>

“ግፍ ሰርቶ መደበቅ፤ ዘርፎ መንደላቀቅ አይቻልም!!!” (ዶ/ር ዐቢይ አህመድ)

“ግፍ ሰርቶ መደበቅ፤ ዘርፎ መንደላቀቅ አይቻልም!!!”
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ
ኢ.ቢ.ሲ

”የግፍ ቀዳዳዎችን መድፈን፣ ሕጎችን ማሻሻል፣ አሠራሮችን ማስተካከል፣ ተቋማትን ማብቃት፣ የዝርፊያን እና የአምባገነን በሮችን መዝጋት አለብን!!!

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ዛሬ አመሻሹ ላይ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በመልዕክታቸው መግቢያ ላይ ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የለውጥ ጉዞ ላይ መሆኗን ያስታወሱ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አምባገነናዊ ሥርዓትን የታገለው ግፍ እንዲቆም፣ ፍትሕ እንዲሰፍን እንጂ ሌሎች ግፈኞችን ለመተካት አይደለም ብለዋል። የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር የሚቻለው ሰብአዊ መብቶችን የማስከበር እርምጃ በግለሰቦች ፍላጎትና ይሁንታ መመራቱ ቀርቶ ‘የጋራ ፍላጎታችን በወለዳቸው’ ተቋማት መመራት ሲጀመር ነው ብለዋል።

”. . . ሀገር የሚዘርፉ ጁንታዎች በኩራት በከተሞቻችን እየተንፈላሰሱ ሕግ ያልፈረደባቸው ዜጎች . . . ግፍ ይፈጸምባቸው ነበር። . . . በፖሊስ፣ በደኅንነት፣ በፍርድ ቤቶች፣ በማረሚያ ቤቶች . . . የሚገኙ ባለስልጣናት ፈቃጅነትና መሪነት፤ ኀሊናቸውን ሽጠው ለሆዳቸው ባደሩ የግፍ ሠራዊት ተላላኪነት በዜጎቻችን ላይ አራዊት የማይፈጽሙት ሰቆቃ ይወርድባቸው ነበር። ግፍ ፈጻሚዎቹ ከሳሽም፣ ምስክርም፣ መርማሪም፣ አሣሪም፣ ዐቃቤ ሕግም፣ ዳኛም ሆነው የግፉን ድራማ ተውነውታል።” በማለት ጠንከር ባሉ ቃላቶች ከዚህ ቀደም በመንግሥት ኃይሎች ይፈጸሙ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ኮንነዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በባለ ሶስት ገጽ መልዕክታቸው ለሞራል ድንጋጌዎች ከፍተኛ ቦታ የሚሰጥ ማኅበረሰብ አለን ያሉ ሲሆን። ”ታዲያ እነዚህ ሰዎች እንዴት ነው ይሄንን ሁሉ ግፍ ሊፈጽሙ የቻሉት?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ግፍ ፈጻሚዎች ናቸው ላሏቸው ግለሰቦች ሶስት ምላሽ መስጠት አለብን ይላሉ። እነዚህም፤ ጥፋተኞችን ለፍርድ ማቅረብ፣ ዳግም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም አስተማማኝ ስርዓት መዘርጋት እና ”ሶስተኛው ከእነርሱ የተሻለን መሆናችንን በተግባር ማሳየት ነው።” ብለዋል።

ግፍ ፈጻሚዎቹ ይህን ሁሉ ግፍ የፈጸሙት ምንም ሳይመስላቸው በልተው ተኝተው እያደሩ ነበር የሚሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ”እኛ ግን ግፉ ይሰቀጥጠናል፣ ያመናል፣ ዕረፍት ይነሳናል።” ብለዋል።

”የግፍ ቀዳዳዎችን መድፈን፣ ሕጎችን ማሻሻል፣ አሠራሮችን ማስተካከል፣ ተቋማትን ማብቃት፣ የዝርፊያን እና የአምባገነን በሮችን መዝጋት አለብን።” ይላል መልዕክታቸው።

”በምንም መልኩ ግፈኞቹ ራሳቸውን እንጂ፣ የበቀሉበትን ሕዝብ ግፋቸው እንደማይመለከተው እናምናለን። የትኛውም ብሄር ወይም የትኛውም ዘር ግፈኞችን፣ ገራፊዎችንና ጨቋኞችን ሊያበቅል ይችላል። . . . ግለሰቦች ባጠፉ የምንቀየመው ወይም ጣት የምንቀስርበት ብሔር አይኖርም። . . . ወንጀለኛ ራሱን ችሎ ወንጀለኛ ለመሆን ከምንም ጋር መለጠፍ እና ማንም ላይ መደገፍ አያስፈልገውም። . . . ግፍ የሠራው ሰው የሚናገረው ቋንቋ ኦሮምኛ ቢሆን ኦሮሞውን፣ ትግሪኛ ቢናገር ትግሬውን . . . የሚወቅስ ሰው ካለ እሱ ከታሪክ የማይማር ደካማ ነው። . . . ለአንድ ገጽ ብለን መጽሐፍ የምንቀድ ሞኞች አይደለንም። . . . ሁሌም ማወቅ ያለብን ነገር ቢኖር፤ ወንጀለኞቹ ሊደበቁበት ከሚፈልጉት ብሔርን ነጥለን ማየትና እስከመጨረሻው ለፍርድ ማቅረብ እንደሚገባን ነው።”ብለዋል።

በመጨረሻም “ቂምና በቀልን ልናስበው አይገባም፤ ፍርድና ፍትሕን እንጂ። ይህን ሁሉ የምናደርገው እንደ እነርሱ ከጥላቻ ተነሥተን ሳይሆን የሕግ የበላይነት መስፈን ስላለበት ነው።

ወንጀለኞቹ ማንም ይሁኑ ማን፣ ከየትኛውም ብሔር ገብተው ይደበቁ፣ የትኛውም ወገን ይጩህላቸው፣ በወንጀል እስከተጠረጠሩ ድረስ ካሉበት አድነን ለሕግ ማቅረባችን አይቀሬ ነው” ይላል የጠቅላይ ሚንስትሩ መልዕክት።

Filed in: Amharic