>

የዘገየ ፍትሕ ብቻ ሳይሆን የዘገየ ከንፈር መጠጣና ሃዘንም አጥንት ይሰብራል!!! (ያሬድ ሀይል ማርያም)

የዘገየ ፍትሕ ብቻ ሳይሆን የዘገየ ከንፈር መጠጣና ሃዘንም አጥንት ይሰብራል!!!
ያሬድ ሀይል ማርያም
መንግስት የጀመረውን ፍትሕ የማፈላለግ ሥራ በርትቶ እንዲገፋበት ዛሬም ብጠይቅም፤ የግፉአንን በደል ለፖለቲካ ቁማር መቆመሪያ ለማዋል የሚደረጉ አንዳንድ እሩጫዎች ግን ከወዲሁ ሊገቱ ይገባል!
ግፍ በመንግስት አፍ ካልተነገረ የማያምነው ወገናችን የትላንቱን አንድ ሰዓት የማይሞላ የሰቆቃ ድምጽ ሰምቶ አገር ይያዝ ይለቀቅ ማለቱ ቢያስገርመኝ የጫርኩት ነው።  ትላንት በመንግስት ቴሌቪዥን ሥርዓቱ በንጹሐን ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን አስነዋሪ ተግባራት ስትሰሙ ቡዙዎⶭ ደንግጣችዋል፣ አልቧችኋል፣ አንብታችኋል፣ ተቆጭታችኋል፣ ፎክራችኋል፣ ዝታችኋል፣ ሰው ሆኖ መፈጠርን ጠልታችኋል፣ የፍትህ ያለህ ብላችው መጮህ ጀምራችዋል፣ ለተጎዶ ሰዎች መዋጮ ማሰባሰብ ጀምራችዋል። እንዲህ አይነት ጉድ እየሰሙ ማዘን፣ መቆጨት እና ማንባት ሰዋዊ ባህሪ ስለሆነ ምንም አያስገርምም። ያስገርም የነበረው ባታዝኑ እና ባትናደዱ ነበር።
እኔን ግን ግራ የገባኝ እና በአእምሮዮ ውስጥ እየተመላለሰ የሚመጣው የሕዝባችን ባህሪ ነው። ሕዝባችን ከመንግስት ሌላ ማንንም አያምንም ማለት ነው? ወይስ ለመናደድ፣ ለማዘን እና ሃዘንንም ለመግለጽ የመንግስትን ፈቃድ ይጠብቃል?
እስቲ ትላት በቴሌቪዥን ከሰማችሁት ውስጥ ሙኑ ነው አዲስ ነገር? ይህ ሥርዓት እኮ እነዚህን እና ሌሎች ከዚህም የከፉ ወንጀሎች ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት ሲፈጽም ነው የኖረው። ድርጊቶቹም በድብቅ አይደለም የተፈጸሙት። ኢሰመጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ይህን መሰል መግለጫዎች አውጥቶ ለሕዝብ እና ለመንግስት ሲያጋልጥ ነው እኮ የኖረው። በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን፤ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢሳት የሰብዓዊ መብቶች ፕሮግራም ላይ የቀድሞ ባልደረባዮ ወንድማገኝ ጋሹ በተመሳሳይ ሁኔታ ሲያቀርባቸው የነበሩ ጉዳዮች ናቸው። ጺዮን ግርማ ለአመታት በቬኦኤ እነዚህን ችግሮች እኮ አጥንት ሰርስሮ በሚገባ አቀራረብ ሲትገልጽልን ኖራለች። ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ለአመታት ይህን ሰቆቃ ሳይታክት ሲገልጽልን ነበር። አንሰማ ብንለው በመጽሐፍ መልክ አሳትሞ አቀረበልን።
መንግስት የጀመረውን ፍትሕ የማፈላለግ ሥራ በርትቶ እንዲገፋበት ዛሬም ብጠይቅም፤ የግፉአንን በደል ለፖለቲካ ቁማር መቆመሪያ ለማዋል የሚደረጉ አንዳንድ እሩጫዎች ግን ከወዲሁ ሊገቱ ይገባል።
ለማንኛውም በጥያቄ ሃሳቤን ልቋጭ፤
ሕውሃት ተደምራ እና ሰጥ ለጥ ብላ አዲሱን አስተዳደር ተቀምላ ከበሮዋን እየደለቀች በደስታ በባቡሩ ላይ ተሳፍራ ቢሆን እነኚህ በደሎች ዛሬ በምናያቸው መልኩ በመንግስት ሚዲያዎች ይቀርቡ ነበር ወይ? እነዚህ እርምጃዎች የሚወሰዱት የህውሃትን ድንፋታ ለማርገብ እና ለማንበርከክ ወይስ ፍትሕ ፍለጋ?
የግፉዋን ስቃይ እና የፖለቲካ ቁማር እየተደበላለቀ የመጣ ስለመሰለኝ ነው።
Filed in: Amharic