>
5:13 pm - Monday April 19, 5030

አዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ያስፈልጋታል? ለምን? (ብርሀኑ ተክለ ያሬድ)

አዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ያስፈልጋታል? ለምን?
ብርሀኑ ተክለ ያሬድ
ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ፈቃድ ተከልክሎ ጠያቂዎች የሚታሰሩበት ብሎም አደርጋለሁ አታደርግም በሚል እሰጥ አገባ የሰው አካል የሚጎድልበትና ባስ ሲልም የሰው ህይወት የሚጠፋበት ዘመን አልፎ ዛሬ ከፋኝ ያለ ሰው ተነስቶ ያለ ምንም የበሰለ ሀሳብ ሰልፍ በመጥራት በአደባባይ ያልመለሰውን ሀሳብና ግለሰብ ሊዘልፍና ሀገር ለመበታተን ሲዝት ወደሚውልበት ዘመን ተሸጋግረናል ይህ የሰልፍ ስካር ጅምሩን “ለውጥን እንደግፍ ዴሞክራሲን እናበርታ” በማለት ለዶ/ር አቢይ ድጋፍ ለመስጠት ከተዘጋጀው የአዲስ አበባው ሰልፍ አንስቶና ሀገሪቷን አካሎ ህጻናትን የጦር መሳሪያ አስታጥቆ የሚሸለልበትና የህጻን ብሽሽቅ አይነት ስድብ እና ፉከራ የታየበት የመቀሌው ሰልፍ ድረስ ተጉዟል፡፡
ይህ የመቀሌሰልፍ በተካሄደ ማግስት ደግሞ የአዲስ አበባን ህዝብ አደባባይ አውጥቶ ለውጡን የሚያደናቅፉ ሀይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ በሚል ስበብ “ብሽሽቁን ለማስቀጠል” የሚመስል ሰላማዊ ሰልፍ በመስቀል አደባባይ ለማካሄድ አንዳንድ ወዳጆቻችን የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ደብዳቤ ለሚመለከተው አካል ማስገባታቸውን እየነገሩን ነው፡፡
በኔ እምነት የመቀሌው ጫጫታና ፉከራ ሀገር እንደማያፈርስና ከልኩ እንደማያልፍ ሁሉ የአዲስ አበባው የውግዘት ሰልፍም ህግን አያስከብርም ሀገር የምትረጋጋውም ሆነ ህጋዊ ስርአት የሚመሰረተው በሰከነና ሁሉን ባሳተፈ ሀገራዊ ንግግር እንጂ በድጋፍ ጫጫታ አይደለም፡፡
ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጅተናል የሚሉ ወገኖችም ቆም ብለው ሊመልሷቸው የሚገባቸው ጥያቄዎችን ሰከን ብለው ሊያስቡ ይገባል ሰልፉ ለምን አስፈለገ? ከሰልፉስ ምን ይገኛል? እንደተባለው ሰልፉ ቢካሄድና የጥፋት ሀይሎች (በዚህም በዚያም ያሉ) በሰልፉ መካከል ሁከት እንዲነሳ ቢያደርጉ አልያም እንደተለመደው የሽብር ተግባር ቢፈጸም ማን ሀላፊነቱን ይወስዳል?አዲስ አበባ ላይ ሰልፍ ማድረግ አስፈላጊ ከሆነስ “ለውጡን መደገፍ” ከሚባል የአጨብጫቢነት አጀንዳ በላይ የአዲስ አበባን ህዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎችና ተፈናቅለው ሜዳ የወደቁ ግፉአንን ድምጽ ይዞ መውጣት ማንን ገደለ? በእነዚህና በሌሎች የማይመለሱ ጥያቄዎች ምክንያት ለእኔ እምነት እየተጠራ ያለው ስልና አስፈላጊ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ወጣትም የመሪዎች የድጋፍ ሰልፍ አስተባባሪ፣ የጎጠኞች ፈንጂ አምካኝ፣ ገዢዎች በደነገጡ ቁጥር ጦላይና ዴዴሳ የሚያግዙት ከሁሉም በላይ ደግሞ ከሰልፍ ትርፍ የሚያገኙ ሰዎች የቤት ኪራይ ከፋይ የሚሆንበት ጊዜ ማብቃት አለበት ባይ ነኝ፡፡
Filed in: Amharic