>

የላሊበላ ጉዳይ ተራ የህንፃ ጉዳይ አይደለም የታሪካ፤ የባህል፤ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳይ ነው!!! (ቹቹ አለባቸው)

የላሊበላ ጉዳይ ተራ የህንፃ ጉዳይ አይደለም የታሪካ፤ የባህል፤ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳይ ነው!!!
ቹቹ አለባቸው
የላሊበላ አለም አቀፍ ቅርስ፤ለኢትዮጵያዊያን እንደ አጠቃላይ ፤በተለይም ደግሞ ለአማራ ህዝብ ሁለመናቸው ነው፡፡ ይህ ቅርስ ኢትዮጵያን በአለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትተወቅና እንድትጠራ አስችሏታል፡፡ ለአማራ ደግሞ፤የላሊበላ ቅርስ ከዚህም በላይ ነው፡፡ ይሄውም ፤ላሊበላ፤በአንድ ወቅት የአማራ ህዝብ ደርሶበት የነበረውን፤የስልጣኔ የከፍታ ደረጃ ማሳያ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው፤የላሊበላ ቅርስ ሁለመናችን ነው የምንለው፡፡ ይሄ ማለት፤ የላሊበላ ቅርስ ለኢትዮጵያ፤በተለይም ለአማራ፤ታሪኩ ፤ኩራቱ፤ የስልጣኔው መገለጫ፤ወዘተ…ሲሆን ዝቅ ሲል ደግሞ የኢኮነሚ ምንጩም ነው እንደማለት ነው፡፡
የላሊበላ ቅርስ ጉዳይ፤ተራ የህንፃ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይልቄንስ፤ ላሊበላ የታሪካ፤ባህል፤ፖለቲካና ኢኮነሚ ጉዳይ ነው፡፡ላሊበላ ትልቅ፤አለማቀፋዊ፤አገራዊና ክልላዊ፤ቅርስና ሀብት ነው፡፡ የላሊበላ ጉዳይ አይመለከተኝም የሚል አካል ሊኖር አይችልም፤ ካለም እሱ ተንኮለኛ ነው፡፡ ይሄም ማለት፤ለላሊበላ ቅርስ ፤ባለቤቶቹ መላው የአለም አቀፉ ማህበረሰብና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ናቸው ማለት ነው፡፡ይሄ በዚህ እንዳለ፤ሰሞኔን ደግሞ፤ የላሊበላ አለም አቀፍ ቅርስ፤እንደ አዲስ ሞቅ ባለ ሁኔታ ማነጋገር ይዟል፡፡
እንደተከታተልኩት ከሆነ ደግሞ፤በተለይም የአካባቢው ህዝብ፤ ሙስሎሞችን ጨምሮ፤የላሊበላ ነገር ስጋት እንዳሳደረባቸው፤ ስለሆነም የሚመለከታቸው አካለት አንድ ነገር እንዲሉ፤በማለት ወደ አደባባይ በመውጣት በሰላማዊ በሰልፍ ጭምር ስጋታቸውን አስተጋብተዋል፡፡ ይሄንን ሁኔታ ተከትሎም፤ የላሊበላ ነገር ማነጋገሩን ቀጥሏል፡፡ የመነጋገሪያው ጭብጥም፤ቅርሱ ወደ መፍረስ ደረጃ ተቃርቧል፤ችግሩን አይቶ መፍትሄ የሚሰጠው አካል አልተገኘም፤ስለሆነም ይሄን ቅርስ እንደታደገው የሚል ነው፡፡ይሄን ጩከት የሰሙ አካላትና ወገኖች፤ ሳያፍሩ አንጀት የማያርሰውን የተለመደውን ሰንካላ ምላሽና አስተያየታቸውን ሲሰጡ እያዳመጥናቸው ነው፡፡
እኔ በበኩሌ፤ ለመጨረሻ ጊዜ የላሊበላን አለም አቀፍ ቅርስ የተመለከትኩት፤በ2008 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ በወቅቱ አብዛኛዎቹን ቅርሶች ተዟዙሬ ተመልክቻቸዋለሁ፡፡ በዛን ወቅትም እንደተመለከትኩት፤ የቅርሱ ይዞታ እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡ሆኖም፤በወቅቱ ከባድ ስጋት አድሮብኝ የነበረ ቢሆንም፤አንድ ተስፋ ግን ሰንቄ ነበር የተመለስኩት፡፡ ይሄውም ከአካባቢው ሰዎች እንደተነገረኝ፤በቅርብ ጊዜ ሙሉ ጥገና እንደሚካሄድለት፤ጉዳዩንም መንግስት በትኩረት እንደያዘው፤በዚሁ አግባብም ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተነግሮኝ ነበር፡፡ እኔም ተስፋ ሰንቄ ነበር የተመለስኩት፡፡ ይሁን እንጅ ከ2 አመታት በኃላም፤አንድም ለውጥ ሳይታይ፤ሁሉ ነገሩ ባለበት እየሄደ እንደሆነ፤ከሰሞኑ መረዳት ችያለሁ፡፡ እንዲያውም፤ አይደለም ችግሩ ሊቀረፍ፤ቅርሱ ባለቤት የሌለው እስኪመስል ድረስ፤ለከፋ አደጋ ተጋልጦ የምንመለከትበት ደረጃ ላይ ደርሰናል አሉ፡
የዚህን ሁኔታና ችግር ለማጣራት፤ባደረግኩት ጥረት ያገነሁት መልስ ቢኖር፤አሁንም ያው ከመንግስት እየጠበቅን ነው የሚል ነው፡፡ ስለጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት እንደተረዳሁት፤ የህንፃውን ጥገና ለማከናወን፤ሁሉም ነገር ተሟልቷል፡፡ ዝርዝር ጥናት ተካሂዷል፤የጥገና ስራው እንዲከናወን UNESCO ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ ጥገናው በ3 አመታት ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችልና፤ ይሄን ተግባር ለማከናወን የሚያስፈልገው በጀትም እስከ 300 ሚሊዮን ብር እንደደሚደርስ ታውቋል፡፡ይሄ ሁሉ መረጃ፤ ለፌደራልና ለክልሉ መንግስታት በወቅቱ ቀርቦላቸዋል፡፡ነገር ግን እነዚህ አካለት በመረጃው ላይ ተኝተውበታል።
እኔ እኮ የሚገርመኝ፤ይሄ ቅርስና ጥበቃ፤ምናምን የሚሉት ጉልትና አጁዛ  መስ/ቤት ነው፡፡ የዚህ ተቋም አላማ ምንድን ነው? የላሊበላን አለም አቀፍ ቅርስ መጠበቅ ያልቻለ ተቋም ምን አይነት ተቋም ነው? የተቋሙ መኖር ጥቅሙስ ምኑ ላይ ነው? ደግሞ እኮ፤ እንደሰማሁት ከሆነ፤የሚሰጠው ምክንያት አስጠሊታ መሆኑ ነው፡፡ ይሄ ተቋም፤እየሰጠው ያለው መልስ፤እስካሁን ወደ ጥገና መግባት ያልተቻለው፤ አስፈላጊው በጀት ባለመገኘቱ ነው የሚል ነው፡፡ ጉድ በል ጎንደር የሚባለው እዚህ ላይ አይደል፡፡ በግለሰቦች ብቻ፤ በየአመቱ በቢሊየን የሚቆጠር ብር የሚዘረፍባት አገር ኢትዮጵያ፤ የላሊበላን አለም አቀፍ ቅርስ ለማስጠገን የሚውል 300 ሚሊየን ብር ማጣት? ያውም እኮ፤ይሄ ገንዘብ የግድ ባንዴ መገኘትን አይጠይቅም፤በየአመቱ 100 ሚሊየን ብር ብቻ መመደብን የሚጠይቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ይሄም ቢሆን አልሆነም፡፡ምክንያት ጉዳዩን በባለቤትነት ወስዶ መሟገት ላይ ችግር ሳይኖር አልቀረም፡፡ ያለበለዝያም፤ አንዳንድ አላዋቂዎች፤ ወይም ተንኮለኞች፤ የላሊበላን ጉዳይ የአማራ ጉዳይ ብቻ አድርገው ሳይመለከቱት አልቀረም መሰለኝ፡፡ እንደዛ ባይሆንማ፤300 ሚሊየን ብር፤ ለኢትዮጵያ ምን ያክል ከባድ ሁኖ ነው?ያውም ለላሊበላ ቅርስ፡፡
ለሁሉም፤የላሊበላ ነገር፤በወቅቱ አንድ ነገር ካልተባለ በስተቀር፤ ሊያስተፋፍረን ይችላል፡፡
 ዛሬ ቀድመን ባለመድረሳችን፤የላሊበላ ቅርስ ወደ አለመሆን ከደረሰ፤ችግር ነው፡፡ በተለይም ይሄ ሁሉ ነገር ሲሆን፤ አንድ ነገር ማድረግ ያልቻሉት አዴፓና የክልሉ መንግስት ከባድ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል፡፡የፌደራሉ መንግስትም፤አባቶቻችን ያቆዩልንን ቅርስ፤ሲፈርስና ሲወድም ዝም ብሎ ተመልክቶ፤ ነገር ከተበላሸ በኃላ ለማስተዛዘን ቢሞክር፤ከባድ ዋጋ ሊከፍል ይችላል፡፡ ማስተዛዘን ይሄኔ ነው፡፡ ስለሆነም፤የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግስታት፤ለላሊበላ ቅርስ የማይሆን በጀት አፈር ይግባ ብለው፤ጠንካራ ውሳኔ ላይ መድረስ አለባቸው፤ነገሩ ቀልድ አይደለም፡፡
እኔ በበኩሌ፤በላሊበላ ቅርስ ላይ እየደረሰ ያለው በደል፤እንዲሁ በድንገት የተከሰተ አደጋ ሳይሆን፤የሌሎቹ በደሎቻችን ተቀጥላና አንዱ መገላጫ አድርጌ ነው የምመለከተው፡፡ ሁላችንም እንደምነገነዘበው፤ሕወሀት አማራን መፈተን የፈለገውና የሞከረው፤ ሥነ-ልቦናውን በመጉዳት፤ለም መሬቶቹን በወረራ በመንጠቅ፤ የአማራ ህዝቦችን እንዲበታተኑ በማድረግ፤የአማራ ህዝብ ስልታዊ በሆነ መንገድ ቁጥሩ እንዲቀንስ በማድረግ፤የአማራ ህዝብ በሌሎች ህዝቦች ዘንድ እንዲጠላና በጥርጣሬ እንዲታይ በማድረግ፤በኢኮነሚ እንዲዳሽቅ በማድረግ፤በአጠቃላይ  በሥርአተ-መንግስቱ ተገቢው ውክልና ተሳትፎ እንዳይኖረው በማድረግ ወዘተ…ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንስ፤ሕወሀት፤የአማራ ህዝብ አኩሪ ታሪክ፤ባህልና ቅርስም እንዲጠፋና እንዲዳከም፤በግልጽ በማኒፌስቶው አስቀምጦ ታግሎበታል፡፡
 ስለሆነም፤አሁን በላሊበላ ፤ቅርስ ላይ አንዣቦ የምንመለከተው የጥፋት ዳመና መንስኤው ከዚሁ ሴራ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ሁኖ ነው የሚሰማኝ፡፡ አንዳንድ የዋሆች፤ዛሬ ሕወሀት ስልጣን ላይ ስለሌለ፤ይሄን ጉዳይ ለምን ከሕወሀት ጋር አያይዘህ ትመለከተዋለህ? ሊሉ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን አያይዘዋለሁ፤ ምክንያቱም፤የላሊበላ ቅርስ ችግር ላይ መውደቁ የታወቀው በነዚህ 2/3 አመታት ውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ሕወሀት አገሪቱን ባስተዳደረባቸው 27 አመታት በሙሉ ሲነሳ ሲወድቅ የነበረ ችግር ስለሆነ ነው፡፡ ስለሆነም፤ጉዳዩ ያደረ የቤት ስራ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ በኩል፤ሕወሀት ሌሎች በርካታ፤ጊዜ የሚጠይቁ የቤት ስራዎችን ጥሎልን እንዳለፈ ማወቅም ተገቢ ነው፡፡
የላሊበላ አለም አቀፍ ቅርስ ጉዳይ፤ ከፈፍ ሰሲለል ባነሳሁት ደረጃ ነው መታየት ያለበት፡፡ የላሊበላ ቅርስ መፍትሄ ሳይሰጠው አንድ ነገር ቢሆን፤የክልሉም ሆነ፤የፌደራሉ መንግስት እራሳቸው፤ በፍቃዳቸው  እንደማፍረስ  ይቆጠርባቸዋል፡፡ መቸም ካለበደ በቀር፤ላሊበላ ሲፈርስ ቆሞ ያየ የክልልም ይሁን የፌደራል መንግስት፤ የአማራንና የኢትዮጵያን ህዝብ ልግዛ አይልም፡፡ ስለሆነም ወደዚህ ሰጣ ገባ የሆነ አስጠሊታ ነገር  ውስጥ ከመግባታችን በፊት፤”ሁሉም ነገር” ወደ ላሊበላ ግንባር ሊሆን ይገባል እንላለን፡፡ በቃ አቋማችን ይሄው ነው፡፡ በሌላ ነገር እንዳይተረጎም ምክር ቢጤ ናት ፡፡
ሁሉም ነገር ወደ ላሊበላ ግንባር!
Filed in: Amharic