>
5:59 pm - Tuesday May 17, 2022

ትላንት የተጥላላው አስተሳሰብ ዛሬ ገዢ ሃሳብ ሆነ!!! (ሀይለገብርኤል አያሌው)ትላንት የተጥላላው አስተሳሰብ ዛሬ ገዢ ሃሳብ ሆነ!!!
ሀይለገብርኤል አያሌው
 
 አማራነት! ሲበርድ የሚለብሱትና ፤ ሲሞቅ የሚያወልቁት እጀጠባብ አይደለም!!              
 በአማራው ሕዝብ ላይ ላለፋት 27 አመታት ሲካሄድ የቆየው ሕልውናውን የመናድ ዘመቻ የአዋጁን በጆሮ እንዲሉ ከማንም የተሰወረ አይደለም:: በዚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ባለታሪክ ሕዝብ ላይ በቅንብር የተከፈተው ዘመቻ በእግዚአብሄር ቸርነት ተጠብቆ ነው እንጂ እረኛ እንደሌለው መንጋ በየአቅጣጫው ተበትኖ ወጥቶ በቀረ ነበር:: ልጅ እያለው እንደ መሀን ወገን እያለው እንደባዳ ለመከራው ቀን የሚደርስ ለሃዘኑ አጽናኝ ዘመድ አጥቶ እንባውን እያበሰ ብዙ የጭለማ እመታትን አሳልፋል::
 ለአማራው ሕዝብ መዋረድ መረገጥና መከራ ላይ መውደቅ ምንም ምክንያቶቹ ጠላቶቹ ቢሆኑም ሳይማር ያስተማረው ሳይጠግብ ያጎረሰው ተራቁቶ ለክብር ባበቃቸው ልጆቹ ተክዶ በመቆየቱ ለመሆኑ ለክርክር የማይቀርብ ሃቅ ነው::
 እርግጥ ነው ቁጥሩ አነሰ እንጂ የወገን ስቃይና መከራን አይተው ማለፍ ያልሆነላቸው ልጆቹ እስከ ሞት ታምነው አልፈዋል:: በእስር ተንገላተዋል በስደትም ባክነው ቀርተዋል። ፕሮፌሰር አስራትን መቼም አንዘነጋም:: የነጎቤን መስዋዕትነት የነኮሎኔል ደመቀን ጀግንነት ፤ የነማሙሸት አማረን ጽናት ታሪክ በክብር የሚያኖረው የቅርብ ግዜ ታሪካችን ነው:: በሃገር ውስጥ አቅምና ደጋፊ አጥቶ እንጂ ሕዝባችን በሚችለውና ባለው አቅም ብዙ ደክሟል::
     በሃገር ውስጥ ከጸናው አፈና አንጻር አንጻራዊ ነጻነት ባለበት በውጪ ሃገር ተሰዶ የሚኖረውን የአማራ ማሕበረሰብ ለማሰባሰብ ላለፋት እረጅም አመታት ብዙ ሙከራ ሲደረግ ቆይቷል:: ነገር ግን ወገናችን የሚደርስበትን የተደራጀ ጥቃት እንደ ሕዝብ ተደራጅቶ ለመታገል እጅግ አሰልቺና አታካች ሂደት ውስጥ አልፏል :: አማራን ማደራጀት እንደ ኒኩለር ሳይንስ የከበደ እንቆቅልሽ ሆኖም ቆይቷል::
         ለዚህ መፈናቀል ፤ መገደል ፤ መታሰርና መሰደድ እጣው ለሆነ ወገን ደጀን ለመሆን የቆረጠ ለዝና የማይወድቅ ፤ ጥቅም የማያጏጏው ግለኝነት ያልተጠናወተው ወገን በመጥፉቱ የስድብ መማሪያና የመድሃኒት ቤተ ሙከራ ሆኖ አሳልፋል::
     ይህ ምስኪን ሕዝን በተፈጥሮ ባገኘው ማንነቱ ሲጠቃ ማገዙ ቢቀር በተለይ ምሁር ነን ባዮችና ቅንጡ የአንድነት ፖለቲካ አራማጆች በአማራነት መደራጀትን ማባሪያ የለሽ የማጠልሸት ቅስቀሳን በማቀንቀን በችግሩ ላይ ሌላ ችግር ፈጥረውበት ቆይተዋል::
     የሌሎች ኢትዮጵያዊ ብሄር የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን እንደ እንቁላል የሚንከባከበው የአማራው ልሂቅና ስጋጃ እያነጠፈ በእንቢልታ የሚቀበለው የአንድነት ርዕዮት አራማጅ ነኝ ባዩ በማንነት መደራጀት ስህተት ሆኖ የሚያገኙት አማራ ላይ ሲደርስ ብቻ እንደነበር አይዘነጋም::
     የተገፋው የአማራነት ጥያቄ በእነ አቶ ገዱ ጉብኝት የሚደንቅ የሕዝብ ብዛት ታዬ:: ይሄን ማየት በራሱ ታሪክ ነው:: አዳራሹ ከሚዘው በሺህ የሚቆጠር ሕዝብ በላይ መግባት አቅቶት የተመለሰው ቢልቅ እንጂ የሚያንስ አልነበረም:: ይህን ያየ በእርግጥ ይህን ያህል ብዛት ያለው አማራ አለ ብሎ ቢገረም አይደንቅም:: ለምን ? ወገን በቃተተበት መከራው በከበደበት ያ የጭለማ ግዜ አደባባይ የሚወጣ አልነበረምና?
        ግዜ ደግ ነው ሁሉን ያሳያል:: ትላንት የተጥላላው አስተሳሰብ ዛሬ ገዢ ሃሳብ ሆነ:: ትላንት ለአማራው ሕዝብ ችግር እንዲደርሱ የተጠየቁ ምሁራን በንቀት እንዳልተራቀቁ ዛሬ ያውም በአዴፓ (ብአዴን) እየተጋፉ በክት ልብሳቸው ደምቀው ተደመሩ:: ትላንት የአማራን ጉዳይ ማንሳት ያልፈለጉ ጋዜጠኞችና ሚድያዎች የመጀመሪያው እረድፍ አድማቂዎች ሆኑ:: ትላንት ከተበደለ ጎን መቆምን ሃዋርያዊ ግዴታቸው መሆኑን ዘንግተው የወገናቸውን በደል የዘነጉት ካህናትና አገልጋዮች ዛሬ ግንባር ቀደም እንግዶች ሆነው ጉባዔውን ባረኩ:: ይህን ሁሉ በዚሁ መስመር ላይ ቆመን አየን::
      የዚህ ጽሁፍ አላማ የአማራ ክልል ልዑካን ለምን ብዙ ሕዝብ ወጥቶ ተቀበላቸው በሚል ተቃውሞ ለማቅረብ አይደለም:: ለኢትዮጵያችን ቀጣይነት እና ለአማራው ሕልውና ዘላቂነት የሚደረገው ትግል ገና ተጀመረ እንጂን አልተጠናቀቀም:: በስሜት ተወጥሮና በአዳራሽ ትዕይንት እረክቶ ወደየመጡበት መመለስ ለውጡን ለቅልበሳ እንዳያጋልጠው እንደ አንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ በየእርከኑ መደራጀት አስፈላጊና አንገብጋቢ የወቅቱ ጥያቄ መሆኑን ለማስረገጥ ነው::
    ከዚሁ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ይህ ሁሉ ምሁርና ሕዝብ ባለበት ከተማ አንድ እንኳ ተጠሪ ሊሆን የሚችል ተቋም መፍጠር አለመቻል የፈጠረው ክፍተት ለመጠቆም ነው:: የሕዝባችንን ጥያቄ ሃሳብና የመፍትሄ አቅጣጫ በተደራጀና በሰለጠነ መንገድ ቀምሮ አንጥሮና አጣርቶ ማቅረብ አቅቶን ሁላችንም ጠያቂ የሆንበት ሁኔታ ማየት ያስገምታል::
   ሌላው አዴፓ (ብአዴን) ምንም አሁን ካለው ተጨባጭ የሃገራችን ሁኔታ አኳያ የተጠናከረ ድጋፍና እገዛ ሊደረግለት የሚገባ ቢሆንም ድርጅቱ ካለፈ አዳፉ ታሪኩ ገና ያልጸዳና የአማራን ሕዝብ ሊወክል የሚችልበት ቁመና ላይ ያልደረሰ መሆኑ ሊጤን ይገባል:: ስለዚህም ትላንት በጥራዝ ነጠቅነት ማንነቱን ሲገፋ የቆየው ምሁርና የሕብረተሰብ ክፍል የተገኘውን አንጻራዊ የለውጥ አቅጣጫ ወደ አስተማማኝ ምዕራፍ ለማሸጋገር ተደራጅቶ መገኘት ይኖርበታል::
     በዚሁ ከነ አቶ ገዱ ጋር በተደረገው ውይይት ላይ አንድ አንጋፋ አባት እንዳሳሰቡትም: ይህ ሕዝብ ሞቅ ሞቅ ሲል መሰብሰብ ብቻ መፍትሄ አይሆነውም:: ብለው ያቀረቡት ምክር ሊሰመርበት ይገባል:: አለያ መከራ እርቆ አሸናፊነት የመጣ የመሰለን ግዜ የክት ልብሳችንን ለብሰን በየአደባባዩ አንቱ ለመባል የምንፈልግ ከሆነ በቆምንበት የምንቀርና ለሌላ ዙር ባርነት የሚዳርገን ለመሆኑ ከሩቁ ሳይሆን ከቅርብ ግዜ ታሪካችን ልንማር ይገባል:: በምርጫ 97 ማግስት በድል ዜና የሰከሩ ተቃዋሚ የዲያስፖራ ኤሊቶች የሕዝብ ነጻነትና የሃገርን ሕልውና ዘንግተው ለሚንስትርነት ቦታ ሲመራረጡ እንደነበር አይዘነጋም:: እንዲህ አይነት ጥቅመኝነትና ለሞቀበት መድረክ መንበርከክ ምሁራዊም ወግ ኢትዮጵያዊም ባህል አይደለም:: በእሁዱ ስብሰባም ላይ የታየው የአንዳንዶች የአድርባይነት ሁካታ የሚያሸማቅቅ ነው::
     የአማራው ምሁር በሃገር ውስጥ ያለውን ሕዝብ ለማገዝና የለውጡን ሂደት ለማፍጠን እንደየችሎታና ሙያህ ተደራጅተህ እገዛ የማድረግ ግዴታና ከፍለህ ያልጨረስከው እዳ አለብህ:: ከጥላህና ከማንነትህ ሸሽተህ ማምለጥ አትችልም:: ከተምታታ ትርክትና ከወጠረህ ኢጎ ተላቀህ ተጨባጩን እውነት ልትጋፈጥ ይገባል:: ትላንት ሲጨልም መሸሽ ዛሬ ሲነጋ መገኘት ሰብዐዊነት የጎደለው ሞራለቢስነት ነው;:  አማራነት ! ሲበርድ የሚለብሱት ሲሞቅ የሚያወልቁት እጀጠባብ አይደለም:: ሊለወጥ የማይችል የደም ማሕተም ነው።
እግዚያብሄር ኢትዮጵያ ሃገራችንን ይባርክ!!!
Filed in: Amharic