>
10:40 pm - Tuesday August 16, 2022

ከስህተቶች ሁሉ ከባዱ ስህተት: ከስህተት አለመማር ነዉ!!!!! (ቹቹ አለባቸው)

ከስህተቶች ሁሉ ከባዱ ስህተት: ከስህተት አለመማር ነዉ!!!!!
ቹቹ አለባቸው
 
የሰው ልጅ/ ድርጅት  መቸም ቢሆን ስህተት ከመስራት ይጸዳል ተብሎ አይጠበቅም፤ባይሆን ከስህተቶቹ ይማራልና፤ የሚፈጽማቸውን ስህተቶቹንም  ይቀንሳል ተብሎ እንጅ፡፡እንዲህ ሲሆን፤ጤናማ ስህተት ይኖራል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን  አንድ ሰው/ድርጅት ዛሬም ስህተት፤ነገም ስህተት፤ከነገ ወዲያም ስህተት የሚሰራ ከሆነ፤ችግር አለ ማለትነው፡፡ዛሬሬሬ በዚህ ርእስ ዙሪያ አጠር ያለች ጽሁፍ እንዳወጣ ያነሳሳኝ ነገር ቢኖር፤ አዴፓ ውስጥ የምሰማቸውና በሩቁም ሆኘ የምታዘባቸው አንዳንድ ነገሮች ስላሳሰቡኝ ነው፡፡ 
እንዲሁም በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ፤በአዴፓ የሚመራው የክልሉ ም/ቤት ለጉባኤ እንደሚቀመጥ ስለሰማሁ፤አዴፓ በድርጅታዊ ጉባኤው ወቅት የፈጸማቸውን አንዳንድ የድርጅት አሰራር መርሆዎች ጥሰቶች በዚህኛው መንግስታዊ ጉባኤም እንዳይደግመው ለማሳሰብ ነው፡፡፡ እንግዲህ ሁላችንም እንደምናስተውሰው፤ባለፈው ወር/ሁለት ወር የተካሄደውና ብአዴንን- ወደ አዴፓነት የቀየረው ድርጅታዊ ጉባኤ፤የራሱ የሆኑ በርካታ ጠንካራ ጎኖች የነበሩትን ያክል፤ የራሱ ሆኑ ድክመቶችም ነበሩበት፡፡ በተለይም ጥሩ ሄዶ ሄዶ፤መጨረሻው ላይ ቀላል የማይባሉ ድክመቶችንም አስተናግዶ ማለፉን ታዝበናል፡፡ 
በተለይም፤በዚህ ጉባኤ ማተቃላያ ላይ የታየው ስህተት እንዲሁ ቀላል ሳይሆን፤ከባድ የመርህ ጥሰት ጭምር የታበት ስህተት ነበር፡፡ እኔ ከብአዴን ጋር በቆየሁባቸው ረዘም ያሉ አመታት ውስጥ ፤እንደባለፈው ድርጅታዊ ጉባኤ፤የድርጅት መርህ እንዲህ በግላጭ ሲደረመስ ያየሁበት ጊዜ የለም፡፡ ያለፈው የብአዴን ጉባኤ፤ የተሳካ ነበር ከተባለ፤መላ የብአዴን አባላት ስለ አማራ ጉዳይ በመሰላቸውና ባመኑበት መንገድ መወያየታቸውና በነጻነት የመሰላቸውን ውሳኔ ማስተላለፋቸው፤እንዲሁም ህዝቡ ያልፈለጋቸውን አመራሮች ከመድረኩ ገሸሽ እንዲሉ ማድረግ መቻላቸው ነው፡፡
በአንጻሩ ደግሞ፤ ይሄ ጉባኤ በተለይም፤የማእኮ ምርጫን ተከትሎ ያስተናገደው ነገር፤እጅግ የተዛባና የድርጅቱን የተለመደ ዲስፕሊን/መርህ የጣሰ ነበር፡፡ ለዚህ ድርጅታዊ መርህ መጣስ ደግሞ፤ካሁን በፊትም  በተደጋጋሚ፤ እንደተቀሰስኩት፤ዋነኞቹ ተጠያቂዎች (ጠያቂ የላቸውም እንጅ) የድርጅቱ ቁንጮ አመራሮች ናቸው፡፡ የአንድ ድርጅተ ከፍተኛ አመራር፤በአንድ ጉዳይ ላይ አምኖ ለወሰነበት ውሳኔ ተገዥና ታማኝ መሆን አለበት፡፡ ይሄ ማለት፤ በአንድ ወቅት አምኖበት የወሰነውን ውሳኔውን ለመቀየር የሚያስችል አሳማኝ ነገር ከገጠመው፤ሃሳቡን መቀየር የለበትም፤በዛው ግግም ይበል እያልኩ አይደለም፤እንደዛ ከሆነ ደንቆሮነት ነው የሚሆነው፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት፤አንድ ትልቅ አመራር፤የወሰነውን ውሳኔ እንዲሁ፤የሆነ ነገር በተነሳና ባጋጠመው ቁጥር ወሰነውን ውሳኔ በቀላሉ መቀየር አልነበረበትም/ የለበትም ማለቴ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል ብየ የማምነው፤ የብአዴን ከፍተኛ አመራር፤ስራ አስፈጻሚውና አጠቃላይ ማእከው፤ ወደድርጅታዊ ጉባኤው ሲገባ፤ ስለ አቶ ደመቀና ገዱን፤እንዲሁም ዶ/ር አምባቸው በተመለከተ፤በ ቀጣይ በድርጅቱ ውስጥ ስለሚኖራቸው የስራ ድርሻ አስተላልፎት የነበረውን ውሳኔና ለውሳኔው ተፈጻሚነት መላ አማራሩ፤ በተለይም የአመራሩ ቁንጮወዎች ያሳየውን ታማኝነትና ቁርጠኝነት በመመልከት ብቻ ፤የብአዴን አመራር ምን ያክል የድርጅቱን መርሆ እንደደረመሰው አንዱ ማሳያ ሆኖ የሚወሰድ ይመስለኛል፡፡ 
 
