>
4:21 pm - Wednesday November 30, 2022

ዳሩ እየተቃጠለ መሃሉ ሰላም ሊሆን አይችልም! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ዳሩ እየተቃጠለ መሃሉ ሰላም ሊሆን አይችልም!
ያሬድ ሀይለማርያም
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች፤ በተለይም በቤንሻጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በጎንደር አንዳንድ ወረዳዎች፣ በሶማሌ ክልል እና በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ወረዳዎች ውስጥ ያለው ውጥረት ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ ወጥቶ ይሁን ወይም ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ሳይቸረው ስለቀረ ለሰው ህይወት መጥፋት፣ ለከፍተኛ ንብረት መውደም እና ለዜጎች ከቀያቸው መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።
አብዛኛዎቹ ግጭቶች ለመንስዔዎቻቸው ምክንያት የሆኑት ነገሮች በቅጡ ተጠንተው ዘላቂ የሆነ የመፍትሔ እርምጃ እስካላገኙ ድረስ በመንግስት ማስጠንቀቂያና ዛቻ የሚፈቱ አይነት አይደሉም። ለእነዚህ ግጭቶች መንስዔ ከሆኑት ነገሮች መካከል የተወሰኑትን መጥቀስ ይቻላል፤
– በህውሃት እና በፌዴራል መንግስቱ መካከል ያለው ውጥረት አለመርገቡ እና መፍትሔ ሳያገኝ መቆየቱ፣
– በአማራ ክልል እና በትግራይ ክልላዊ መንትግሥታት መካከል የተፈጠረው ቅራኔ እየተካረረ መምጣቱ፣
– ኦነግ ወይም በስሙ የተደራጁ ታጣቂ ኃይሎች በተወሰኑ የኦሮሚያ ክልል ወረዳዎች ውስጥ ያለምንም ገደብ መንቀሳቀሳቸው እና ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ አለመሆናቸው፤ እንዲሁም ትጥቅ ለማስፈታት የተንቀሳቀሰው የመከላከያ ሰራዊት የታጣቂ ቡድኖቹ ደጋፊ በሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ችግር እየተፈጠረበት መሆኑ፤ መንገድ መዝጋት እና የመሳሰሉት፤
– ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ጥያቄ የተሳባቸው አካባቢዎች ላይ ያለው ውጥረት አሁንም አለመብረዱ እና የክልል መንግስታትም በእነዚህ ጉዳዮች በጋራ መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ የግጭቶቹ አካል መሆናቸው ነው።
እነዚህ እና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች በቅጡ ካልተያዙ እና አፋጣኝ መፍትሄ ካላገኙ ዳሩ ብቻ ሳይሆን መሃሉም መታመሱ አይቀርም። ያ ደግሞ የተጀመረውን የለውጥ መነቃቃት ሊገዳደር እና ሂደቱም አዝጋሚ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ የሚደርሰውም ውድመት በእጥፍ ሊጨምር ይችላል።
መፍትሔ
– በህውሃት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለውን ክፍተት እና ተቃርኖ አዲስ አበባ እና መቀሌ ላይ ሆኖ አንዱ በሌላው ላይ መግለጫ በመስጠት እና በመወራረፍ ሊፈታ አይችልም። በዚህ ጉዳይ ከተቻለ ሸምጋይም ፈልገው ሊነጋገሩበት እና በአፋጣኝ ሊፈቱት ይገባል። ያ ካልሆነም የፌደራል መንግስቱ ሕገ-መንግስቱን መሰረት ያደረገ ሕጋዊ እና የፖለቲካ ውሳኔ የታከለበት እርምጃ ሊወስድ ይገባል። ይህ ችግር እንዲህ እንደማውራት ቀላል ባይሆንም እያስታመሙ መቀጠሉም ከዚያ በላይ ችግር ያስከትላል።
– በአማራ እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥታት መካከል ያለው ግጭት የድንበር ብቻ አይደለም። በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ተዳፍኖ የቆየና ታሪካዊ ይዘትም ያለው ተቃርኖ መሆኑን የሚያመላክቱ ብዙ ነገሮች አሉ። የሁለቱ ክልል ባለሥልጣናት ችግር ወደፊት እስኪፈታ ድረስ ግን አወዛጋቢ የሆኑት እና የማንነት ጥያቄ የተነሳባቸው አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሔ እስኪያገኙ ድረስ በፌደራሉ መንግስት እንዲተዳደሩ እና በሥፍራዎቹም ላይ የፌደራል ልዩ ኃይል እንዲሰፍር ማድረግ ግጭቱን በተወሰነ ደረጃ ሊቀንሰው ይችላል።
– በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ ቦታዎች ላይ በተለይም ግጭቶቹ በተከሰቱበት ሥፍራም የፌደራል መንግስቱ ሊቆጣጠራቸው ይገባል። በአካባቢው ላይ የሚንቀሳቀሱትን ታጣቂ ቡድኖች በቁጥጥር ስር ማዋል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።
– በኦነግ ስም ተደራጅተው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እየተባለ የሚገለጹት ኃይሎች ላይም መንግስት ተመሳሳይ እና ተመጣጣኝ እርምጃ ሊወስድ ይገባል።  እነዚህን ኃይሎች ለመቆጣጠር የሚወሰደውን እርምጃ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችም ድርጊቱ ሕገ ወጥ ተግባር መሆኑን ተረድተው ሊታቀቡ ይገባል። ካልሆነም ግን ይህ ሕገ ወጥ ተግባር ሥለሆነ በሕግ ጥላስር ሊወድቁ ይገባል።
-በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሕዝብ ባለፉት ሦስት ቀናት በሰላማዊ ሰልፍ ላነሳቸው ጥያቄዎችም እንዲሁ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት ይገባል።
ሕዝብም መንግሥት ሰላምን ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት ከማደናቀፍ ወይም በታዛቢነት ዳር ቆሞ ከማየት የግጭት ተሳታፊ ባለመሆንም ሆነ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ የሚደረጉ ጥረቶችን በመደገፍ ለመንግስት እገዛ ሊያደርግ ይገባል። ዞሮ ዞሮ በሰላም እጦት የመጀመሪያው ተጠቂ የአካባቢው ሰው ነው።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic