>
2:52 pm - Tuesday July 5, 2022

ከስደቶች ሁሉ ክፉው ስደት ከህግ የበላይነት የተሰደደ ስደት ነው!!! (ገበያው ይታየው ጌትነት)

ከስደቶች ሁሉ ክፉው ስደት ከህግ የበላይነት የተሰደደ ስደት ነው!!!
ገበያው ይታየው ጌትነት
አንድ ሰው ከሀገሩ እርቆ  ነገር ግን መብቱ ተከብሮ ሀገር አልባ ሆኖ ከሚኖር እና በሀገሩ እየኖረ ነገር ግን ሀገሩ ውስጥ የህግ የበላይነት ከሌለ ይህ ሰው በሁለቱም ስደተኛ ነው፡፡ አንደኛው ስደት ከተወለደበት፤ከአደገበት፤ዘመድ ልጅ ሆኖ ከቦረቀበት፤ጓደኞቹን በትዝታ ከሚያስታወስበት ትውልድ ሀገሩ መሰደዱ ሲሆን ሁለተኛው ስደት ደግሞ ከሕግ የበላይነት ነው፡፡

ከህግ የበላይነት የሚደረግ ስደት ከራስ አስተሳሰብ ጋር የሚደረግ ስደት ነው፡፡የሰው ልጅ ከራሱ ከተሰደደ እሱነቱን እንደረሳ አቅሉንም የሳተ በመሆኑ የጤንነቱ አሳሳቢነትም ችግር ውስጥ እንደሆነ ልንረዳው ይገባል፡፡ከህመም የሚጠበቀው አንድም ስቃይ፤ወይም መጥፎ ሽታ እና ቁስል አንድም ተያይዞ ሞት ነው፡፡ በተለይ ተላላፊ ህመም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የህግ የበላይነትን በተመለከተ ተላላፊ ህመሞች በዝተዋል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ በዜጎች ላይ የሚፈጠርን አይን ያወጣ ሰብአዊ መብት ረገጣ፤አድሏዊ አሰራር፤የቡድን የበላይነት እና የመሳሰሉትን ለመታገል በተደረገ የሞት ሽረት ትግል በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ መስዋትነት ተከፍሏል፡፡ ይህ አይተኬ የሆነ የጀግና ወጣቶች ወሳኝ አቅም በሞት መገታት፤ሩጠው ቦርቀው ያልወጣላቸው ጨቅላ ህጻናት መቀጨት፤ለምረቃት የተሰናዱ የአረጋዊያን አንደበቶች በአንባገነን ወታደር ተዘግተዋል፡፡ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ደርሷል፡፡ይህ የአንድ ጊዜ ያውም ወደ መልካም መንገድ መሸጋገሪያ እንጅ በየአመቱ ልንዘክረው የሚገባ ድርጊት መሆን የለበትም፡፡ስንት ጊዜ ለአብዮት እንዘጋጅ? ስንት ትውልድስ በአቢዮት የሚበላባት ሀገር ልጆች እንሁን?

አሁን እየመጣ ባለው አንጸራዊ የዲሞክራሲ መስፈን ስንት አመት ስንጠላው የነበረው የመንግስት ስርዓት እራሴን ላርም ነው እያለ በተዘጋጀበት ሁኔታ ህዝብ እያደረገው ያለው መረን የለቀቀ የህግ ማስከበር ሂደት ግን የ2010 ዓ.ም የአሮጌው ዘመን በሽታችን ነው፡፡

ለመሆኑ የሕግ የበላይነት ማለት ምንድን ነው? የሕግ የበላይነትስ እንዴት ሊከበር ይችላል? የህግ የበላይነትን ማን ያስከብር? በአዲሱ ዓመት የህግ የበላይነት በሀገራችን ምን ድርሻ ሊኖረው ይገባል? የሚለውን እንመልከት፡፡

