>

ሀሳብ ቫይረስ ነው - የቫይረሱ ተሸካሚ ሰው ነው?!? (ደረጀ ደስታ)

ሀሳብ ቫይረስ ነው – የቫይረሱ ተሸካሚ ሰው ነው?!?
ደረ ደስታ
እስኪ የሰውየውን ሀሳብ አመጣጥ ለማወቅ እንድችል ትንሽ የጀርባ ታሪኩን ስጠኝ ማለት ጥሩ ነው። ግን በሰበብና ፍረጃ አድቅቄና አጠፋው ዘንድ ማወደቂያውን አቀብለኝ ማለት ትልቅነት አይደለም። ወይም ለባለጌነቱ እንኳ ባለጌ ነው ግን የኛው የራሳችን ባለጌ ነው መባሉም አስተዋይነት አይደለም!!!
መቸም ሰው ስለሰው ያወራል እንጂ ስለ ጥጃ አናወራም። ዛፍን አናማውም። ድመትን አናሽሟጥጣትም። ለፍየል አናጨበጭብም። ለበረንዳ በግ አንሰግድም። ዝሆን የምንፈራበትና ሰው የምንፈራበት መንገድ የተለያየ ነው። እዚህ ቤት ክፉ ውሻ አለ (ተጠንቀቁ) የሚል ነገር ድሮ አጥርና በር ላይ ይለጠፍ ነበር። እዚህ ቤት ክፉ ሰው አለ ተብሎ ግን አይለጠፍም። ምክንያቱም የሰው ልጅ ሺ ቢከፋ ያው ሰው ነው! የቀን ጅብ እንኳ ቢሆን!
የሰው ልጅ እንኳን ነጽቶ ከፍቶም ቢሆን በሰውነቱ ይወራል። ቦንብ አፈንድቶ ሰው ፈጅቶ እጅ ከፍንጅ ተይዞ እንኳ “ በሽብር ተጠርጣሪው” ይባላል እንጂ “አሸባሪው” አይባልም። ስለጭካኔውማ ህጻናትን ከመረሸን ሌላ ምን ጭካኔ አለ? ግን በሰለጠነው ዓለም መጀመሪያ ፈጥኖ ወደ ህሊና እሚመጣው “ሰው በጤናው እንዲህ አያደርግም፣ አንድ ነገር ሆኖ መሆን አለበት…” ይባልና ይመረመራል። ሰውነት እንዲህ በቀላሉ አትሻርም። ከሞተ ሰው ደግሞ ያለ ሰው ይበልጣል። እርግጥ ነው አንዳንዴም – የሞተለሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ ይባላል። (ታዲያ የሞተማ ሞቷል ምኑን በላው ብለው ነበር ሀሳብ አገላባጩ አባት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም!)
ፍሬ ነገሩ ሀሳብ ብቻውን ወሬ አይሆንም ለማለት ነው።  ደግሞም አልሆነም። ሞክረነዋል። ሀሳብ ቫይረስ ነው። የቫይረሱ ተሸካሚ ሰው ነው። ሰው ማለት ከሀሳብ ጋር አብሮ የሚኖር ፍጡር ነው። ለሀሳብ ስንል ሰዎችን እናመጣቸዋለን እንጂ ለሰዎቹ ስንል ሀሳቡን አናመጣውም። ሰዎች ዜና ናቸው። ሰዎች ሲንቀሳቀሱ ዜና ይፈጠራል። ወንጀል ሲሰሩ ዜና ይሆናሉ። አደጋም ሲደርስባቸው ወይም ሲያደርሱ ጆሮ የሚይዝ ዜና ይወጣቸዋል። መቸም ሙያ ነውና ሐኪም ምንህ ጋ ነው የተጎዳኸው ሲል፣ ፖሊስና ጠበቃ ማነው ጥፋተኛ ይላሉ። ጋዜጠኛ ደግሞ እኔ እሱ ሁሉ አያገባኝም ብቻ የሆነውን ነገር ንገሩኝ፣ አደጋው በርግጥ ደርስቦብሃል? እስኪ ማልልኝ? ማስረጃህ ምንድነው ነው? አደጋው ስለመድረሱ የሚያረጋግጡ ሰዎች ምን ያላሉ ይላል… ወሬ ነዋ። ምክንያቱም ሰፊው ህዝብ ጥሎበት የሚፈልገው ይህኛውን ወሬ ነው። ምን ይደረጋል ደስ ይለዋል። ስለፖለቲካም ሲወራ እንዲሁ ነው። ሰውየው በሰውየው ነው።
