>

ይድረስ - ዩኒቨርሲቲ ለምትገኘው ልጄ!!! (ኤልያስ ታረቀኝ)

ይድረስ – ዩኒቨርሲቲ ለምትገኘው ልጄ!!!
ኤልያስ ታረቀኝ
ልጄ ሆይ ፈፅሞ ዘረኛ አትሁን! ሰብአዊ ክብርህን ገፎ ክፉ ያደርገሃል! ተው ልጄ ክፉ አትሁንብኝ! ከሁሉም ነገር በላይ ሰው ሁን! ከሁሉም በፊት ሰውነትን አስቀድም! እኛ ሰዎች እኮ በድርሰቶች ውስጥ ለምናነባቸውና በፊልም ለምናያቸው አሳዛኝ ገፀ-ባህሪያት እንስፍስፍ የምንል ድንቅ የእገዜር ስራዎች ነን! ፊልም አይተህ አልቅሰህ አታውቅም? ለማይጨበጡት የምናብ አለም ገፀ-ባህሪያት ማዘን ከቻልን እንዴት በገሀዱ አለም ላሉት እህትና ወንድሞቻችን እንጥፍጣፊ ርህራሄ ይጠፋናል!?
 ተው ልጄ! እባክህ ዘረኛ አትሁን! የአለም ሰው ሁሉ ዘረኛ ሆኖ አንተ ብቻ ብትቀር እንኳ ምርጫህ ዘረኝነት አይሁን! መውደድን ጠልቶ፣ መጥላትን መውደድ ሰውኛ አይደለም ልጄ! እግዜር የሰጠህን ሰው የመሆን ክብር ዘረኝነት ተብሎ በሚጠራ ጥቁር አቡጀዲ ጠቅልለህ አትቅበረው! እረፍ ልጄ!
ፍትህ ጠይቅ እንጂ ዳቦ አትለምን ልጄ! ምን ደረሳቸው እንጂ ምን ደረሰኝ አትበል! ያለህን አካፍል እንጂ ከትንሻቸው አትዝረፍ!
ተው አይበጅህም የኔ ጌታ ቂም አትቋጥር! አብሮ ለመኖር እንጂ አጥፍቶ ለመኖር አታልም!
ልጄ ሆይ እብጠትህን ቀንስ! የጋራ ጎጆ ቀልስ! ፍቅር ተንፍስ! ሰላም ዘምር! አንድነት ቀምር! ይቅርታ አስተምር! መልካም አስብ! በብሔር ልክ አትጥበብ! ሀገር ነህና በሀገር ልክ ሰፋ! ሰው ነህና በአለም ልክ ስፋ! ቀና ተመኝ! በጎ ስራ! አታብዛ ከንቱ አተካራ! ክፉ አትስራ!
ከዚህ ሌላ የምልህ የለኝም ብሌኔ! ከዚህ ሌላ ሁን ብዬ የማስቸግርህ ነገር የለኝም የኔ ጌታ! ሰው ብቻ ሁንልኝ! አደራ! ዘረኝ ሆነህ አታሳፍረኝ! የሰው ቡና መጠጫ መሆን አልፈልግም! የዘረኛ እናት መባል አልፈልግም! የኔ ልጅ ሰው ነው! ዘረኝነት ጨርሶ የለበትም እያልኩ በኩራት አወራ ዘንድ እድሉን ሰጠኝ!
Filed in: Amharic