>

የኢትዮጵያና ህዝቧን ደም በስሪንጅ የመጠጠው ሜቴክ!!! (ሉሉ ከበደ)

የኢትዮጵያና ህዝቧን ደም በስሪንጅ የመጠጠው ሜቴክ!!!
ሉሉ ከበደ
የኢሳቱ ሲሳይ አጌና መስከረም 5፣ 2018 ከብርጋዴር ጀነራል መላኩ ሺፈራው ጋር ሜቴክን በተመለከተ ቃለ ምልልስ እድርጎ ነበር። ጀነራሉ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የመረጃ ዋና መምሪያ የትንተናና  ፕሮዳክሽን ዲሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ኢትዮጵያዊ ናቸው። የአማራ ተወላጅ በመሆናቸው ከሰራዊቱ ከተገለሉ ዜጎችም መካከል እንዱ  ናቸው።
ጀነራሉ ስለ ሜቴክ አመሰራረት  ሲናገሩ፤ የዝርፊያው ሰንሰለት እንዴት እንደተዋቀረም ቁጭ ቁልጭ አድርገው አስቀምጠውት ነበር። ተቋሙ ባስር ሚሊዮን ብር የተጀመረ  ነው። ከዚያ በፊት የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች በሚል የተደራጀ  ፤ ስምንት የሚያህሉ ፋብሪካዎች የነበሩት ክፍል ነበር።በዋናነት ያመርት የነበረውም  የመከላከያ አልባሳት፤  ቁሳቁስና ጦር መሳሪያና ጥይት የመሳስሉ ለጦር ሰራዊት አገልግሎት   የሚውሉ ምርቶችን  ነበር ። ሀገሪቱ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ኢንዱስትሪ መር ለማድረግ በመንግስት በታቀደው መሰረት  ሜቴክ የሀገሪቱን ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች እሰባስቦ  እንዲመራ ሀላፊነት ተሰጠው። ከዚያ በፊት አቶ ሱልጣን የሚባሉ ሚኒስትር ዴኤታ በሙያ ብቃትም በትምህርትም  የበለጸጉ ሰው ኢንዱስትሪውን ይመሩት ነበር። ለአዲሱ ወያኔያዊ አወቃቀር ሁኔታውን ለማመቻቸት ሲባል እኒህ ባለሙያ ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ ከመከላከያ እንዲለቁ ተደረገ። ከዚያ ጀነራል ክንፈ ከደጀን አቪየሽን የስራ ሀላፊነት ወደ ሜቴክ ተዛውረው ባዲሱ ተቋም ዳይሬክተር ሆኑ። ከዚያ በኋላ ሰባ የሚሆኑ ፋብሪካዎችና  አስራአምስት የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች አንድ ላይ ተጠቃለው ሜቴክ እንዲያስተዳድራቸው በአዋጅ ተቋቋመ።
ሜቴክ ሲቋቋም ጀነራል ክንፈ ዋና  ዳይሬክተር ሲሆኑ ፤ሌሎች ምክትል ዳይሬክተሮች ጀነራል ጥጋቡ ፈትለ፤ ጀነራል  ጠና ቁሩንዲ፤ ኮሎኔ በርሄ በጊ፤ ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብሬል፤ኮሎኔል ጌትነት፤ ኮሎኔል አብዱሰላም የሚባሉ ተጨመሩ።