አቶ እንቶኔ ስለ መሬት ፖሊሲ ይህን አሉ የሚለው ሳይሆን፣ ይህን ያህል ሚሊዮን ብር አላቸው ወይም አቶ እገሌን እንዲህ አሏቸው፣ ማንትስን አሽቀነጠሩ ሲባል የአገር ጆሮ እንደለገዳዲ ሳተላይት ይቆማል። አቶ መለስ ዜናዊ ስለ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ያወሩ ቀን ሳይሆን ፓርላማቸው ላይ አንድ ሰው የሰደቡ ቀን አገር በሙሉ መነጋገሪያ ያደርጋቸዋል። አቶ ኃ/ማርያም እኮ ሀሳብ አጥተው ብቻ ሳይሆን የሰው ጥላ እንጂ ሰው ሆነው አልታይ እያሉ በመቸገራቸውም ሊሆን ይችላል። ሀሳብ ብቻውን ብዙም ዋጋ የሌለው ለመሆኑ ገለጭ ናቸው። ስለኦባማ ፖሊሲ ሳይሆን ስለ ኦባማ ማንነትና ትውልድ ማውራት እነ ትራምፕን እስከፕሬዚዳንትነት አድርሷቸዋል። ኦባማም ከሀሳባቸው ቀለማቸው በልጦ መልካቸው ትዝ ይለናል። እኔ ኦባማዬ የፈለገውን ያስብ ብቻ ይመረጥልኝ ማለትን ያመጣው – ጥቁር ነው፣ ሎጋ ነው፣ ድምጸ ነጎድጓድ ነው …. ብዙ ብዙ ነገር አለበት። በግድ ጠምዝዘው ሀሳብ ላድርገው ቢሉትም ወደፊት ለጥቁር ዘር ምሳሌ ይሆናል ከመባል አይዘልም።
እና እንዳንዴም “አትፈላሰፍብኝ” ከሚሉ ደናቁርት ፈንጠር ብለው ለብቻ በመሆን በሀሳብ ሲጫወቱ ደስ መሰኘትና መፍትሔህንም መቀኘት አይቀርም። እንኳን አገር፣ ዓለም የተስማማባቸውን ምቾት ሰጪ ሀሳቦችን ራሳቸው እያገላበጡ ቢሰሟቸው ወዲያኛው መልካቸው ያስደነቃል። ለምሳሌ “ትላልቅ ሰዎች ሀሳብን ይወያያሉ። ትናንሽ ሰዎች ግን ስለሰዎች ያወራሉ – ይባላል።” እኔም ብዙ ጊዜ እለዋለሁ። ግን ሌላኛው እኔነቴ ደግሞ- “ ኡ ኡ ቴ! አይተነዋል። መቸም ብቻችንን ሊቅ አንሆንም። አገር ስለሰው ማውራቱን ብቻ ከወደደ፣ ትልቅነትና ትንሽነት ብቻውን ምንም አያደርገም። ሀሳብ እናወራለን ብለን አለቅንኮ!” እያለ ይራቀቃል።
ይህ ደግሞ እውነት ሊሆን ይችላል። የበላ በለጠኝ የሮጠ አመለጠኝ እንዲሉ – ሀሳብ ትተው ሰው አውርተው የከበሩ ብዙ ናቸው። ከድርጅት ይልቅ ሰው ሆነው፣ አንዳንዴም ድርጅቱ ሳይኖር ብቻቸውን ድርጅት ሆነው፣ ከኢትዮጵያ በፊት እነሱ ቀድመው አገር ያስጨበጨቡ ብዙ ናቸው። አውቀውበት ሰው ስለሆኑ እንጂ ሀሳብ ስለሆኑም ብቻ አይደለም። የቁርጥ ቀን ልጆች ሞልተውን የቁርጥ ቀን ሀሳብ ያጣነው ፍቅራችን ከመሪ ሀሳብ ሳይሆን ከሰው ስለሆነ ይመስለኛል። እና ለዚህ ነው፣ ማነው እሱ ? ከየትኛው ብሔር ነው የመጣው? ድርጅቱ ምንድነው?  የሚለው ጥያቄ ፈጥኖ እየተነሳ ለመግባባት አጥር እሚሆነው። “ይሄ ሰውዬ ጥሩ ያስባል፣ የሚለው ነገር ሁሉ ጥሩ ነው፣ ግን ማን ነው እሱ?” ማለት አይቀርም። እንኳን ፖለቲካ የእግዜር ቃል በሚሰማበት ቤት እንኳ ይሄ ጥያቄ ይነሳል። ደግነቱ ያው ካህኑን ይሆን እንጂ – ቃሉንስ ሰማነው እግዚአብሔር ግን ማን ነው? አንልም። ስለ እግዚአብሔር – ብሔር አይጠየቅም። አምላክ እንጂ ሰው አይደለማ! ሰውየው ግን እንደኢትዮጵያ ብሔሩ ከማነው መባሉ አይቀርለትም።
እና ወዳጄ ሆይ ከፖለቲካ ይልቅ ስለትግሬና አማራ ወይም ኦሮሞዎች ማውራት ቀላል የሆነው ሀሳብ ማፍረጫ ሰው ስላለበት ነው። የአማራ ሰዎችን ማፈናቀል የተገባው ሀሳብን በሀሳብ መግጠም ስላልተቻለም ሊሆን ይችላል። ሀሳብን በሀሳብ መግጠም የማይችሉ ሰዎች ቶሎ ብለው ይሄ ሰው ማነው ይላሉ? እነሱም ወደው አይደለም። ሀሳባቸውን በሀሳብነቱ ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው ጋር ብቻ አያይዘው ማቅረብ የሚፈልጉ ሰዎች ጣፋጩን ሀሳባቸውን በገዛ ማንነታቸው ጭምር ጠልፈው እየጣሉ ስለሚያስቸግሩም ጭምር ነው። ይህ ሰው ኢህአፓ ነው፣ ወያኔ ነው፣ ግንቦት ሰባት ነው፣ ኦነግ ነው ምንትስ ነው፣ ማለት ሁል ጊዜ መጥፎ ጥያቄ ነው ማለት ባይገባም፣ ብዙ ጊዜ ግን የሰውን ሀሳብ መግጠም ባልቻሉ ትናንሽ ሰዎች የሚነሳ ጥያቄ ነው። እስኪ የሰውየውን ሀሳብ አመጣጥ ለማወቅ እንድችል ትንሽ የጀርባ ታሪኩን ስጠኝ ማለት ጥሩ ነው። ግን በሰበብና ፍረጃ አድቅቄና አጠፋው ዘንድ ማወደቂያውን አቀብለኝ ማለት ትልቅነት አይደለም። ወይም ለባለጌነቱ እንኳ ባለጌ ነው ግን የኛው የራሳችን ባለጌ ነው መባሉም አስተዋይነት አይደለም።
እናም ስለሆነም ያገኙትን ሰው ሁሉ መጠርጠር በቡድን መፈረጅ የሰዎችን ነጻነት ካለመፍቀድ የተነሳ ሀሳብ ሰው ሳይሆን ማንነት የሚያደምጡ ሰዎች ኢትዮጵያ ላይ ሰው ያስራሉ። ሀሳብ ማሸነፍ ሲያቅታቸው ሀሳቢውን እስከነማሰቢያው ከርቸሌ ይጥሉታል። ውጭ አገር ደግሞ እነደ ተናካሽ ውሻ ጮኸው ከማህበር ያስወጡታል። አሁን ደሬ ሀሳብ ናት ሰው? አብያችንስ ቢሆኑ?! እሳቸው እንኳ መሪ ስለሆኑ ሀሳብ ቢሆኑ ነው ሚያምርባቸው። የሰውየው ሰዎችም ሆኑ ተቃዋሚዋቻቸው ይህን ቢያውቁ እነሱም ሰውና ብሔር መሆናቸው ቀርተው ሀሳብ በሆኑልን ነበር። ጎበዝ አገር እኮ ሰው አይደለችም ሀሳብ ናት! ባትሆንማ ኖሮ ኤርትሬው ኢሳያስ ኢትዮጵያ ላይ ምን ይሰራሉ?  ሰውየው ኢሳያስ ለብዙ ሰው ህልፈት ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ሀሳቡ ኢሳያስ ደግሞ ለብዙ ሰው ህይወት ተስፋ ሆነው ሊክሱን ይችላሉ። ማን ያውቃል? እና በየቀኑ አብይ አብይ ማለታችን ወደን ሳይሆን በአዳዲሶቹ ክስተቶች ተገደን ይመስለኛል። የክስተቶቹ ፍጥነት አስግቶን ሊሆን ይችላል። ጥይቱን ቶሎ ቶሎ ከሚተኩስና ጉዳዮችን ቶሎ ቶሎ ከሚተኩስ መሪ ግን የቱ ይሻለናል እሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ባይሆንም፣ ባለ ጥይቱ አንዳንዴም ኢላማውን አነጣጥሮ መንደል ይችላልና አብይም ሲተኩሱ እያነጣጠሩ ቢሆን ጥሩ ነው ማለቻን አይቀርም። በተቀረውማ መቸም መሪያችንን በጉርምስናቸው ይንቀርፈፉ ይንከርፈፉ አይቀላጠፉ አንላቸውም። አይደል?
Filed in: Amharic