>
4:38 pm - Sunday December 3, 5758

ከሽምግልናው ጎን ለጎን!  (ቹቹ አለባቸው)

ከሽምግልናው ጎን ለጎን! 
ቹቹ አለባቸው
ሰሞኑን  በጎንደርና አካባቢ በሁለቱ ወንዳማመች ህዝቦች መካከል የተከሰተው ደም አፋሳሽ ግጭት፤ በተወሰነ መልኩ መቀዝቀዝ የታየባቸው አካባዎች ቢኖሩም በአንዳንድ አካባዎች ደግሞ በአስከፊነቱ መቀጠሉን ሰምቻለሁ፡፡
በመተማ መስመር 3 ያህል ሰዎች ሲገደሉ፤ ከአርማጭሆ ወደ ዳዋና ጨንጮቅ የተሻገረ አርሶ አደርም ባደረገው ግጭት ገድሎ መሞቱን ሰማሁ፡፡ ብቻ ልብ ይነካል፡፡ ሕወሀት ጦርነቱን እዛው ቤታችሁ ድረስ እንልክላችኋለን ያለችውን አባባሏን ተገበረችብን፤ እኛ ግን ሁሉን ነገር በሰላም መፍታ ይሻላል ብለን፤ተመሳሳዩን ጦርነት እዛው ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ጠለምትና ራያ ላይ እንዲቀጣጠል አላደረግንም፡፡ መነሻችንም፤ጉዳዩ በሰላም ይፈታል ከሚል ነበር፤ግን አልሆነም፡፡
ያም ሆነ ይህ በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ዘንድ እየተከሰተ ያለው ደም አፋሳሽ ግጭት በፍጥነት ሊቆም ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁላችን ልባዊ ጥረት እጅግ አስፈላጊ ነው፤የራሳችንን ውስጣዊ አቅም ነው እያዳከምን ያለነው፡፡ ይህ ማለት ግን ልክ እንደ እስከዛሬ በመጠናንበት መንገድ መለሳለስ ያስፈልጋል ማለት አይደለም፤በፍጹም ሊሆን አይገባም፡፡ ሁለቱን ህዝቦች ማጋጨት ስራየ ብለው የተሰማሩ ወገኖች ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መታደንና ለህግ መቅረብ አለባቸው፡፡ ስለዚህ ከሁሉ በፊት መቅደም ያለበት ስራ፤በዚህ እኩይ ድርጊት ውስጥ ስለመሳተፋቸው፤ከሁለቱም ወገን የሚጠረጠሩ አካላትን በሙሉ ለቅሞ በስም ዝርዝር መያዝ፤ቀጥሎ ተጨባጭ ወንጀል ውስጥ ስለመግባታቸው ማስረጃ ማፈላለግ፤ይህ ከተከናወነ በኋላ ደግሞ ለሚመለከተው አካል መረጃ ማድረስ፡፡
 በዚህ በኩል የጎንደር ከተማ ወጣቶች በተደራጀ መልኩ እየሰሩ እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ አወ እንዲህ ነው መሆን ያለበት፤ዝም ብሎ መጮህ ሳይሆን፤ ትልቁ መፍተሄ ወደ ገደለው መግባት ነው ፡፡ በርግጥ እነዚህን በወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎች ስም ዝርዝር ስታወጡ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤በስመ ቅማንት ንጹሀን ወንድሞቻችንን ስሜትም እንዳንነካ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፤ሰሞኑን በጎንደር ዩኚቭርስቲፕሬዝዳንትና አንዳንድ ግለሰቦች ላይ የታዘብኩት ነገር፤አሁንም መደማመጥ የቀረን መሆኑን ነው፡፡
የቅማንትና አማራ ጉዳይ የሚፈታው ካሁን በኋላ በመንግስት ውሳኔ አይመስለኝም፡፡ መፍትሄው ያለው በሁለቱ ወንድማማቾች ህዝቦች ሽማግሌዎች እጅ ብቻ ነው፤ሁኔታው በነዚህ ወገኖች እጅ ወድቋል፤ ነገሩ ከመንግስት እጅ ወጥቷል፡፡ በዚህ በኩል መንግስት ታማኝነት ክፉኛ ተሸረሸረ መስሎ ይሰማኛል፡፡ ስለሆነም፤ከሁለቱም ወገን ሽማግሌዎች መሰማራት አለባቸው፡፡ በርግጥ የአካባቢው ህዝብና የክልሉ መንግስት ይሄንን እያደረጉ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡
ለምሳሌ ከ2 ወር በፊት የጎንደር ህዝብ ተሰባስቦ ከ20 በላይ ሽማግሌዎችን መርጦ አስማርቶ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ 14 (ከቅማነት 3፤ከአማራ 3፤ከእስልማናና ኦርቶዶክስ እምነቶች 6፤ ከሴቶች 2) ሽማግሌዎች ተለይተው ወደ ስራ ለመግባት እየሞከሩ ነው፤ግን ፈራ ተባ እያሉ ነው፡፡ ቢፈሩ አያስገርምም፡፡ ሌላ መፍትሄ ግን የለም፡፡ ስለሆነም፤ሽምግልናው ይቀጥል፤ግን-ግን በአንድ ነገር እንግባበባ፡፡ ይሄውም ምን አይነት ሽምግልና? በሚለው ነጥብ ላይ፡፡
የቅማንት ማንነት ከተነሳበተት ወቅት ጀምሮ፤ የተነሱትን ግጭቶች ለማብረድ ምን ያክል ጊዜ ለሽምግልና ተቀምጠናል? ብዙ ጊዜ! ግን ለምን መፍትሄ አልመጣም ? ስለሆነም፤አሁን በሽምግልና የተሰማራችሁ ወገኖች፤ዘላችሁ ወደ ሽምግልና ከመግባታችሁ በፊት፤እነዚህን ነጥቦች መርምራችሁ፤አጥጋቢ መልስ አግኝታችሁ ነው ስራችሁን መጀመር ያለባችሁ፡፡ እስከዛሬ አደረግናቸው ያልናቸው አርቆች፤ውጤት ማምጣት ያልቻሉት፤ላይላዩንና አደረግን ለማለት ብቻ የሚካሄዱ ስለነበሩ ነው፤አሁን ይሄንን ስህተት መድገም የለብንም፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ልንፈታ ከሆነ፤ከስሩ መነጋር አለብን፤ላይላዩንና የማያዛልቀውን ነገረ ብንነጋገር ተመልሰን እዛው መሆናችን አይቀርም፡፡
ለሁሉም ሽማግሌዎቻችን፤ስታሸማግሉ የሚከተሉትን መሰረታዊ ነጥቦች አደራ ተመልከቷቸው፡-
1.አሁን አትቸኩሉ፤ነገሮች ሰከን ይበሉ፤ነገሮች ወደ ነበሩበት ሲመለሱ ብቻ የሽምግልና ጥረት ይጀመር፡፡ አሁን ከሁሉ በፊት፤ወንጀለኞች ታድነውና ተለቃቅመው ይያዙ፡፡ከዚያ ወደ ስራ ትገባላችሁ፡፡
2.በሽምግልና ጥረታችሁ ሁሉ፤ የአማራ ህዝብ የቅማንትን ማንነት፤ከልብ እንደሚቀበል( አልቀበልም አላለም) በደንብ ስሩበት፡፡ ሊበለጽግና ሊነቃቃ የሚችል የቅማንት ራሱን የቻለ ባህል፤ወግና ታሪክ እንዲሁም ቋንቋ ካለ፤ ከቅማንት ወንድሞቻችን ጋር ሁነን በጋራ አብረን የምናሳድገው ሀብት መሆኑን አማራ ከልብ እንደሚያምን ለቅማንት ወንድም/እህቶቻችን መልእክት አስተላልፉ፤
3. የቅማንት ወንድሞቻችን ደግሞ፤ የአስተዳደር ወሰን የሚለውን ጥያቄ እንዲያነሱ ምከሯቸው፡፡ የቅማንት ህዝብ የሚጠቀመው ከአማራ ወንድሙ ጋር በደንበር ተካልሎ ሳይሆን፤ደንበር የለሽ ግንኙነት ከኖረው ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም፤ ይህ የአስተዳደር ወሰን የሚባል ነገር እንዲቀር እመክራለሁ፤ግድ የላችሁም ምክሬን በቅንነት እንየው፡፡ ከዚህ ውጭ ቅማንትና አማራ በደንበር ተካልለው በሰላም ስለመኖራቸው፤እጅግ ሲበዛ እጠራጠራለሁ፡፡ ቅማንትና አማራ ደንበር አያስፈልጋቸውም፤እንዲህ ለመኖር ቢሞክሩም አያምርባቸውም፡፡ ስለሆነም ሽግሌዎች በተቻላችሁ መጠን እነዚህን  ነጥቦች መዝግቡልኝ፡፡
