>

ህወሀት ያልፋል፡ የትግራይ ህዝብ ግን ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ይኖራል!! (መሳይ መኮንን)

ህወሀት ያልፋል፡ የትግራይ ህዝብ ግን ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ይኖራል!!
መሳይ መኮንን
 
በህወሀት መዝገብ ኢትዮጵያ ለህወሀት ትኖራለች እንጂ ህወሀት ለኢትዮጵያ አይኖርም። በህወሀት መዝገብ ኢትዮጵያ የህወሀት ንብረት ናት። ኢትዮጵያ የምትኖረው የህወሀት ህልውና እስከተጠበቀ ድረስ ብቻ ነው። የህወሀቶች የአእምሮ ስሪት በዚህ አመለካከት ላይ የተዋቀረ ነው!!!
ዝም ብሎ መሞትም ያባት ነው። ህወሀቶች በመጨረሻው ሰዓትም እየለፈለፉ፡  እየቀጠፉ ይህቺን ዓለም መሰናበትን መርጠዋል። ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ፡ ሀገሪቱን የዓለም ጭራ አድርገው፡ ለመሰማት ጆሮን የሚያምሙ ሰብዓዊ ጥፋቶች ፈጽመው፡ ሀገር በቁም ገድለው፡ ሁለት ትውልድ አበላሽተው በመጨረሻው ሰዓት ንሰሀ ይገባሉ፡ አሟሟታቸውንም ያሳምራሉ ብለን ጠብቀን ነበር። ከሰሞኑ የህወሀት አንዳንድ መሪዎች፡ ልሂቃኖቻቸውና የፌስቡክ ሰራዊታቸው ይዘው የተነሱት ትርክት ግምታችንን ዜሮ አስገብቶታል። በራሳችን ዘመን የተፈጠረውን፡ በዓይናችን ስር የተደረገውን፡ ሰለባ የሆነው ሀገርና ህዝብ በህይወት እያለ ጻድቅ ነበርን፡ ለውለታችን ምስጋና ሲገባን ወቀሳ ምን ባጠፋን? ብለው ተነስተዋል።
ኤል ቲቪ ለህወሀቱ ጌታቸው ረዳ ያደረገውን ቃለመጠይቅ በተመለከተ ለቅምሻ ያቀበለንን አንድ ክሊፕ ተመለከትኩት። እነስብሃት ነጋ መንደር ተጠግቶ ከአዛውንቶቹ ህወሀቶች አፍ ሀሜትና አሽሙር እየሰበሰበ የሚጽፍልንን አንድ የህወሀት ቀንደኛ የፌስቡክ አዝማች ሰሞኑን የከተበውን ጽሁፍ አነበብኩት። በተለያዩ ሚዲያዎች የህወሀት ደጋፊዎች የሚሰጡትንም አስተያየትና መልዕክት አዳመጥኩት። እዚህም እዚያም በህወሀቶች ሰፈር ምን እየተባለ ነው የሚለውንም ለመቃረም ሞከርኩ። እኛና እነሱ ተለያይተናል። ከሁለት አንዳችን ተሳስተናል። ወይ እነሱ ልክ ነበሩ፡ ወይም እኛ አልተረዳናቸውም፡ አልያም የሆነ ነገር ሆነናል። ከእነስብሃት ነጋ ጋር ውስኪ እየላፈ፡ ወሬ ለቅሞ የሚነግረን አፈቀላጤያቸው ሰሞኑን የጻፈውን አንዳንድ ነገሮች ላንሳ።
”እንደ ድርጅት ከተመዘነ በሙስና ኣመለካከትና ተግባር በኣንፃራዊነት ህወሓት ከሌሎች የኢህኣዴግ ኣባልና ኣጋር ድርጅቶች የተሻለ ነው የሚል ስሜት ኣለኝ።” ይሄን መልዕክት ከማንበብዎ በፊት የልብ ድካም ችግር እንደሌብዎት እርግጠኛ ይሁኑ። ደም ግፊት፡ የሚጥል በሽታም ካለብዎት ይህን መልዕክት ባያነቡ ይመረጣል። እንግዲህ ህወሀቶች የሚያስቡት እንዲህ ነው። ለ27 ዓመታት ሀገር በአንድ ብሄር የተደራጀ የማፊያ ኢኮኖሚ መስርተው በብቸኝነት ሲግጡና ሲዘርፉ ከርመው የእነሱን ትርፍራፊና እንጥብጣቢ ኪሳቸው የወሸቁ የሌሎች ብሄር ተወላጆችን ተጠያቂ አድርገው መጥተዋልና እስኪ እንስማቸው። የጆሮ ግድግዳችን እንዳይበጠስ ብቻ እንጠንቀቅ። ህወህቶች ይናገራሉ። እንቀጥል።
” የቲም ለማ አካሄድ የኦሮሞ ሃይል ስልጣን ላይ ካልወጣ ኣገሪቱን ግጭት ውስጥ እናስገባታል: በውጤቱም ትፈረካከሳለች የሚል ነበር። ያኔ የህወሓት ኣመራር ወደ መድረክ ከመሄድ ይልቅ መላተሙን ቢያከረው ኖሮ ኣገሪቱ ወደማትወጣበት ኣዘቅትና መበታተን በገባች ነበር።” እንግዲህ ይህን የሚሉ ሀገሪቱን በ21ኛው ክፍለዘመን ባህር አልባ አድርገው፡ በከፍተኛ የሀገር ክህደት ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉ አያሌ ወንጀሎችን የፈጸሙት ህወህቶች ናቸው። እነሱ ለኢትዮጵያ ተቆርቁረው፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያን ከጨለማ መንጭቀው ያወጡትንና የተስፋ ብርሃን እንድናይ ያደረጉትን የለውጥ ሃይሎች ደግሞ በሀገር አጥፊነት ፈርጀው እየከሰሱ ነው። የሚያስገርመው ይሄን የሚነግሩን ለእኛው መሆኑ ነው። በእነሱ የዘረኝነት ፖሊሲ ስቃይ መከራ ለተሸከምን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን። እንኳን በዚህ የኢትዮጵያ የተስፋ ዘመን ይቅርና በእናንተ የክፋት ዓመታትም ኢትዮጵያ አልፈረሰችም። ምናለ ዝም ቢሉ?!
እንቀጥል። ”የህወሓት ኣመራር ከራስ ክብር በላይ የኣገር ኣንድነትና ቀጣይነት ኣስቀድሟል ነው። ይኸን የህወሓት ኣመራር ውሳኔ በክብር ልንቀበለው ይገባል እንጂ ከዚህ በላይ ውርደት እንዲደርስባቸው ኣንፈቅድም።” አጃኢብ ነው።
 አንድ ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ የተናገሩትን አስታወሰኝ። የመያዶች ህግ በወጣ ሰሞን የውጭ ድርጅቶችን ከሀገር ውስጥ ጠራርገው ካባረሩ በኋላ የተቀሩትን ሰብስበው ‘‘ ድርጅቴ አደጋ ውስጥ ወድቋል። ከገደል አፋፍ ተጠግቷል። ድርጅቴን ለማዳን የትኛውንም እርምጃ እወስዳለሁ።” ልክ ነበሩ። ከሀገር ይልቅ በድርጅታዊ ፍቅር የተለከፉት እሳቸውና ተከታዮቻቸው ማለት ያለባቸውን ቢሉ አይደንቅም። በወቅቱ እሳቸው በወሰዱት እርምጃ ድርጅታቸው ለጊዜው ተርፏል። ኢትዮጵያ ግን  በቀላሉ እንዳትንሰራራ ሆና ክፉኛ ተጎድታለች።
ኢትዮጵያን ለብርቱ የህልውና አደጋ አሳልፎ የሰጣትና በጎሳ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝምን የፈቀደውን ህገመንግስት(የህወሀት ፕሮግራም) ያረቀቁ ጊዜ እንደአምላክ ይሰግዱላቸው ለነበሩት ለአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ረቂቁን ያሳዩት አቶ መለስ ዜናዊ ” ከዚህ ውጪ ምርጫ የለኝም። ድርጅቴ በማዕከላዊ መንግስት ለረጅም ጊዜ በስልጣን እንዲቆይ ከፈለግን ኢትዮጵያን በብሄር ፖለቲካ መምራት ውጪ ሌላው ተመራጭ አይደለም”ማለታቸውን ከራሳቸው ከአቶ ኢሳያስ አንደበት ሰምቼአለሁ።
በህወሀት መዝገብ ኢትዮጵያ ለህወሀት ትኖራለች እንጂ ህወሀት ለኢትዮጵያ አይኖርም። በህወሀት መዝገብ ኢትዮጵያ የህወሀት ንብረት ናት። ኢትዮጵያ የምትኖረው የህወሀት ህልውና እስከተጠበቀ ድረስ ብቻ ነው። የህወሀቶች የአእምሮ ስሪት በዚህ አመለካከት ላይ የተዋቀረ ነው። ዛሬ ጉልበት ሲከዳና ቀን ሲጨልም ” የህወሓት ኣመራር ከራስ ክብር በላይ የኣገር ኣንድነትና ቀጣይነት ኣስቀድሟል ነው።” የሚል ዜማ ማቀንቀን ራስን ከማሞኘት ያለፈ ትርጉም የለውም።
አቶ ጌታቸው ረዳም ከአዲስ ነጠላ ዲስኩር ጋር ሰሞኑን እንሰማቸዋለን። ለቅምሻ በተለቀቀው አጭር የቪዲዮ ክሊፕ ላይ በጋዜጠኛዋ ”ላጠፋችሁት፡ ለገደላችሁት፡ ለዘረፋችሁት ይቅርታ አትጠይቁም?” የሚል ዓይነት ጥያቄ ሲቀርብላቸው ” እኛ ጦርነት ላይ ነን። እያንዳንዷ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረችውን ችግር ከትግራይ፣ ከህወሓት ጋር ከሚያያዝ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ጋር ነው ጦርነታችን። ፌደራል ስርዓቱ አፈርሳለው፣ አሳያችኋለው እያለ በየሰፈሩ ከሚፎክር ትምክህተኛ ጋር ነው ጦርነታችን።” ብለው መልስ ሰጡ። ይህን ከየትኛው የእብደት አይነት ጋር እንደምንመድበው ግራ የሚያጋባ ነው።
ሲጀምር ህወሀት ብቻ ሲዘርፍ ሲገድል አንድ ሀገር በቁሟ ሲግጥ ስለነበር ከህወሀት እኩል የሚጠየቅ አይኖርም። የ27ዓመቱ ስርዓት ህወሀት ያዋቀረው፡ በአንድ አካባቢ ተወላጆች ፍጹም የበላይነት የተያዘ በመሆኑ በዘመኑ ለተፈጸመው ወንጀል ሁሉ ተጠያቂው ህወሀትና ህወሀት ብቻ ነው።
 ሌላውም እንደወንጀሉ ዓይነት በግለሰብ ደረጃ ሊጠይቅ ይችላል። ሆኖም ህወሀት እንደቡድን የአስከፊው ዘመን ተጠያቂ ሆኖ ለታሪክ ፍርድ ቀርቧል። ቅጣቱንም እየተቀበለ ነው። አሳፋሪና ሰቅጣጭ ወንጀሎቹ በአደባባይ እየተጋለጡ ነው። የምን ጦርነት ነው አቶ ጌታቸው? በምን አቅም የሚገጥሙት ጦርነት? በጦርነት ለማሸነፍ አንዱ ስንቅና ትጥቅ እውነት ነውና እውነትን ይፈልጉ።
ህወሀቶች ሰሞኑን የጀመሯት ፈሊጥ የትግራይን ህዝብ የወንጀላቸው ተባባሪ እንዲመስል የሚያደርጉት አደገኛ ትርክት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ሀሙስ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ‘’የጥንት ሽፍቶች መሸሸጊያ ጫካ ነበር። ዛሬ ግን ጫካው አልቋልና መደበቂያቸውን ብሄር ወይም ጎሳ ለማድረግ ይኳትናሉ። ሲበሉ ዞር ብለው ያላዩትን ህዝቡ ሲያዙ ይፈልጉታል።’’ ብለው ነበር። ህወሀቶች የትግራይን ህዝብ እንደጫካ ሊጠቀሙት ከምንጊዜውም በላይ እየተንቀሳቀሰ ነው። ህወሀትን መንካት የትግራይን ህዝብ መንካት ነው የሚለውን የከሰረ ትርክት ዳግም እያቀነቀኑት ነው።
 በፊት ህወሀት ከሌለ ኢትዮጵያ አትኖርም የሚለው የህወሀቶች መፈክር ኢትዮጵያ ከእነሱም በኋላ በተስፋ ቆማ ሲያይዋት ተገለበጡና ህወሀት ከሌለ የትግራይ ህዝብ ያከትምለታል የሚል አጀንዳ ቀርጸው እያራገቡ ነው። የእነ ስብሃት ነጋ ሌላኛው አፈቀላጤ ሰሞኑን የጻፈው ይሄንኑ ነው። የህወሀትን መዳከም ማመን ያቃተው አፈቀላጤው ”የትግራይ መዳከም እየመጣ ነው። የምስራቅ ኣፍሪካ የህዝብ ልዕልና ፖለቲካ መዲና የሆነችው ትግራይ ከተዳከመች መዘዙ ለአፍሪካም ጭምር የሚተርፍ ነው” እያለ ነው። ጆሮ መቼም ይሄን ሰማሁ ብሎ አይታመምም እንጂ ነገሩ ከባድ ይሆን ነበር።
የትግራይ ህዝብ ትልቅ ሃላፊነት ከፊቱ ተደቅኗል። ሲዘርፉ ዞር በልው ያላዩት ህወሀቶች በወንጀል ሲፈለጉ ጫማው ስር ለመግባት ጉዞ መጀመራቸውን ማስተዋል አለበት። ወንጀል ብሄር የለውም። ህወሀቶች ሀገር ሲያጠፉና ህዝብ ሲገድሉ የትግራይ ህዝብ ውክልና ሰጥቷቸው አልነበረም። ዛሬ ለፈጸሙት ሃጢያት ዋጋ በሚከፍሉበት ጊዜ የትግራይን ህዝብ ተንጠልጥለው አብረው ለመውደቅ የሚያደርጉትን ሙከራ ማክሸፍ ከማንም በላይ የሚጠበቀው ከትግራይ ህዝብ ነው።
የህወሀት ጸሀይ እየጠለቀ ነው። ህወሀት በታሪክ ገጽ ላይ ከጥቁር ገጽታው ጋር ተከትቦ የሚሰናበትበት ዋዜማ ላይ ነው። የህወሀት መዳከም የትግራይ ህዝብ መጠናከር ነው። የህወሀት ውርደት ለትግራይ ህዝብ ክብር ነው። የህወሀት ሞት ለትግራይ ህዝብ ህይወት ነው። ህወሀት ያልፋል፡ የትግራይ ህዝብ ግን ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ይኖራል።
Filed in: Amharic