የሕግ የበላይነት ትርጉም

የሕግ የበላይነት በዓለም ላይ ባሉ የሕግ ልሂቃን ብዙ አሻሚ ትርጓሜዎች ቢኖሩትም  አስማሚ ትርጉም የሰጡት ብርያን ዘ ታማባለሃ “የህግ የበላይነት ማለት የአንድ ሀገር የመንግስት ባለስልጣናት፤ሃላፊዎች እና ዜጎች በሙሉ የሚያከብሩት  እና የሚታዘዙለት ስርዓት ነው” ሲለው ታዋቂው ግሪካዊ ፈላስፋ አርስቶትል ደግሞ “የህግ የበላይነት ማለት ከማንኛውም ግለሰብ በላይ ነው ” በማለት ትርጉም ሰጥተውታል፡፡ በዚህ ትርጉም ውስጥ የሕግ የበላይነት ማለት ለሁሉም ሰው ጥቅም፤ክብር፤የሀገር ሉዓላዊነት ሲባል ሊከበር የሚችል የሀገር እና የዜጎቿ ዋስትና ነው ማለት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሀገራትን እና ዜጎቿን በወርድ እና ቁመት አይመዝንም፡፡ የሕግ የበላይነት መነሻው ሰው መሆን ብቻ ሲሆን መዳረሻው ደግሞ ሰብአዊነትን በልኩ ማስከበር ነው፡፡

የሕግ የበላይነት እንዴት ሊከበር ይችላል?

የሕግ የበላይነት ለሁሉም ጥቅም የተመሰረተ ዓለም ቀፋዊ የሕግ ልዕልና ምሰሶ እስከሆነ ድረስ መጠኑ እና የስራ ድርሻው ይለያይ እንጅ የማስከበር ግዴታ የሁሉም  ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ለማስከበር ዜጎችም ሆነ የመንግስት አካላት ህግን ሊያውቁ፣ ሊረዱ፣ ሊማሩ፣ሊተገብሩ ይገባል፡፡

ይህ ከአንድ የሰለጠነ ህዝብ የሚጠበቅ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ተፈርቶ ሊከበር አይገባም፡፡ ሕግ ማክበር አንዱ የግብረ ገብ ግዴታና የመልካም ዜጋ መገለጫ ነው፡፡ ሕግን ሲመቸኝ አከብረዋለሁ፤ ሳይመቸኝ እጥሰዋለሁ የሚል አመለካከት ትክክል አይደለም፡፡ በፍርሐት ብቻ ሕግን ማክበር ግን በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ስለሆነ አጋጣሚው ሲገኝ ሕጉ ስለማይከበር ለማሕበረሰብ አደገኛ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ስለሕግና ፍትሕ በጎ አመለካከት መኖሩ ለሕግ መከበር ቀዳሚ ሁኔታ ነው፡፡ ዜጎች የፍትህን ጥቅም ልናውቅ ልንጠይቅ ይገባል፡፡ ካላወቅን እንዴት ነው መንግስትንስ ልንተች የሚገባን? የሕግ የበላይነት በአንድ ሀገር ውስጥ መንግስት እና እያንዳንዱ ዜጋ ድርሻውን ሲያውቅ መንግስት የሙያ ስራ ህዝብ ደግሞ የደጋፊነት የጠቋሚነት፤የአዋቂ ተችነት፤ጥሩ ሲሰራም አመስጋኝነት  እና በህግ ማስከበር ሂደት የራስን ድርሻ መወጣት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

የህግ የበላይነትን ማን ያስከብር?

የህግ የበላይነት ማስከበር ማለት ከህግ በላይ በመሆን የአንድ ሀገር መንግስት ያወጣውን ሕግ በመተላለፍ በመንግስትም ሆነ በዜጎች አካል፤ሕይወት፤እና ንብረት መብት ላይ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን የሚፈጽምን ሰው ወይም አካል በህግ አግባብ ስርዓት ማስያዝ ማለት ነው፡፡ይህን ለማድረግ ህግ መማርን፤ማወቅን ያወቀ ስለመሆኑም ከሚመለከተው አካል ማረጋገጫ ማግኘትን ይጠይቃል፡፡

ሕግ የሕግ የበላይነት በማን መከበር እንዳለበት እራሱ መድሃኒት አለው፡፡ የሕግ መድሀኒቱ ህግ ነውና፡፡ በዚህም መሰረት በአንድ ሀገር ውስጥየህግ የበላይነትን ማን ያስከብር የሚለውን በተመለከተ የህግ አውጭ የተባለ የመንግስት አንድ አካል ለሌላው ሕግን ለማስፈጸም ስልጣን ላለው አካል በግልጽ ህግ ሃላፊነቱን ቆጥሮ ይሰጠዋል፡፡ የእኛ ሀገር ሕግም ሕግን ለማስከበር ስልጣን የተሰጣቸው የፍትህ እና የጸጥታ ተቋማት ማለትም ፖሊስ ፤ፍትህ ጽ/ቤት፤ፍርድ ቤት፤እና የመሳሰሉት ተቋማት በየደረጃቸው እና ስልጣናቸው እንጅ ህዝብ ሆ ብሎ ወጥቶ ምርመራ ያካሂድ፤ክስ ይመስርት ፍርድ ይስጥ አይልም፡፡

እነዚህ ተቋማት አንድን ሰው እና ድርጊት ከመጠርጠር አንስቶ እስከ እርምጃ አወሳሰድ እንዴት ሊያስተናግድ እንደሚገባ በህግ አግባብ ሊሰሩ ሃላፊነት የተጣለባቸው ናቸው፡፡ ህዝብ ሆይ በእሩቅ ጥርጣሬ እራሳችንን ዳኛ አድርገን የምንጠላውን ስርዓት አሳልፈን ልንሰጥ አይገባም፡፡ የእኛ ድርሻ ምንድን እንደሆነ ልናውቅ ይገባል፡፡ ይህ ድርጊት ህገ-ወጥ ነው? ወይስ አይደለም? ለማለት የሚመዝን ህግን የሚያውቅ አዕምሮ፤የሚመረምር ልቦና፤ይህን ለማስፈጸምስ ሃላፊነቱ የሚወስድ ትውልድ በሀገራችን እስካልተገነባ ድረስ የራሳችንን መብት ጠያቂዎች የሰው መብት በማናለብኝነት እረጋጮች እየሆንን ስለሆነ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ ሕዝብ ሲሳሳት ሊመከር ይገባል፡፡ ያለድርሻው ዘሎ እየገባ ታሪክ ይቅር የማይለው አሳፋሪ ድርጊት መስራታችንን ማቆም አለብን፡፡

የህግ የበላይነት በሀገራችን ምን ድርሻ ሊኖረው ይገባል?

አምና አምና ነው፡፡ትላንት ትላንት ነው፡፡ሻል ቢል መደሰት ሲከፋ ደግሞ ከመጸጸት ምንም የማናተርፍበት ጊዜ ነው፡፡ አምና፡፡ ነገ ግን ነገ ነው፡፡ነገ የሚሰራ ሃሳብ አለው፡፡አሳቢ እና አልሞ አድራጊ ተግባሪ አእምሮ ይፈልጋል፡፡ እኛነታችንን በአምናነት ስንረዳው አምና መልካም ነገሮችን የሰራንበት ቢሆንም ከእኛ የማይጠበቅ አሳዛኝ ስራዎችንም የሰራንበት ዓመት ነው፡፡እኛ በኢኮኖሚም ብቻ ሳይሆን በመብት መከበርም ሆነ ማስከበር ድህነት እና ድህነት ወለድ በሽታዎች የተጠናወተን ህዝቦች ነን፡፡ ይህ አንድም የእውቀት ችግር ነው በሌላም በኩል የክፋት ውጤትም ነው፡፡ በራሳችን ህገ-መንግስት አንቀጽ 8 ላይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ሁነን እያለ የተሰጠንን ስልጣን በእውነት ስለ ሀገራችን እና ልጆቿ ስንል ጥንቁቅ አዋቂዎች እና ነቅ ነቃሾች ሆነን መንግስትን ካልፈለግነው በካርድ የምንዘርር ሞገደኞች ልንሆን ይገባል፡፡የራስን መብት ሳያውቁ፤መብት በልመና የሚገኝ ምጽዋት እንዲሆን የምንፈልግ አሳዛኝ ህዝቦች መሆናችንን ልናስወገድ ይገባል፡፡

በእኛ ሀገር አንድ ልብ ያላልነው ነገር “የኢትዮጵያ ሕዝብ የዋህ እና ጭዋ ነው” የሚል ተረት ነው፡፡ ለመሆኑ ጨዋነት በንግድ አለም መስረቅ ነው?ጨዋነት ካለ የሚሰርቅ አመራር የት መጣ? ማን ወለደው? ማን አሳደገው? የማንን ባህሪ ይዞ አድጎ ነው የሚሰርቅ? ጨዋ ከሆንን ጀሶ ጤፍ ነው ብለን የምንጋግር እኛ ማነን? ጨዋነት ካለ ከእኔ ብሄር ውጭ፤ከእኔ ሃይማኖት ውጭ ላሳር የምንል ለምንድን ነው? ሌባ ዳኛ ካለ ከዚህ ህዝብ የወጣ ነው፡፡ ሌባ መሃንዲስ ከዚህ ህዝብ የወጣ ነው፡፡ የእኔ ፖለቲካ ብቻ ነው ጀግና እኔን የሚቃወም ጸረ-ሰላም ነው የምንል ሰዎች እንዴት ነው ጨዋ በሚባል ቃል ልንቆለጳጰስ የሚገባን? ልጆቻችን ሩጠው ሲያሸንፉ እኛ እንዲህ ነን የምንል ነገር ግን ከደጃችን መጥፎ ድርጊት ሲፈጸም “እኛን አይወክለንም!” የምንል እኛ ማነን? በእውነት በአረጀ አበባል ዘመን ልንሻገር አይገባም፡፡ የተፈጠሮ ሃብቱ በተትርፈረፈበት፤የስራ ፈጠራ ሞልቶ በተረፈበት ሀገር ወስጥ ሆነን መንግስትን እላፊ እና አሳፋሪ ጥያቄ መጠየቅም አግባብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እኛ ከመጀመሪያው ሃላፊነታችን ሳንወጣ ሌላውን ለምን እናኮስሳለን፡፡ ሃያ አራት ሰአት ሙሉ ተኝቶ በአንድ እጁ ጫት የሞላ ፔስታል በአንድ እጅ ሊወልቅ የተዝረከረከውን ሱሪ ይዞ የሚውልን ወጣት እንዴት ነው ሀገሬ ልትሸከም የሚገባው? ይህ ወጣት የአማራ ወይም የኦሮሞ ብሄርተኛ ነኝ ቢለኝ የታባቱ አውቀዋለሁና? አማራነት አርቆ አስተዋይ ኦሮሞነት የመመካር እሴት ያለው እንጅ በዘፈቀደ የሚመራ እንዳልሆነ ሊያውቅ ይገባል፡፡

በመጨረሻም ሁሉም የመንግስት ተቋማት ለህግ የበላይነት ያላቸውን ክብር ሊያሳዩበት የሚችሉበት ሊሆን ይገባል፡፡ቢሮህ አንድ ጉዳይ እንድትፈጽምልኝ መጥቸ በህገ-ወጥ መንገድ ብታስተናግደኝ አንተ ተደማሪ ሳይሆን በታኝ ነህ፡፡ ስለሆነም ሁላችንም በሀገራችን የሕግ የበላይነት እንዲከበር ተግተን የምንሰራበት በሃላፊነት ደረጃም መጀመሪያ እራሳችንን የምናይበት ዓመት እንዲሆን እንድንሰራ ፈጣሪ በረከቱን ያድለን፡፡

የሕግ የበላይነት የተከበረባት ሃገር የምነገነባበት ዘመን ይሁንልኝ፡፡ከጣና ዳር ድጋሚ እመለሳለሁ፡፡ቸር እንሰንብት

Filed in: Amharic