>
6:40 pm - Tuesday May 17, 2022

በይዘቱ ለየት ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ደብዳቤ ለየመን እና ተፋላሚ ወገኖች!!! (ቢቢሲ አማርኛ)

በይዘቱ ለየት ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ደብዳቤ ለየመን እና ተፋላሚ ወገኖች!!!

ቢቢሲ አማርኛ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በጦርነት ለዓመታት እየታመሰች ላለቸው የመን እና ተፋላሚ ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ፣ እንዲሁም በስቃይ ውስጥ ያለውን ሕዝባቸውን ከከፋ ችግር እንዲታደጉት የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፈዋል።

ከተለመደ ፖለቲካዊ ዘዬ ወጣ ያለ ይዘት ያለው ይህ ደብዳቤ በየመን በጦርነት ተሳትፎ ያደረጉ የውጭ ኃይሎችን ከማውገዝም ሆነ ከመውቀስ የተቆጠበ ሲሆን በየመን ሁለት ጎራ ይዘው የሚዋጉ ወገኖችን ግን ክፉኛ ይወቅሳል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በይፋ በድረ ገጹ ትናንት ባሰራጨው በዚህ መልዕክት የመን ውስጥ ላለው ምስቅልቅል የየመን ሕዝብን ብቸኛ ተጠያቂ ያደርጋል።

በጥንታዊ ሥልጣኔ ውስጥ የመን የነበራትን ታላቅ ስፍራ በመዘርዘር የሚጀምረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አሊ ደብዳቤ የመን በሁለቱ ቅዱሳን መጻሕፍት የነበራትን ቦታና ክብር ለማጉላት ይሞክራል። በተለይም በብሉይ ኪዳን “የብልጽግና ምድር” መባሏን በጥንታዊ ግብጻዊያን “ቅዱስ ምድር” እየተባለች መሞካሸቷን በቁርዓንም እንዲሁ መጠቀሷን በመግለጽ ይጀምራል።

ደብዳቤው ጨምሮ “ለእናንተ ለየመን ሕዝቦች፤ ለደስተኞቹ፤ ማንም አገር በነብዩ መሐመድ የናንተን ያህል አልተጠቀሰም” ካለ በኋላ “ነብዩ መሐመድ ይህንን ብለውም ነበር” ሲል ያጣቅሳል። “…የየመን ሕዝቦች ወደናንተ ይመጣሉ፤ የቅን ልቦና ባልተቤቶች፣ ገራገሮች…እና ብልህ ሕዝቦች…” ሲል።

“በአንድ አምላክ የሚያምንና አንድ ሃይማኖት የሚከተል ሕዝብ ስለምን ጦርነት ውስጥ ይዘፈቃል?” ብሎም ይጠይቃል ደብዳቤው። ጦርነት ክልክል (ሐራም) ነው ሲልም መንፈሳዊ አንቀጾችን ጭምር እየጠቀሰ ይቀጥላል፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለየመን ሕዝብ ይድረስልኝ ያሉት ይህ ጦማር።

ደብዳቤው ተዋጊ ወገኖችን በጥብቅ የማውገዝ ዝንባሌም ከፍ ያለ ነው።

“ስለምን ሥልጣኒያችሁን በገዛ እጃችሁ ታወድማላችሁ? ስለምን ክብራችሁን ታዋርዳላችሁ? ስለምን ልጆቻችሁን ወላጅ አልባ ታደርጋላችሁ? ስለምን ከልጆቻችሁ ደስታን ትሰርቃላችሁ? እናንተ በቅዱሳን መጻሕፍት ‘ደስተኛ ሕዝቦች’ ተብላችሁ የተወደሳችሁ አልነበራችሁምን?” ሲል ይጠይቃል።

ዐብይ አሕመድ በዚህ ጦማራቸው ሁለቱንም ወገኖች ‘ከንቱ ጦርነት ላይ ናችሁ’ ሲሉም ደጋግመው ያስገነዝቧቸዋል።

ይህ ጦማር የአገሪቱን ጥንታዊ ገናናነት ካወሳ በኋላ በቀጣይ አንቀጽ ተዋጊ ወገኖችን በተመሳሳይ ወደማውገዝ ይመለሳል።

“…አገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ እያፈራረሳችሁ ያላችሁት [ለመሆኑ] ምን ለማግኘት ይሆን? ስለምን ምክንያት አልባ ትሆናላችሁ? በታላቁ ነብይ ብልሆች ተብላችሁ አልነበረምን? ስለምን የጦርነት ነጋሪት ትጎስማላችሁ? መነጋገርና መወያየትን እየቻላችሁ?” ብለዋል።

ደብዳቤው በሁለተኛ ገጹ አሁን ላይ በየመን ለደረሰውና እየደረሰ ላለው ሁሉ ኃላፊነቱን የመናዊያን ብቻ እንዲወስዱ ይሞግታል።

“እናንተ አሁን በጦርነት ለፈረሰችው የመን ኃላፊዎች ናችሁ” ሲልም ያሳስባል።

በመጨረሻም የዕርቅና የሰላም ጥሪን የሚያቀርበው ይህ ደብዳቤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማስታረቅ ሚና መጫወት እንደሚፈልጉ በቀጥታ ባይጠቅስም ለሚፈለግ ማንኛውም ትብብር ግን ዝግጁ እንደሆኑ ሳይጠቅስ አላለፈም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሊ በደብዳቢያቸው መጨረሻ፣ “አሁን ተጨባበጡ፤ በፍቅርና በንጹሕ ልብ ተዋደዱ፤ ብልህነታችሁ ብርሃን ይሁናችሁ….” ካሉ በኋላ “…የሚፈለግብንን ለማድረግ፣ እርቅን ለማምጣት፣ የደም መፋሰስን ለማቆም እናንተን ወደ ሰላምና ብልጽግና ለመመሰለስ የሚፈለግብንን ለማድረግ በእኛ በኩል ዝግጁ ነን” ሲሉ አስታውቀዋል።

Filed in: Amharic