>

ማፈናቀሉም ስደቱም አዲስ አበባም ደርሷል - ልያውም መንግስት ነኝ በሚል አካል!!! (ዘመድኩን በቀለ)

ማፈናቀሉም ስደቱም አዲስ አበባም ደርሷል – ልያውም መንግስት ነኝ በሚል አካል!!!
ዘመድኩን በቀለ 
ስደት መፈናቀሉ ከሶማሊያ ክልል ተነስቶ አዲስ አበባ ጫፍ ደርሷል። በጊዜ መፍትሄ ካልተሰጠው ሀገራዊ ምስቅልቅል ይፈጠራል። በዚህ ደግሞ ማንም አትራፊ አይሆንም። ሁሉም ከሳሪ ነው የሚሆነው!!!
 
~ ሰሚ ኖረም አልኖረ፤ እኔ ግን ለህሊናዬና ለማዕተቤ ስል፣ ደግሞም አንድ ምስኪን ኢትዮጵያዊ ዜጋም ነኝና ስለ ዜጎች መበደል፣ መፈናቀልና ፍትሕ ማጣት ለዓለሙ ሁሉ ጮኼ መናገሩን እቀጥላለሁ። መሞቴ ላይቀር እውነትን ሳልናገራትማ ዝም ብዬ ተለጉሜ አልሞታትም። ስለ እውነት እየለፈለፍኩ ወደማይቀረው መቃብር እወርዳታለሁ። አከተመ።
* ስደተኞቹ አዲስ አበባ ጫፍ ካራ ቆሬ ቅዱስ ፋኑኤል ቤተክርስቲያን ተጠልለው ይገኛሉ።
የሰበታ ከተማ አስተዳደር አስለቃሽ ጭስ የታጠቀ የኦሮሚያ ፖሊስን በማሰለፍ፣ የአካባቢውን ቄሮም በማሰማራት በአዲስ አበባ መውጫ አካባቢ ከገበሬ ቤት ገዝተው ከ15 ዓመት በላይ በሕጋዊ መንገድ መብራት፣ ውኃ አስገብተው፣ ትምህርት ቤት ተገንብቶላቸው ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን መኖሪያ ቤት ፍርስርሱን አውጥተው ዜጎችን ሜዳ ላይ እንዲበተኑ አድርገዋል።
የኢቲቪ ጋዜጠኛ ያነጋገረቻቸው የከተማው አስተዳደር ኃላፊ እንደተናገሩት ከሆነ ከመፍረስ የዳኑት በአየር ካርታ ላይ የተገኙ 7 ቤቶች ብቻ ናቸው እንጂ ቀሪዎቹን ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንዲፈርሱ አድርገናልም ሲሉ ተደምጠዋል። ነዋሪዎቹ ደግሞ ያልፈረሱትን ቤቶች ከመፍረስ ያዳናቸው የቤቶቹ ባለቤቶች ዘር ከአፍራሾቹ ወገን ስለሆነ ነው ይላሉ።
በአሁኑ ጊዜ መንግሥቱን በመልካም ጎዳና እንዲራመድ በቅንነት መተቸት በመንግሥቱ ጭፍን ደጋፊዎቹ አማካኝነት የለየለት የስድብ ዘመቻ የሚያስከፍት ቢሆንም እኔ ግን ደግሜ እላለሁ። ኦህዴድ/አዴፓ ሆይ ! ጊዜው የአንተ ነው። ጊዜና አጋጣሚ ይህቺን ታላቅ ሀገር የመምራት ዕድሉን ሰጥቶሃል። ዘመኑ የራስህ ነው። ዕድሉን በአግባቡ ተጠቀምበት። ያለፈውን የዘረኛዋንና የአፈናቃይዋን የህወሓትን ስህተት ኮፒ ፔስት አድርገህ አትድገም። የጥፋት መንገዷንም አትከተል። ከአንደበትህ የሚወጣው ወርቃማው ቃልህና ተግባርህ አይለያይ። ጌዜ የሰጠው ቅልም አትሁን። ፎቶ እያሳመሩ በመነሳት የሀገር ችግር አይፈታም። ተወዳጅነትም አይገኝም። ዘመኑ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መሆኑንም አትዘንጉ።
ጎበዝ ! የድሆች ሀዘን ብርቱ ነው። ለመጽሐፍ ቅዱስ ቀረብ ያላችሁ እንደሆናችሁ ስለሚጠረጠር የራሔልን እንባ ማስታወሱ በቂ ነው። የድኾች እንባ እሳት ነው። አቃጥሎ በቁም ለብልቦም ይጨርሳል። የድኾች እንባ ጎርፍ ነው። በዳዮችን፣ ግፈኞችንና ጨካኞችን ግፈኞችንም አጥረግርጎ ይወስዳል። የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም የሚባለው እኮ ያለ ነገር አይደለም። በእንቁላሉ ጊዜ አስተዳደራችሁን ለማረም ሞክሩ። የእግዚአብሔርና የህዝብ ዝምታ የፍርሃት እንዳልሆነ እወቁ። የህዝብ እንባ ተጠራቅሞ ጎርፍ ሆኖ እስኪወስዳችሁ አትጠብቁ። የግፍ ጽዋው የሞላ ዕለት ግን አሁን በቀበሌ ሚኒሻ የምታስጨንቁትን ህዝብ ከኔቶ የጦር ኃይል ብታመጡ እንኳ የህዝብን ብሶት ለመገደብና ለማቆም ትቸገራላችሁ። ይሄ የእኔ ምክር ነው። እናም አስቡበት። ማን ነበር ” ማርክ ማይ ወርድ ያለው? እንደዚያ ነው። “ማርክ ማይ ወርድ”።
አሁን ቤታቸው በላያቸው ላይ የፈረሰባቸው ዜጎች በአዲስ አበባ ከተማ በካራቆሬ ቅዱስ ፋኑኤል ቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ ተጠልለው ይገኛሉ። ቤተክርስቲያኒቱ ለሙስሊሙ፣ ለክርስቲያኑ ሁሉ መጠለያ ሆናቸዋለች። በአጎራባች የአዲስ አበባ ከተሞች የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎችም የዳቦና የውኃ አቅርቦት አቅም በፈቀደላቸው መጠን እያቀረቡላቸው እንደሚገኙ ከደረሰኝ መረጃ ለመረዳት ችያለሁ።
በተፈጠረው የጭካኔ ተግባር ህጻናት ደንግጠዋል። ትምህርታቸውንም አቋርጠዋል። ይባስ ብሎም ሳያስቡት የጎዳና ተዳዳሪ የመሆኛ መንገዱን ሳያስቡት ጀምረዋል። አረጋውያን፣ ህመምተኞችና ሴቶችም ሳያስቡትና ባለገመቱት መንገድ አውራ ጎዳና ላይ ወድቀው ራሳቸውን አግኝተዋል። 50 ከመቶ ሴት ሚንስትር ሾማ ዓለምን ጉድ ባሰኘች ሀገር ውስጥ 70 ከመቶ የሚሆኑ ሴቶችና ህጻናትን፣ እንዲሁም አረጋውያን እናቶችን በግፍ አፈናቅሎ ጎዳና ተዳዳሪ የሚያደርግ መንግሥት በየትኛውም መመዘኛ ፌር አይሆንም።
መንግሥታዊ ተፈናቃዮቹ የትም መሄጃ የሌላቸው እንደሆኑ ታውቋል። የቤት ኪራይ የመከራየት አቅሙም የሌላቸው ምስኪኖች መሆናቸውም ተነግሯል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የቤት ኪራይ የማይቀመስና የማይሞከር እንደሆነም ይነገራል። አብዛኛው ተፈናቃይ ለፍቶ አዳሪና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ ኑሮውንና ህይወቱን የሚገፋም ምስኪን ነው። እናም ምን እንደሚያደርጉና ወዴትስ እንደምንሄድ ጨንቆናል ነው የሚሉት የአዲስ አበባ ጫፍ ስደተኞቹ።
~ ” አባቶቻችንም ሁሉ እንደነበሩ እኛ በፊትህ ስደተኞችና መጻተኞች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ናት፥ አትጸናም።” 1 ዜና 29፣15።
Filed in: Amharic