዐያና ምሳሌ ሆነን መገኘት ሲገባን ግራ ተጋብተን ግራ ባናጋባው መልካም ነው::
ልቦና ይስጠን!!
Filed in: Amharic