>
5:55 am - Wednesday December 7, 2022

ወጣትነት እኮ የራስ መንገድ የሚቀየስበት እንጂ የማንንም ዘረኛ ህልም የምናስቀጥልበት አይደለም!!! (በቃሉ አላምረው)

ወጣትነት እኮ የራስ መንገድ የሚቀየስበት እንጂ የማንንም ዘረኛ ህልም የምናስቀጥልበት አይደለም!!!
በቃሉ አላምረው
* ሁለቱን ህዝቦች ወደ አንድ ለማምጣት የሚያስችሉ ስራዎችን እንስራ! እስኪ እርስበእርሳችን አንደድሮው አንጋባ! እስኪ አብሰን እንስገድ! አስኪ አብረን ሰንበቴ አንጠጣ! ያኔ ድንበር ይፈርሳል፤ ያኔ የተገረፍነው ቁስል ይድናል፤ ያኔ ኢህአዴግ፤ ያኔ ህውሓት፤ ያኔ ብአዴን ምን ይውጣቸዋል!? 
ነገሮችን ሁሉ ለምን ሆኑ ብሎ መጠየቅ ቂልነት ነው፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካ በመካከላችን ያሳደረውን መጥፎ ጠባሳ አውቃለሁና! ነገር ግን የትግራይ ህዝብ ምን አደረገን!? የትግራይ እናት ምን አደረገችን!? ዘራፊዎች እኮ መጠኑ ይለያይ ይሆናል እንጅ ሁላችንም ውስጥ አሉ!! የትግራይ አባትስ ምን በደለን! የአማራ አባትስ ምን ፈጠረብን!? የአማራ እናትስ ምን አደረገችን!? ሁለቱ ህዝቦች በደም የተሳሰሩ ዝምድና ብንቆጥር ሶስት ጉልበት እንኳን የማይራራቁ ፤ በችግር ጊዜ የሚበዳደሩ፤ በደሰታ አብረው የሚደሰቱ፤ በጋራ ጠላታቸውን ያንበረከኩ፤ በአንድ ቋንቋ አንድን አምላክን የሚያመልኩ ናቸው! ማን ነው አማራ ያልሆነ!? ማን ነው ትግሬ ያልሆነ! ? የትኛው ትግሬ ነው ጎንደሬ ያልሆነ! የትኛው ጎንደሬ ነው ትግሬ ያልሆነ!? ማን ነው ቅድመ አያቱ አገው ያልሆነ አማራ? ወይስ ትግሬ!?
በአንድ ሙዚቃ የጨፈሩ፤ በአንድ ፅዋ ወተት የጠጡ ህዝቦች እንዴት !?ርሃብ ሲቆላቸው አብረው የሞቱና አብረው የወደቁ ህዝቦችን እንዴት በእኛ ዘመን እንለያቸው!?
ለመሆኑ የቴዎድሮስ ራዕይ፤ የአሉላ ተጋድሎ፤ የምኒሊክ ልፋት፤ የዮሐንስ ሀይማኖተኛነት፤ የበላይ ዘለቀ ስቅላት ለዚህ ነው!? ደርቡሽን ፤ግብፅን ጣሊያንን፤ ቱርክን፤ እንግሊዝን በጋራ የተዋጉ ቤተሰቦቻችን ዛሬ እንዲህ ስንሆን ምን ይሉናል!? እንዲት የአማራ እናት የትግራይ እናት የምትበላውን እህል መንገድ ትከለክላለች!? እንዴት ለፍተው በባዶ እግር እየሄዱ አስተምረውን ወላጆቻችን በህይወት ይህን ያያሉ!? ጎረቤት ሆነን የበላነው የጠጣነው፤ የተጋባነው፤ አብረን ለፀሎት የቆምነው፤ አብረን ያለቀስነው እንዴት ይረሳል! አንድ ላይ ቅኔ የቆጠሩ፤ ትርጓሜ የተማሩ፤ መዝሙር ያጠኑ፤ ቅዳሴ የቆሙ የቅዱስ ያሬድና የብዙ ሊህቃን ልጆች አንዲህ አንሆናለን!? ለምን!? ለማን አንዲደላው!? ትላንት ኢትዮጵያ እያልን እንዳልቃተትን ዛሬ በየጎጣችን ለምን መመሸግ ፈለግን!? ይህን የመጨረሻ አማራጫችን ስለሆነ ነው!? አይደለም!!!
አንድ አባት እንደ ልጁ ቆንጥጦ አሳድጎን የታል ግብረገብነቱ!?ለመሆኑ በየቦታው የምንሰዳደበው ሁሉቱን ህዝቦች የሚመያዋርድ መሆኑ ጠፍቶን ነው!? በቃ ወንድ ልጅ ተወልዶ ካልሆነ እንዳባቱ ማለታችን ይህ ነው!? ተው የሚል ሽማግሌ፤ ቄስ፤ ሸህ፤ እናት አባትስ ይጠፋል!?
በእውነት አውቃለሁ ትንሽ ልጅ ነኝ፡፡ ግን እየሆነ ባለው ነገር በእጅጉ አዝናለሁ! የአማራና የትግራይ ወጣት በቦለቲከኞች አስረሽ ምቺው ዳነንኪራና ሴራ እንዲህ መሆን አለበት ብዬ አላስብም! አንድ የአማራ ወጣት ጤፍ ገዝቶ የሚሄድን የትግራይ ወጣት ንብረት አስቁሞ ከዘረፈና ከበላ ሰባዊነታችን ወርዷል፡፡ ለመስዋዕትና ለቅዳሴ የተገዛ ስንዴ የትም ይበተናል፡፡የአንተ እናት አንደሚርባት ሁሉ፤ የአንተ ህፃን ልጅ በጠዋት ዳቦ ብላ እንደምታለቅስ ሁሉ የትግራይ እናትና ልጅም ታለቅሳለች፤ ይርባታል፡፡
እስኪ የራሳችንን ዘመን እንባርክ፡፡ ሁለቱን ህዝቦች ወደ አንድ ለማምጣት የሚያስችሉ ስራዎችን እንስራ! እስኪ እርስበእርሳችን አንደድሮው አንጋባ! እስኪ አብሰን እንስገድ! አስኪ አብረን ሰንበቴ አንጠጣ! ያኔ ድንበር ይፈርሳል፤ ያኔ የተገረፍነው ቁስል ይድናል፤ ያኔ ኢህአዴግ፤ ያኔ ህውሓት፤ ያኔ ብአዴን ምን ይውጣቸዋል!? ሳይወዱ በግድ ይጠፋሉ ወይም እኛን ይመስላሉ! እስኪ በየማህበራዊ ድሩ መልካም ነገር እንነጋገር! እስኪ የሀይማኖት ጉዞና ጉብኝት አንጀምር! ወጣትነት እኮ የራስ መንገድ የሚቀየስበት አንጅ የማንንም ዘረኛ ህልም የምናስቀጥልበት አይደለም!
እባካችሁ ነገሮችን አናርግብ!!!!
Filed in: Amharic