4.በሁሉም የሰላምና እርቅ ውይይቶች ወቅት፤ቅድሚያ ለሁለቱም ህዝቦች ወጣቶች ስጡ፡፡ ካድሬና አመራር፤ሸህና ቄስ ብቻ ተሰባስቦ የሚመጣ ውጤት የለም፡፡ እንደዛማ ቢሆን እስከዛሬ ድረስ ስንት ቄስና ሸህ፤ካድሬና አመራር ይዘን ስንቴ ተሰባሰብን? ውጤቱ ግን ያው ነው፡፡ ስለሆነም፤ እነዚህ አዛውንቶች፤ቄሶችና ሸኮች፤እንዲሁም አመራሮች በመካሪነት ሚናቸው ዛሬም የምንፈልጋቸው ሆኖ፤ በዋነኛነት ግን ትኩረት ለወጣቶች ይሁን፡፡ ይሄም ሲሆንም ጎንደር ከተማ ላይ ብቻ ሳይሆን ወደ ገጠሮቹ ከተሞችም ወጣ በሉ፡፡
መልእክት ለአማራ ህዝብና ወጣት፡- 
ወቅቱ ከባድ ነው፡፡ ሕወሀት በልቧ፤ወደ ወልቃይት፤ጠገዴና ጠለምት፤እንዲሁም ራያ የምናደርገውን የሰላማዊ ትግል ጉዞ፤እዚሁ ቤታችን ታስረን እንድንቀር አስባ እየሰራች ነው፡፡ አኛ ግን በሷ ወጥመድ ታስረን  እነዚህን የሞትንባቸውን ርስቶቻችንን ጉዳይ  መቸም ቢሆን የምንረሳ አንሆንም፡፡ አሁን በአጭሩ፤የቤታችንን ጣጣ ጨርሰን  ሁሉም ነገር ወደ “ሰሜን ግንባር” እንላለን፤ግን ሰላማዊ ትግል ነው፡፡ በነገራችን ላይ በአንዳንድ የአማራ ወጣቶች  ዘንድ መጨናነቅ አያለሁ፡፡ይሄውም አሁን ከቅማንት ጋር የገባንበትን ፈተና፤ህወሀት በግላጭ ቢጨመርበት ነገሩ ይከብደን ይሆን ሲሉ በተጋጋሚ ይጠይቁኛል፡፡ መጨነቁ ጥሩ ነው፡፡ ግን- ግን እንዴት ነው የአማራን አቅም የምንመዝነው? አማራ እኮ አማራ ነው! እንዲያው አበአሁኑ ወቅት ያለው የአማራ ትውልድ ቢያንስ በትንሹ በ2 /3 ግንባሮች በአንዴ ፈተና ቢገጥመው፤እነዚህን ፈተናዎች ባንዴ መመከትና ክብሩን ማስመለስ ካልቻለ እማ ምኑን አማራ ሆነው? እናማ ብዙም መጨናነቅ አያስፈልግም፡፡
 እነ ዶክተር ደ/ጺወን መቀሌ ላይ ህዝባቸውን ሰብስበው ሲያለቅሱ ሲውሉ፤ አቶ ገዱና ቡድናቸው አሜሪካ ላይ ሁኖ ሰላማዊ ስራውን ሲሰራ ሚውል ለምን ይመስላችኋል? በርግጥ ቢያንስ እሱ እንዲመላ መክሬ ነበር፤ግን አቶ ገዱ ያለውን ውስጣዊ አቅም ስለሚያውቅ፤በነ ደ/ፂወን ስራ እሳቀ ስራውን አሜሪካ ውስጥ ይሰራል፡፡ አቶ ገዱ የተከዜ ማዶ ሰዎችን በጣም ንቋቸዋል፤እንደዛማ ባይሆን ኖሮ፤ጦርነት ሲያውጁበት ደንገጥ ብሎ ተሎ ይመለስ ነበር፡፡ ብቻ እኛ እንደነ ደ/ጺወን በአደባባይ ስላለፈለፍን፤አቅም የሌለን እንዳይመስላችሁ፤እጅግ ኋይለኛ አቅም  አለን፡፡ እንዲያም ሲል ደግሞ፤ አማራ የነደጀኔ ማሩ ፤ኮ/ል ደመቀ፤ የነማስረሻ ሰጤ፤ሰፈር መለሰ  ወዘተ… መንደር መሆኑንም አትርሱ እንጅ?
ለሁሉም፤ ራሱን የቅማንት ኮሚቴ ብሎ ሚጠራው ቡድን ዛሬም ወደ ቀልቡ ተመልሶ፤ ሰላምን በማስፈን ሂደቱ እንዲሳተፍ እንመክራለን፡፡ ነገር ያበላሹ ደግሞ በህግ ይዳኛሉ፡፡ አማራ ግን ወለም ዘለም አትበል፤እድሉ በእጅህ ነው፡፡ አንተን እንደ ቅማንት ኮሚቴ፤መሳሪያና ጥይት የሚልክልህ  የውጭ እረዳት የለህም፤ ስለሆነም፤ሁሉን ነገረ በቁጠባ ተጠቀም፡፡ አሁን መንግስት በፈቀደው መሰረት ደግሞ ትጥቅህን አስመዝግብ፤ አራት ቀን ሲበዛ በቂ ነው፡፡ ምንድን ነው ደግሞ መንግስትን ማሰቸገር?ሌላ ስራ ቢኖርህም እርግፍ ብሎ ይቅር፤መጀመሪያ መሳሪያህን ህጋዊ አድርግ፤ከዚህ በለጠ ወቅታዊ ስራ የለህም፡፡ መንግስትንም ማስቸገር ጥሩ አይደለም፡፡
እስኪ ቸር ያሰማን!
Filed in: Amharic