>

ቻይና በሰማይ ሲያሽ ዋለ! (አዛዡ ኢትዮጵያ ተቀምጦ ሳተላይቱ ከቻይና ይነሳል) ደረጄ ደስታ

ቻይና በሰማይ ሲያሽ ዋለ!

(አዛዡ ኢትዮጵያ ተቀምጦ ሳተላይቱ ከቻይና ይነሳል)
ደረጄ ደስታ
በመጪው መስከረም (September 2019) ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳተላይቷን ሽቅብ ወደ ጠፈር ለመላክ መወሰኗን አይአፍሪካን ዘግቧል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ዶ/ር ሰሎሞን በላይ እንደተናገሩት “ሳተላይቱ ሽቅብ እሚነሳው ከቻይና ሲሆን ማዘዣውና መቆጣጠሪያው ጣቢያ ደግሞ እሚሆነው ኢትዮጵያ ላይ ነው!”
የሳተላይቱ ፕሮጀክት ወደ 8 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል ተብሏል። ከዚያ ውስጥ 6 ሚሊዮን እሚሆነውን እምትሸፍነው ቻይና ናት። ሁለት ሚሊዮን ይዛ ከ6ቱ ሚሊዮን የተጠጋችው ኢትዮጵያ ከሳተላይቱ እምትጠቀመው ብዙ መሆኑን መገመት ይቻላል። የአገር ደህንነት ማስጠበቅን ጨምሮ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ቴሌቪዥን፣ የሰብል ምርት፣የአየር ትንበያ መረጃና ሌሎች አገልግሎቶችን ታከናውንበታለች። ከታች ያለውን ድህነት ከላይ ባለው ብልጽግና ቁልቁል እየተመለከተች ራሷን ትፈውስበታለች። ሀሳቡ ግሩምና ቅዱስ ነው።
በቻይናና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ውለታ ግን ማብራሪያ ይፈልጋል። ሳተላይቱ እሚነሳው ከቻይና ነው። ከገንዘቡም እሚበልጠው የቻይና ነው። ይህ ከሆነም ብድር ይሁን እርዳታ ምክንያቱ መገለጥ አለበት። ሳተላይት፣ ቴኮኖሎጂ ማቀላጠፊያ፣ ልማት ማስፋፊያ ብቻ ሳይሆን ሳር ቅጠሊቷን ሁሉ መመልከቻ ነው። ውሎ አድሮ የአገሬ ህዝብ ወደ ላይ አንጋጦ “እንግዲህ ቻይና አንቺ ታውቂያለሽ!” እንዳይል ማሰቡም አይከፋም።
ብድሩም ሆነ እርዳታው ያው ውለታ ነውና፣ ውለታው መልክ መልክ መያዝ ይኖርበት ይመስለኛል። ጥቅም ስናገኝ ምን ከፍለን ነው? ከሌሎች አገራትስ ቻይናን የመረጥነው ለምድነው? በሙያው ሊቅነት ባይጠበቅብንም ቢያንስ ቀለል ተደርጎ ቢብራራልን ጥሩ ነው። ኢትዮጵያ “ለምድር ወገብ ባላት ቅርበትና በጠራ ሰማይዋ ምክንያት ለጠፈር ምርምር አጓጊ በመሆንዋ” አገሮች ይፈልጓታል እየተባለ ሲሸለል ሰምቻለሁ። ግን አገራችን ቻይና ቻይና ብላ ልትሞት ሆነ። ውይይቱ ቻይናን በደፈናው መጥላትና መውደድ እየተደረገ ሳይነገር፣ ቢያንስ ላይ ላዩን እንኳ ማወቁ እሚደገፈውን ለመደገፍ እሚቀረፈውን ለመቅረፍ ይረዳ ይመስኛል። ምን ይመስላችኋል?
Filed in: Amharic