>
10:07 am - Sunday May 22, 2022

የብርቱካን እዳ!  (ደረጄ ደስታ)

የብርቱካን እዳ! 
ደረጄ ደስታ
ዳኛዪቱ ዳኛ ሆነች። ብርትኳን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ሆና እየተሰየመች ነው። እንግዲህ ለምርጫችን ዳኝነት ልትቀመጥ ነው። ግን አሁን ጥያቄው ማንን ነው የምንመርጠው እሚለው ነው? መቸም አብይን ደገፍናቸው እንጂ አልመረጥናችውም። መርጠናቸዋል ብንልም ከኢህአዲጎቹ መካከል እንጂ ከኛዎቹ መካከል አይደለም። ኢህአዴጎችና ኢህአዴግን ጠልተን አብይን ወደን መከራችንን እምናይ በርካቶች ነን። በሚቀጥለው ምርጫ የራሳችን ድርጅትና መሪዎች  ከሌሉን ኢህአዴግ ማሸነፉ የጠቅላይ ሚንስትራችን ስም ርቆ መንሳፈፉ አይቀርም። ነጻ ምርጫ ነው እንጂ የሌለው መሪማ ሞልቶ ተርፏል ማለት ብቻውን አይሠራም። የተበታተነና በቅጡ ያልተደራጀ መሪ አሸናፊ ድርጅት አይወጣውም። በዚያ ላይ በዚህ አያያዛቸው አብይን ራሳቸውን መልሰን መላልሰን እምንመርጠም እንኖራለን። ዋናው ነገር መቸም በምርጫው ሐቅን ፍትህና ዳኝነት እንድታደላድል እንጂ ብርትኳንን የፈልግናት ለተቃዋሚዎች እንድታደላ አይደለም። ደግሞ በሷ እንዳናሳብብ ! መንግሥትም እንደልማዱ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም ካለ ልጅቷ በወዲያና ወዲህ እዳ መግባቷ ነው። የዛሬ ሰባት ዓመት በዘ ኢትዮጵያ ጋዜጣ የጻፍነው ያንኑ ዓይነት ስጋት ነበር።  ከዚህ በታች ያለው ይገኝበታል-
…ብርቱካንን ለመቀበል ብዙ ሰው ቤቷ ድረስ ሄዶ ነበር። ፕሮፌሰር መስፍን ዶ/ር ነጋሶ አቶ ስዬ አብርሃ ኢንጂነር ግዛቸውን ጨምሮ ብዙ የፖለቲካ ሰዎች ነበሩ። ድርጅቷን እንደቅርጫ ተከፋፍለው፣ በነገር ታስረው ሲባሉ የከረሙት ፖለቲከኞች፣ በመፈታቷ የተፈቱ “ሆነው” ቤቷ ተገኙ። ባይከፋፈሉ ናሮ አንድነት የተባለው ድርጅቷን ሁለት ቦታ አይከፍሉትም ። ጠንክረውና አገር አስተባብረው የአፈታቷንም መልክ ሌላ ገጽታ ባስያዙት ነበር። ወይ ከምርጫው ወይ ከእርግጫው ሳይሆኑ ነገሩን ሁሉ እንዲህ ካበለሻሹት በኋላ አሁን ደግሞ እሷን ለሁለት ለመክፈል የየአንጻራቸውን ሤራ እያንሾኳሾኩባት ይመስላል። ከእስር ቤት ወጥታ እንኳ ማረፊያ ድርጅት ያሳጧት እነዚህ ሰዎች በፊቷ እየተሳሳቁ ሲያወሩ ፍቅር ያላቸው ይመስላሉ።
እሷም የዋዛ አይደለችምና “ፖለቲካውን ለመቀጠል ሁኔታዎችን እስካጠና ድረስ ትንሽ ጊዜ እወስዳለሁ” ብላለች። ጊዜው ምን ያህል እንደሆነ ማሰብ የማይቀር ቢሆንም ማጠደፉም የሚሆን አይደለም። በሌላም በኩል ጽናቷ የሚደነቅ ቢሆንም አመራሯ የሚናፈቅ እንደ አስፈላጊነቱም የሚጠየቅ መሆን ይኖርበታል። ሁሉንም ነገር ከሷ ጋር ብቻ አቆራኝቶ ነገር ዞር ያለ እንደሆን የዓለም መጨረሻ አድርጎ ከመሸበር እንቁላሎችን ሁሉ አንድ ቅርጫት (ብርቱካን) ውስጥ ብቻ መክተት አደጋ አለው። መሪያችን! ጀግና! ማንዴላ… የተባሉ ብዙ ሰዎቻችን እየመጡ ሄዳዋል። ይህ ደግሞ አንድም ለኛ አንድም ደግሞ አብዝተን ለምናስጨንቃት ብርቱካን ሚደቅሳ ጥሩ አይደለም። ድክመቷን ስንፈቅድ፣ ልጅነቷን ስናስተውል፣ የደረሰባትን ግፍ ሁሉ ስናስብላት፣ የተሰጣትንም ማስፈራሪያና ስውር ማስጠንቀቂያ…ስንገምት ትንሽ ለቀቅ እናደርጋታለን። በተመለደው ጭካኔያችን (ድሮም እኮ እሷ…እያልን) ነገ አውርደን ከምንፈጠፍጣት ጀግናም ብትሆን ሰው መሆኗን አውቀን ልንጠነቀቅላት ይገባናል። አይዞሽ ብለናት ከድቅድቅ ጨለማ አስጥለናት ተኝተን ያደርን ሰዎች “እንዲህ ብታደርግ እንዲያ ባታደርግ” ከሚል ስሜት አልባ ወሬ ፈቀቅ ብንል ጥሩ ነው። “መለስን ፈርቶ ብርትኳንን” እንዳይሆን ትችቱን አነስ ውዳሴውን ቀነስ ማድረግ ያስፈልገናል። ከእስር ወጥታ እስር እንዳትገባ ነጻነቷን እንስጣት! እስኪ ፀሐይቱንም ትንሽ አይታ ትጠግብ! (zethiopia)
(እና ዘንድሮም እስኪ እሷም ለሹመት ኃላፊነቱ ትንሽ ፋታ ታግኝና እሚሆነውን ብቻ ሳይሆን እኛም እምናደርገውን እንይ ለማለት ነው)
Filed in: Amharic