>
6:59 am - Tuesday December 6, 2022

የጃዋር ማስጠንቀቂያ (ደረጀ ደስታ)

የጃዋር ማስጠንቀቂያ

 

ደረጀ ደስታ

 

“ታች ያለው አመራር ተሽመድምዷል” በሚል ርዕስ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ የጃዋር መሃመድን ቃለጠመጠይቅ ይዞ መውጣቱን አነበበኩ። ጃዋር አስረግጦ የተናገረውን አስረግጨ እንደሰማሁት ገዢው ፓርቲም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግሥት አገሪቱን ማስተዳደር አልቻለም። አለመቻልም ብቻ ሳይሆን በዚህ አካሄዱ ወደፊትም አይችልም። ይህ የጅዋር ማስጠንቀቂያ አስግቶኛል። ሁለት አገር የሌለው ሰው መቸም በአንዲት አገሩ ጉዳይ ራሱ ይጠነቀቃል ይጨነቃል እንጂ ሌላውን ሰው አያስጠነቅቅም። ስለዚህ በጅዋር አነጋገር መጨነቄ አልቀረም። እንዲህ አለ ጃዋር-

እቅጩን አስረግጨ የምናገረው ኢህአዴግ አሁን ባለው ሁኔታ አገር ማስተዳደር አይችልም። ከታች ያለው መዋቅር ፈርሷል። ስለዚህ ሕዝቡ ይህን የፈረሰ ሥርዓት እያየ ትዕግስት እያጣ በመሄድ ላይ ነው። መንግሥት ሊሰጠው የሚገባውን የደህንነት፣ የልማትና ሌሎች ነገሮችን መስራት አልቻለውም። የሚያስችለው አቅምም የለውም። እንደ ፖለቲካ ልሂቃኖች ሆነን ህዝቡ ጊዜ እንዲሰጠን ከፈለግን “ጊዜ ስጠን፣ ይኸው ቀነ ቀጠሯችን ራስህ በመረጥከው መንግሥት ትተዳደራለህ የሚለውን ማሳየት መቻል አለብን። ስለዚህ መፍትሔው አሶሳ ላይ አልያም ጊምቢ ላይ የለም። ወይም ደግሞ አላማጣ ላይ የለም። ችግሩ አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ስለዚህ የገዢው ፓርቲና የተፎካካሪ ፓርቲ አብረው ቁጭ ብለው ተደራድረው የሽግግር አቅጣጫ ካላስቀመጡ በቀር ወደ ከፍተኛ አደጋ ነው እየገባን ያለነው። ከታች ያለው የመንግስት አካል ተሸመድምዷል። ይህም ወደላይ እየመጣ ነው።

….ኢህአዴግ የሚሾማቸው ሰዎች የአቅምም የሞራል ብቃት የላቸውም። ስለዚህ ምርጫውን አካሂደን ከታች ወደላይ ህዝብ በመረጠው መዋቅር መስተዳደር እስካልተቻለ ድረስ የመንግሥት መፈረካከስና መውደቅ ይመጣል።

ጃዋር ከፊል አገሪቱን እየተዟዟረ በመሆኑ መሬት ያለውን እውነታ ያውቃል ብዬ እገምታለሁ። ማወቅ ብቻ ሳይሆን ከእውነታው ጋር ያለውን የራሱንም ግንኙነትና ድርሻም አሳምሮ ያውቃል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በዚህ መግለጫው ጃዋር ያስጠነቀቀው ወደላይ ብቻ ነው። መስጋትና መጨነቅና መለወጥ ያለባቸው ልሂቃኑና ባለሥልጣናቱ ብቻ ናቸው። ህዝቡ ምን ማድረግ እንዳለበት ከታች ያለው አልገዛም አሻፈረኝ ያለው ምን ማስተዋል እንደሚኖርበት እሱም ተጎጂም መሆን መቻሉን አልገለጠም። ሁለተኛ ለውጡ የመጣበትን ቅጽበት ሊገጥመው እሚችለውን ፈተናና ችግር ከማንም በላይ ቢያወቀውም ሁሉንም ነገር “አሁኑን” ባይ መስሏል። ለህዝቡ የተቆረጠ የጊዜ ሰሌዳ (የምርጫ) እንዲሰጠው ሲጠይቅም አሁን ባለበት ሁኔታ ምርጫ ቢገባ ማን ሊያሸነፍ ማን ድርጅታዊ ብቃት ኖሮት ከሥልጣን ሊወጣ እንደሚችል መገመቱ አይጠፋውም። እንዲያውም በዚህ የበለጠ ተደሳች ሊሆን እሚችለው ገዢው ፓርቲ መሆኑን አያጣውም። ለአንዳንድ አመጸኛ አካባቢዎችና ጥቂት ግለሰቦች ወንበር ብቻ ተብሎ የጠቅላላውን አገሪቱን ሁኔታ ለተቻኮለ የምርጫ ሥርዓት በመስጠት አብላጫውን አስረክቦ እንዲሁ አጨብጭቦ መቅረት መኖሩን ጅዋር ያውቃል።

ሁለተኛ “የታችኛው አመራር ፈርሷል”። ኢህዴግ ከታች መሠረት የለውም።” በማለት እንዳያስገብር አቅም የለውም ሥራ እንዳይሰጥ በጀት የለውም ዓይነት አገላለጽ ተጠቅሟል። እና የዚህ መፍትሔው ታቹ ላዩን እንዲያስገብር እንዲታጠቅ ነው ወይስ ታቹ በጀት ያፈራ ዘንድ እቁብ እንዲጥል ነው የተፈለገው? እዚህ ጋ ሁለት አከራካሪ ነገሮች ይኖራሉ። ለውጥ ከላይ ወደታች ነው ወይስ ከታች ወደላይ ነው መምጣት ያለበት? ቲዮሪው ወደሚጣፍጥበት ሊጣፍጥ ይችላል። ልምድና ታሪካችን እሚያሳየን ግን ምንድነው? በኢትዮጵያ እስከዛሬ የመጡ ለውጦች ከላይ ወደታች እንጂ ከታች ወደ ላይ (ከዳር ወደ ማዕከል ) ስለመምጣታቸው አናውቅም። ቢመጡም መጠናቀቂያቸው ማዕከላዊነት ነው ዳር ሆነው አልቀሩም። ላዩ እስካለ ታቹ የትም አይደርስም ቢሄድም የጊዜ ጉዳይ ነው። ላዩ ከፈረሰ ግን ታቹ ሲፈራርስ መቆሚያም የለውም። ዘመነ መሳፍንትን ማሰብ ነው። ለውጥን ከታች ወደላይ ለማምጣት እሚያስችል የምርጫ የውይይትና የመግባባት ባህል፣ የተጠያቂነትና አቅመ ህዝብን ገና አላዳበርንም። ልምዱም የለንም። በዚያ ላይ ተከፋፍለናል። እንኳን ከቀበሌ ልንነሳ ክልል ለክልል እንኳ የተስማማ ድምጽ ያለን አይመስለኝም። ለዛሬ ችግር የተዳረግነው ማዕከላዊነት በመዳከሙ ይሆን ወይስ ክልላዊነት በመስፋፋቱ ነው? ታቹን ያፈረሰው የማዕከሉ መዳከም እንጂ የታቹ መጠናከር አይመስለኝም። ታቹማ ጅዋር ራሱ እንደሚለው ተበትኗል። የተበተነ ራሱን አይሰበስብም። ሁሌም ሰብሳቢ ይሻል። በተሰበሰበ አገር ማዕከላዊ መሠረት በመገንባቱ ከታች ወደላይም ሆነ ቀበሌያዊ ተሳትፎ (የግራስ ሩት) ፖለቲካው ይሰራል። እኛ ስንበተንና ስንሰበሰብ በመኖራችን ዘላቂ መሠረቱን ገና አልጣልንም። የክልልና የማዕከል ሚዛን መጠበቁ ዋና ቁምነገር ሆኖ፣ ክልላዊነት በዝቶ የተዛነፈውን ማዕከላዊነት ወደሚዛኑ እየመለስን ታቹን ብናጠናክረውና ብናግዘው ይበጅ ይመስለኛል። እስክዚያው ግን የፖለቲካችን ክፋቱ ከአናት ከጭንቅላቱ ነውና ከላይ ወዳታች የተያዘው ለውጥ ጊዜውን እየጠበቅ ይወርድ ይመስለኛል። ሌሎችና ሌቦች የበተኗት አገር በጥበብ ትሰበሰባለች። አንዲት አገር ብቻ ላለን ሰዎች ሌላ ምርጫ የለንም። እግዜአር የተመሰገነ ይሁን አገራችን አንድናት እሷም ምንም አትሆን!

Filed in: Amharic