አነዚህ ተሰባስበው ይህን ተቋም እንዲመሩ የተመረጡ የህውሀት ሰራዊት መኮንኖች፤ ካሳለፉት ወታደራዊ ልምድና ህይወት በስተቀር የትምህርትም የስራ ልምድ ተሞክሮም ያልነበራቸው የትግራይ  ሰዎች  ስብስብ ነበሩ። ከፊሎቹም በጡረታ ከመደበኛ ስራቸው የተገለሉ ነበሩ። በተለይም ሁለቱ ምክትል ዳይሬክተሮች ፤ ጀነራል ሙሉ ወልደገብሬል ቻይና ሚሊታሪ እታሼ የነበሩና በጡረታ የተሰናበቱ፡ ሁለተኛው ኮሎኔል በርሄ በጊ ደቡብ ሱዳን ሚሊታሪ አታሼ የነበሩና ጡረታ የደረሱ ነበሩ። ነገር ግን በሜቴክ ምክትል ዳይሬክተርነት እንዲሰሩ ተሹመዋል። ይህም ሆን ተብሎ የጥቅም ሰንሰለት ለመፍጠር በታቀደው መሰረት የተቀናጀ እሰራር ነበር። ፕሮፌሽናል ሰዎች ሆን ተብሎ እንዲገቡበት አልተፈቀደም። ኢንዱስትሪውንና ስታፉን የሚመሩት ሰዎች በህውሀት መኮንኖች እየተሞላ የሄደበት ሁኔታ ተፈጠረ። መጀመሪያ ላይ ሲዋቀር ግን  ከኦሮሞም ከአማራም  አንዳንድ ሰዎች በጣልቃ በጣልቃ ተመድበው ነበር። በሂደት ግን ለሌብነት ለቡድን ዝርፊያ በሚያመች መልኩ ያንድ አካባቢ ሰዎች በተለይም የህውሀት መኮንኖች በሀላፊነት እየተመደቡ የመጡበት ሁኔታ ተፈጠረ።  በስንት ጊዜ ውስጥ ሆነ ትግሬ ያልሆኑትን  ማጽዳቱና ሽግሽጉ? ከአንድ አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ። ተፈጸመ። እንዲህም  ከላይ እስከታች የሌብነት ኔትዎርክ ተፈጠረ። ከመከላከያ ቺፍ ኦፍ ስታፍ አስከ ታችኛው የሜቴክ የኢንዱስትሪ ሀላፊ።  እንዳንዱ በቀጥታ በዝርፊያው የተሰማራ ፤አንዳንዱ ደላላዎችን በስተጀርባው ያዘለ፤ አንዳንዱ ደግሞ የሚነሱ ተቃውሞዎችን የሚያፍን ቡድን  ሆነው ሜቴክ በህውሀት ሰዎች ተደራጀ።
ሜቴክ በሂደት ብቃት ያላቸውን  ዋና ዋና ስታፍና የኢንዱስትሪ ሀላፊዎችን እያስወገደ በሚፈለጉ ሰዎች ሲተካ ሌብነቱን ተቋማዊ ለማድረግ የተጓዘበት ሂደት መሆኑ  ነበር። ሜቴክ የሚሰራው ለሀገሪቱ ትራንስፎርሜሽን እድገት ነው የሚል ሽፋን ተሰጠውና የሚቃወሙ ጀነራሎች፤ የሚቃወሙ የክፍል አመራሮች ፤ ልማታዊ  አመራር የሚከተለውን ሜቴክ በኪራይ ሰብሳቢ ሀይሎችና  ጥገኞች ወሬ ስም እያጠፋችሁ ነው የሚል ስም እየተለጠፈላቸው  በህውሀት ያልተፈለጉት ዜጎች እንዲሸማቀቁና ካካባቢው እንዲገለሉ ተደረገ። እንዲህም ተቋማዊ የሌብነት አካሄድ እንዲኖር  ተመቻቸ።
ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ በሀገሪቱ አራቱም ማእዘን ልማት ተብሎ ከህውሀት ራዳር ውጪ አንድ ነገር እነሱ የሌሉበት ያልገቡበት መስክ እንዳይኖር የተደረገው። በአራቱም ማእዘን ህውሀት እጁ የሌለበት ስራ እንዳይኖር የተደረገው። ብሎም የኢትዮጵያና ህዝቧ ደም በስሪንጅ የተመጠጠው።
Filed in: Amharic