ስለሆነም፤በእኔ እምነት፤ባለፈው የብአዴን/አዴፓ ድርጅተዊ ጉባኤ ወቅት፤ጥሩ ነገሮች እንደተከናወኑ፤ ሁሉ፤በዚያው ልክ ደግሞ፤ከባድ የድርጅት አሰራሮችና መርሆዎች ተጥሰዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህ በርከት ያሉ መገለጫዎችን ማቅረብ ብችልም፤ ለድርጅቱና ለትግሉ ስል፤አንዳንዶቹን የመርህ ስህተቶች ሳላነሳ ማለፉን መርጫለሁ፡፡ ነገር ግን፤ላልፈው የማልችለውና፤ከወዲሁ ችግሩ ላይ በግልጽና በድፍረት ተነጋግረን ተገቢውን ማስተካካያ ካላደረግንበት በስተቀር፤መጀመሪያ አዴፓን፤ቀጥሎ ደግሞ የአማራን ህዝብ ይጎዳዋል ብየ ያመንኩበትን የመርህ ስህተት ግን በትንሹም ቢሆን ጠቁሜ ማለፉን መርጫለሁ፡፡ 
—-
ይሄ ባለፈው ጉባኤ፤ተከስቷል ብየ ያመንኩበት፤ከባድ የመርህ ጥሰት፤የጉባኤው አንዳንድ ወሳኝ ውሳኔዎች ( በተለይም፤ከድርጅት ሊ/መንበርና ም/ሊቀመንበር መሆንና አለመሆን ጋር በተያያዘ)፤ከስራ አስፈጻሚውና ከማእኮው ፍላጎትና ውሳኔ ውጭ፤በአንዳንድ ባለሀብቶች ያልተገባ ጣልቃ ገብነት መከሰቱና፤ይሄ ሁኔታም የአዴፓን አመራር ውሳኔ በታሰበው መልኩ እንዳይፈጸም ነገሩን አዛብቶቷል ብየ የአመንኩ መሆኔ ነው፡፡ በዚህ በኩል፤ምንም አይነት የአንዳንድ ባለሀብቶች ጣልቃ ገብነት አልነበረም፤በዚህም የተዛባ ውሳኔ አልነበረም/የለም ብሎ በድፍረት ሊሞግተኝ የሚፈልግ የአዴፓ አማራ ካለ፤እኔም ነገሩን በአስተማማኝ መረጃ አስደግፌ፤ ካስፈለገም፤በሂደቱ የተሳተፉትን ግለሰብ ባለሀብቶች ስም ጠቅሸ፤ ልሟገተው ሲበዛ ዝግጁ ነኝ፡፡ 
ነገር ግን፤በዚህ በኩል ወጥቶ ሊሞግተኝ የሚፈልግ የአዴፓ አመራር ከሌለለ፤እኔም ቢያንስ ለአዴፓና ላማራ ህዝብ ፖለቲካዊ ጤንነት ስል ነገሩን በለሆሳሱ አልፈዋለሁ፡፡ 
 
ችግሩ ግን፤እጅግ አደገኛ ስለሆ፤ከወዲሁ በወቅቱ ተገቢው ማስተካካያ ካልተደረገበት በስተቀር፤ ለአዴፓም ሆነ ለአማራ ፖለቲካ መጥፎ ስለሆነ፤ ስህተቱ እንዲሁ እንዳልተፈጸመና እንዳላወቅነው ሆኖ ከሚታለፍ፤በለሆሳሱም ቢሆን ችግሩ እንደነበር ተነስቶ ማለፍ አለበት ብየ ስላመንኩ አንስቸዋለሁ፡፡መነሻየም፤ ቅንነት የተላበሰ፤ምን አልባትም አዴፓ የሚሰማኝ ከሆነ፤ የአዴፓን ፖለቲካዊ ጤንነትም ለመመለስ ያግዝ ይሆናል ከሚል ነው፡፡
 
ከዚህ ስህተት ሁላችንመ ልንማር ይገባል፡፡ በተለይም የአዴፓ ቁንጮ አመራሮች፤ስራ አስፈጻሚና የማእኮ አባላት፤ለውሳኒያችሁና ቃላችሁ ታማኝ ልትሆኑ ይገባል፡፡ በመጀመሪያ ስለምታስተላልፉት ማናቸውም ውሳኔ፤በቂ አውቀትና እምነት እንዲሁም መረጃ ኖሯችሁ ሊሆን ይገባል፡፡ መጨረሻም ላይም፤ለዚህ ውሳኒያችሁ ተፈጻሚነት በጽናት መቆም አለባችሁ፡፡ ከዚያ ውጭ ነፋስ በነፈሰው አቅጣጫ ሁሉ እየተከተላችሁ በመንፈስ፤ውሳኒያችሁ ሲከረባበት እንደሌላው ሰው በትዝብት አትመልከቱ፡፡ ውሳኒያችሁን የሚያስቀይር አዲስና አሳማኝ ነገር ከቀረበ፤ ተነጋግራችሁና አምናችሁበት ቀይሩ፤ከዚያ ውጭ ወጀብ ስለገጠማችሁ ብቻ በወጀቡ አትመቱ፤አቋምና እምት ይኑራችሁ፡፡ አሁን ይሄንን ነገር እያጣችሁ እንዳይሆን ስጋት አድሮብኛል፡፡ አንድ አመራር በሌሎች ዘንድ፤ክብርና ተዳጭነትን ማግኘት የሚችለው ፤ የሚለውን ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የሚገኝ ክብርና ተደማጭነት የለም፤ካለም ጊዚያዊና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚንኮታኮት ነው ሚሆነው፡፡ ስለሆነም፤ ለክብራችሁ ተጨነቁ፤እናንተ ያላከበራችሀትን ክብራችሁን፤ ማንም ሊያከብርላችሁና፤ ሊያስከብርላችሁ አይችልም፡፡
ባለሀብቶቻችንም አስውሉ፡፡ እውነት ነው፤ለአማራ ህዝብ ልማትና እድገት ለምታደርጉት አስተዋጽኦ ፤እንዲሁም ስለ አዴፓ የምታሳዩትን መጨነቅ እናደንቃለን፤እንወዳችኃለንም፡፡ ነገር ግን በአዴፓ ፖለቲካ ውስጥ እጃችሁን ማስገባቱ፤ጥሩ አይሆንምና ይቅርባችሁ፡፡ይሄ ሁኔታ፤አዴፓን ዋጋ አስከፍሎታል፤ለ ወደፊቱም የሚስከፍለው ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ካሁን በኃላ፤በድርጅተ የውስጥ ጉዳይ ባትገቡ ስል እመክራለሁ፡፡ እውነት ነው፤ለናንተ የንግድ ስራም ቢሆን ጥሩ ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዲኖር ትፈልጋለችሁ፤ መፈለጋችሁም ተገቢነት አለው፡፡ ነገር ግን ይሄ ሁኔታ ከልኩ ካለፈ፤ነገር ስለሚበላሽ፤ካለፈው ስህተታችሁ ተምራችሁ፤ቀጣይ በአዴፓ ፖለቲካ ውስጥ የሚኖራሁን ተሳትፎ፤በቅጡና በልኩ እንድታደርጉት ወንድማዊ ጥሪየን አቀርብላችኃለሁ፡፡
—-
መፍትሄ፡-
 
አሁን አሁን ነገሮች ደስ እያሉኝ አይደለም፡፡ ስለሆነም፤ ሁላችንም በያለንበት፤ቢያንስ የጋራችን ለሆነው፤ ለአማራ ፖለቲካ ጤናማነት የየበኩላችንነ ድርሻ ብንወጣ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ስለሆነም፤የሚከተሉትን ጉዳዮች ብንተገብር፡-
 
1. ለአዴፓ ከፍተኛ አመራር፡-እናንተ ብዙ ነገሮችን አበላሽታችኃል፡፡ ነገር ግን “የፈሰሰ ውሐ አይታፈስ” እንደሚሉት፤ያለፈውን ስህተት እረስታችሁ፤ ሁላችሁም፤የገፋችሁም ሆነ፤ተገፍተናል ብላችሁ የምታስቡ አማራሮች፤ ለአዴፓና ለአማራ ፖለቲካ ጤንነት መመለስ ስትሉ፤ነገሮችን ትታችሁ/ለጊዜው በይደር አዘግይታችሁ፤በጋር እንድትቆሙ፡፡ይሄንን አንድነታችሁን ደግሞ፤በቀጣዮቹ ቀናት በሚካሄደው፤ የክልሉ ም/ቤት ጉባኤ እንድታሳዩን እንፈልጋለን፤
 
2. ለመላው የብአዴን አባላት፡-ድርጅታችሁ ታሟል፤ ይሄንን እውነታ ደግሞ ከኔ የበለጠ እናንተ እንደምታውቁት አውቃለሁ፡፡ ስለሆነም፤ጉዳዩ ወሳኝ መሆኑን አውቃችሁ፤ድርጅታችሁ፤ለመርህ እንዲገዛ በድፍረት ታገሉ፤ይሉኝታ ይብቃ፡፡ ሰው መከበርና መወደድ ያለበት በስራውና /በሚሰራው ተጨባጭ ስራ እንጀ፤በያዘው ቦታ መሆኑ ማቆም አለበት፡፡
 
3. ለአማራ አክቲቪስቶች፡- አሁን ነገሩ ሲሪየስ ነው፡፡ ነገሮች እንዲህ ከውጭ ሁነን እንደምንመለከታቸው አይደሉም፡፡ ይሄን ስላችሁ ነገር ለማካበድ አይደለም፤ ነገሮች እንደምላችሁ እንደሆኑ በቂ መረጃ ስላለኝ እንጅ፡፡ በአሁኑ ወቅት በክልላችን፤የልማት ስራዎች በተፈለገው ልክ እየተከናወኑ አይደሉም፤አዴፓም ለህዝብ እመልሳቸዋለሁ/አስመልሳቸዋለሁ ብሎ ቃል የገባቸውን የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች እየመለሰ/ ለማለስ በሚያሰችለው ቁመና ላይ አይደለም፡፡ ስለሆነም፤ነገሮችን በተለመደው መልኩ ከመመልከትና እርስ በርሳችን ከመጎነታተል ወጥተን፤የየበኩላችንን በጎ አስዋጽኦ ወደ ማድረግ ደረጃ ብንሸጋገር እላለሁ፡
 
4. ለአማራ ወጣቶች፡- ነገሮችን ከስሜት እርቃችሁ ተመልከቱ፡፡ በስሜት የሚከወን ድርጊትና፤የሚነገር ነገር ለጊዜው ባይመስለንም፤ ውሎ አድሮ እዳ ያስከፍላል፡፡ ስለሆነም እያንዳንዷ እንቅስቃሲያችሁና ንግገራችሁ፤የተመጠነ፤ የተጠና፤ብስለት ያለው፤  ወዳጅን እንጅ ጠላትን የማያባዛ፤ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን ያገናዘበ፤ ከአማራ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም ጋር የሚመዘን ይሁን፡፡
Filed in: Amharic