>
8:20 pm - Wednesday February 8, 2023

የማለዳ ወግ ... የሞሚና እንባ ! [ነብዩ ሲራክ]

በኮንትራት ስራ ስም ወደ አረብ ሃገራት የሚመጡ እህቶቻችን በተደጋጋሚ በግፍ ሲበደሉ ማየት እየተለመደ መጥቷል። በደል ሲደርስባቸው ወደ ፍትህ ፊት ