>
5:13 pm - Thursday April 18, 2182

ስለ ቅማንት ጉዳይ በግልጽና በድፍረት የምንናገርበት ወቅት አሁን መሰለኝ!  (ቹቹ አለባቸው)

ስለ ቅማንት ጉዳይ በግልጽና በድፍረት የምንናገርበት ወቅት አሁን መሰለኝ! 
ቹቹ አለባቸው
 
* የጠላፊና አስጠላፊ ጨዋታ መቆም አለበት!
* …በወቅቱ ህወሀት፤ከአጭር ጊዜ አኳያ አንገረብ ወንዝ መለስ፤በመካከለኛ ጊዜ ደግሞ እስከመተማ፤ከዚያም እያለች የመስፋፈት ፖሊሲ ነድፋ እየሰራች ነው ስል፤ስሟገት ኖሪያለሁ!! 

 

በተደጋገሚ እንደነገርኳችሁ፤የዚህን አካባቢ ማህበረሰብና አጠቃላይ ሁኔታ ከሚያውቁት ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ ለሁለት አመታ አካባቢውን በካድሬነት መርቸዋለሁ፡፡ እኔ በአካባቢው በነበርኩበት ወቅት፤ የአካባቢው ማህበረሰብ መጀመሪያ ላይ ቅማንት ተብሎ ለመጠራት እንኳን ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ ሆኖም በሂደት የቅማንት ሙህራን በሰሩት የተራዘመ ቅስቀሳ አብዛኛው የቅማንት ማህበረሰብ፤እኔ ከአማራ የተለየ ማንነት አለኝ ብሎ የራሱን ማንነት አስከብሯል፤ የራስ አስተዳደር ባለቤትም ሆኗል፡፡ ወደ ዚህ ደረጃ ለመደረስ ደግሞ ብዙ አላስፈላጊ ዋጋ ተከፍሏል፡፡
ነገር ግን ይሄ ሁሉ ዋጋ ተከፍሎ እዚህ ደረጃ ቢደረስም፤ ዛሬም ላይ የቅማንት ጥያቄ መቋጫ አላገኘም፡፡ ከቅማንት ጥያቄ ጋር በተያያዘ፤ አንዴ ሰው ሲሞት፤ሌላ ጊዜ ንብረት ሲቃጠል፤ሌላ ጊዜ ደግሞ መንገድ ሲዘጋ፤ በሌላው ወቅት  ደግሞ ለ3 አመታት ያክል ግብር አንከፍልም ሲባል፤ብቻ ብዙ መከራዎችን እያስተናገድን ነው፡፡እነዚህ መከራዎች የሚከሰቱት በሁሉም ወገኖች ቢሆንም፤ ዋነኛው መንስኤ ግን በአንዳንድ የቅማንት ወገኖች የሚነሳው ቅጥ ያጣ ጥያቄ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ጥያቂያቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታ ከመሞከር ይልቅ፤ በትቢት ተወጥረው ሲቸገሩም ይታያል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ፤ በአንዳንድ የአማራ ወገኖችም ስህተቶች አሉ፡፡ ይሄውም አንድ ቅማንት ባጠፋ ቁጥር በጀምላ ሌላውን መቅጣትና ጉዳት እንዲደርስበት ማድረግ እየተደጋገመ  መጥቷል፤ ይሄ መስተካከል አለበት፡፡ ድርጊቱ የጅምላ ፍርድም ይሆናል፡፡
ለመሆኑ የቅማንት እውነተኛ ጥያቄ ምንድን ነው? 
ውዝግቡስ መቋጫ አላገኝ ያለው ለምንድን ነው?
ለነዚህ ጥያቄዎች፤ሰዎች ምላሾቻችን አንድና ወጥ እንደማይሆን አውቃለሁ፤ቢሆንም አይደንቀኝም፤ ምክንያቱም፤ስለ ጉዳዩ ያለን ቅርበት እውቀትና አመለካከት የሚለያይ በመሆኑ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በተመለከተ፤የኔ የግሌ እይታ እንደሚከተለው ነው፡-
1.የቅማንት እውነተኛ ጥያቄ ምንድን ነው? በዚህ በኩል፤አንድ የማልክደው እውነታ አለ፤ይሄውም በተለይም አብዛኛው የቅማንት ህዝብ ፍላት፤ከአማራ ወንድሞቹ ጋር ሳይጋጭ፤በተቻለ መጠን በነበረበት አከኋን ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንዲረጋገጥለት ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ጤነኛና በሁሉም ወገን የሚደገፍ ነው፡፡ በመሆኑም ህገ -መንግስትን ተራምዶም ቢሆን የክልሉ መንግስት የቅማንትን ጥያቄ በበቂ መጠን አስተናግዶታል ብየ አምናለሁ፡፡በዚህ  በጎ ምላሽ እረክቶ አለመቀመጥ፤ እኛ አማራዎች፤ በቅማንት ህዝብ ጥያቄ ህዊነትና እውነተኝነት ላይ ጥያቄ እንድናነሳ እንገደዳለን፡፡ ህገ-መንግስትን ሳያመልኩ፤ ለቅማንት ማህበረሰብ የተፈቀደው  ራስን- በራስን  የማስስተዳደር ውሳኔ፤ሰላምና ፍቅርን ማንገሱ ቀርቶ፤ እረብሻና ሞት የሚያስከትል ከሆነ፤ ለምን ህግገ-መንግስትን ችላ ብለን  የራስ አስተዳደርን ጥያቄን እናስተናግዳለን? በእኔ እምነት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከማህበረሰቡ ሙህራን ጋር እንደገና መምከርና ውሳኔ ላይ መደረስ ያለበት ይመስለኛል፡፡
2.ሁለተኛው መታየት ያለበት ነጥብ ፤መንግስትና የአማራ ህዝብ ይሄንን ሁሉ ትእግስት እያሳዩ፤ ከቅማንት ጋር ተያይዞ የተነሳው ውዝግብ መቋጫ ያጣው ለምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ ይሄ ጥያቄ፤ የቅማንትን ጥያቄ  እውነተኝነትና ሀቀኝነት እንደገና እንድንመረምር ያስገድደናል፡፡ከላይ እንዳነሳሁት፤ በቅንነት ጥያቄውን የሚያነሱ ወገኖች እንዳሉ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ የነዚህ ወገኖች ጥያቄ፤ቅንነት የተሞላበት፤ከአማራ ጋር በሰላም መኖርን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ይሄንን ሃሳብም እንደግፈዋለን፡፡
ነገር ግን በእኔ እምነት፤ የቅማንት ጥያቄ በሌላ ወገኖች ፍላጎት ተጠልፏል(Hijack ተደርጓል)፡፡በዚህ በኩል ዋነኛው ጠላፊ ህወሀት ስለመሆኑ፤የራሳቸው የትግራይ አክቲቪስቶች እየመሰከሩ ነው፡፡ አሁን ትኩረታችን መሆን ያለበት ጠላፊው ላይ ብቻ ሳይሆን አስጠላፊውም ላይ መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡ጠላፊዋን ህወሀትን በመርገም ብቻ፤የቅምንትን ችግር የምንፈታው አልሆነም፡፡ ህወሀትናማ ህወሀት ነው፡፡ ህወሀት የትግራይን ደንበር ቤንሻንጉል ለማድረስ በነበራት እቅድ መሰረት፤ቅማንትን ዋነኛ መሻጋገሪያ ድልድይ አድረጋ መነሳቷን እናውቃለን፤ሲክዱት ቢኖሩም፤እነሆ ጊዜው ደርሶ ዛሬ በራሳቸው አንደበት እየለፈለፉት ነው፡፡
ከዚህ ህወሀት ቅማንትን ተጠቅሞ፤ቤንሻንጉል ለመድረስ ከነበረው እቅድ አንጻር፤ሁለት ነገሮችን ዛሬም አስተውሳለሁ፡፡ ይሄውም፤ አንዱ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ የተገነዘብኩት እውነታ ሲሆን፤ሌላኛው ደግሞ የ2008 ዓ.ም አመጽ ተከትሎ የተገነዘብኩት እውነታ ነው፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ ህወሀት፤ከአጭር ጊዜ አኳያ አንገረብ ወንዝ መለስ፤በመካከለኛ ጊዜ ደግሞ እስከመተማ፤ከዚያም እያለች የመስፋፈት ፖሊሲ ነድፋ እየሰራች ነው ስል፤ስሟገት ኖሪያለሁ፡፡
በተለይም ይሄን አቋሜን፤በ2008 ዓ.ም አቶ አለምነው መኮንን በአብቁተ አዳራሽ በመራው መድረክ ያቀረብኩ ሲሆን፤በዋናውና እነ በረከትና አዲሱ በተገኙበት የማጠቃለያ መድረክም ላይ ይሄንን እምነቴን ደግሜው ነበር፡፡ በወቅቱ የተመለሰልኝ መልስ ግን፤ “ይሄ የመንደር ወሬ ነው፤እኔ ህወሀት ደንበሬ መተማ ነው ስትል ሰምቸ አላውቅም፤ሰው መናገር ያለበት በተጻፈ ነገር ላይ ተመስርቶ እንጅ፤በስሜትና በአሉባልታ መሆን የለበትም” ተባልኩ፡፡ እኔም እንዳላችሁ ብየ ዝም፤ምን አቅም አለ፡፡ እኔ ግን እንደዛ በድፍረት የተናገርኩት እውነቴን ነው፡፡ የህወሀትን ሴራ ጥሩ አድርጌ ስለማውቃት፤ከልቤ ነበር የተከራከርኩት፤ግን ምን ዋጋ አለው፡፡
ብቻ በዚህ መልኩ ህወሀት መተማ ከደረሰ፤ቀድሞ ያዘጋጃቸውን የቅማንት ወገኖች ተጠቅሞ፤ መጀመሪያ ቋራ ለመድረስ ፤ከዚያማ ማን ያቆመዋል፡፡ ህወሀት ዛሬም ድረስ አንዳንድ የቅማንት ወገኖችን ከፊት አድርጎ፤ እንዲህ ሰላም የሚነሳን ፤ያችን የረዥም ጊዜ እቅዱን ለማሳከት ካለው ፍላጎት ተነስቶ ነው፡፡
ሌላውና የማረሳው ነገር ደግሞ፤የ2008 ዓ.ም አመጽን ተከትሎ አንድ፤ በናቱ ከትግራይ በአባቱ ደግሞ ከጎንደር አማራ የሚወለድ  የቅርብ ጓደኛ ያጫወተኝን ነገር ነው፡፡ ይህ ጓደኛየ እንዳጫወተኝ፤ የጎንደር አመጽ በተነሳበት ወቅት፤ ወደ ትግራይ ይደውልና ዘመዶቹን ያገኛል፡፡ እንዴት ነው ዘንድሮ ወልቃይትን ካልመለሳችሁ ተነስተንባችኋል፤ ልንጨርሳችሁ ነው ሲል ይቀልደዋል፡፡ የተከዜው ማዶ  ሰው ደግሞ ቧ፤ አታ፤ ወደይ፤ ወልቃይትን ካለችሁማ፤የትግራይ ወጣት በሙሉ ወደ ጦርነት መዝመቱ ነው አለው፡፡ የኔው ጎንደሬ ደግሞ፤አይ አትችሉነም፤ አይሆንላችሁም፤ይልቁንስ ወልቃይትን በሰላም  ብታስረክቡን ይሻላል ሲል መልሶ ይቀልደዋል፡፡ በዚህ መካከል የተከዜው ማዶ ሰው፤ ስማ እንጅ ይለዋል፤ጎንደሬውን፤ አቤት፤ በጎንደር አካባቢ ትክል ድንጋይ ምትባል ወረዳ ታውቃለህ? ይለዋል፡፡ የኔው ጓደኛም፤አወ አውቃለሁ፤ የተከዜ ማዶው ሰው፤ የትግራይ እኮ ደንበሩ እስከሱ ድረስ ነው፤በማለት እንደመለሰለት ጓደኛየ አጫወተኝ፡፡ እኔም ይችን ነገር ነገር ማባበስና የግለሰብ ሃሳብምበማለት፤እስከዛሬ ሳልናገራት ቆየሁ፡፡ አሁን ግን ነገሮችን ስመለከታቸው ለካስ የተከዜው ማዶ ሰው፤ ትግራይ ደንበሯ ትክል ድናጋይ ድረስ ነው ያለው፤ በግሉ ስሜት ተነሳስቶ ሳይሆን ድርጅቱ ህወሀት ያለውን ሰምቶ ነው፡፡
እና ምን ይሻለናል?
እንግዲህ ይሆናል ብለን ብዙ ነገሮችን አሳለፍን፤በዚህ ሂደት ደግሞ ከሁለቱም ወገኖች ሰው እየተጎዳ ነው፤ንብረት እየወደመ ነው፤ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል መኖር የነበረበት የመተባበር መንፈስ ከአደር አደር ወደ መበጠስ እያመራ ነው፡፡ ብቻ ነገሩ ወደድንም ጠላንም፤ጣመንም አልጣመንም ወደ ከፋ ጫፍ እየደረሰ ነው፡፡ብንደብቀው፤ ብንደብቀው፤ብንሸሽገው፤ ችግሩ በራሱ እየተናገረ ነው፡፡ ስለሆነም፤ከአሁኑ የከፋ ነገር ሳይገጥመን፤መላ ብንፈልግ ጥሩ ነው፡፡ እኔ በግሌ፤በሚከተሉት ነጥቦች ዙሪያ ብንረባረብ እላሁ፡-
1.ካሁን በኋላ፤ከቅማንት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጥያቄ፤ንጹህ ጥያቄ እንዳልሆነ፤ትክክለኛው የህዝብ ጥያቄው በጠላፊዎችና አስጠላፊዎች እጅ ገብቶ አገርን እያመሰ እንደሆነ፤ስለሆነም፤ካሁን በኋላ፤በትእግስት እንደማይታይ፤ መንግስት እንቅጩን መናገ አለበትር፡፡ መላው የአማራ ህዝብም ጉዳዩን በዚህ ልክ አስፍቶ በማየት ጠላፊና አስጠላፊዎችን፤ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ያለ ምህረት መታገል አለበት፡፡ ይህም ማለት፤ከመቸውም ጊዜ በላይ ይሉኝታና መቻል የሌለበት የህግ የበላይነት የማስከበር ስራ መጀመር አለበት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ በዚህ ምክንያት፤እውነተኛው ህዝብ ጥያቄ አብሮ እንዳይጨፈለቅ፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
2.የሁለቱንም አስተዳደሮች ማጠናከር( ቅምንትና አማራ)፡፡ በተለይማ ዛሬ አዳኝ አገር ጫቆን ባካተተ መልኩ ነጋዴ ባህር ላይ የተቋቋመው አዲሱ የአማራ ወረዳ፤ሁሌ ስመኘው የነበረ ነገር ስለነበር ደስ ብሎኛል፡፡ የዚህ ወረዳ መመስረት፤ለቅማንት ጥያቄ ጠላፊዎችና አስጠላፊዎች ከባድ መርዶ እንደሚሆን አውቃለሁ፡፡ስለሆነም፤ይህ ወረዳ በልዩ ትኩረት መጠናከር ይገባዋል፡፡
3.ሁሌም ቢሆን፤በሁለቱም ወገኖች በኩል፤በችግሩ ውስጥ የሌሉበት ወገኖች ለጉዳት እንዳይጋለጡ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ሁሉም የቅማንት ህዝብ የጠላፊና አስጠላፊ ድራማው አካል አይደለም፤ ስለሆነም፤ ከነዚህ ጠላፊዎችና አስጠላፊዎች ጋር የምናካሂደው የመረረ ትግል፤ይሄንን እውነታ ግምት ባስገ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ይህ ክፉ ቀን ያልፋል፤ስለዚህ በተቻለ መጠን፤ ነገ የማንጸጸትበትን ስራ ብቻ እንስራ፡፡
Filed in: Amharic