>

የእማማ ቀልድና ጦርነቱ! (ደረጄ ደስታ)

የእማማ ቀልድና ጦርነቱ!
ደረጄ ደስታ
እኛ ጨርሶ አልሰረቅንም አልገደልንም ብሎ መከራከሩ ቀርቶ፣ እነ እገሌ እነገሌም አሉበት፣ ብቻችንን አልሰረቅንም፣ እሚሉት ነገር፣ ዋና  መከራከሪያ ሆኖ መቅረቡ እየገረመኝ ነው።
በሥልጣን እኩል ባንሆንም፣ በወንጀሉ ተጠያቂነት ግን ውሃ ከታች ወደላይ መፍሰስ አለበት ሲባልም እየታዘብን ነው። አሁን ደግሞ ነገር አድጎ ተጠምዝዞ የወሬ ጦር ተመዞ  ያ ህዝብና ያ ድርጅት አንድ አይደሉም። ይሄ እዚያ ህዝብ ላይ የታወጀ ጦርነት ነው… ዓይነት ንግግር እየበዛ ነው። ምንም ጥያቄ የለውም ሐቅ ነው “ድርጅቱና ህዝቡ አንድ ነው” ብለው በከንቱ እሚከሱ ሰዎች እሉ። የነዚህ ሰዎች ብዛትና “ድርጅታችንና ህዝባችን አንድ ነው” በሚሉት ከንቱ ሰዎች መካከል ያለው ቁጥር ተመሳሳይ ነው ማለት ቢቸግረንም፣ ሁለቱም እዚያው በዚያው “በአንድ ነን – አንድ ናችሁ” ጨዋታቸው መነታረካቸው የሰነበተና መቸም እማይቀር ነገር ነው። ግን ያንን ተገን አድርጎ፣ ድርጅቴን በተናገራችሁ ቁጥር ህዝቤን ተናግራችኋል፣ እሚለው ማስፈራሪያ ሁላችንንም አፍኖ መግደል የለበትም። ጭራሽ ጦርነት?! ጉድኮ ነው። ጨዋታችንም እንደገንዘባችን እየተቀማ፣ “ ሰላምና ህዝባዊ አንድነት ይሻለናል” እሚለው ብልጠት ግን አያደናግረንም። ይህን እያሰብኩ አንድ ወዳጄ የነገረኝ የእማማይቱ ቀልድ ትዝ አለኝ። ከአንድ ወዳጃቸው ጋር ሲያወሩ.. “ምንም ጤናም የለኝ ያመኛል..!” አይነት ነገር ተናግረው ነበር መሰለኝ። እና ሰውየው – “እማማ እግዜር ይማርዎ!” አላቸው በጨዋታ መካከል “አሜን!” አሉ። አሁን ትንሽ እያወሩ እንደቆዩ አሁንም መልሶ ደገመና እግዜር ይማርዎት አላቸው። አሜን ብለው ቀጠሉ። ቆየት ብሎ ደሞ ለሶስተኛ ጊዜ እግዜር ይማርዎት ሲላቸው። እማማ ምርር አላቸውና “ምነው ልጄ ደጋገምከውሳ። እሱ (እግዜር) እሺ ብሎ እኔ እንቢ ያልኩ አስመሰልከውኮ!” አሉት ይባላል።
እና ደጋግማችሁ የማንትስ ህዝብና ማንትስ አንድ አይደለም እያላችሁ በቀን አስራ አምስት ጊዜ ለምን ትነግሩናላችሁ። ጎሰኝነትና ጠላትነት ቀርቶ ህዝባዊ አንድነትና ብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል እያላችሁ ለምን ትጨቀጭቁናላችሁ? ህገመንግሥቱ ይከበር! ወንጀለኞቹ ለፍርድ ይቅረቡ! ሌቦች ይታቀቡ!… እያላችሁ… እረ ተው ባካችሁ!! እናንተ እሺ ብላችሁ እኛ እምቢ ያልን አሰመሰላችሁት እኮ!
Filed in: Amharic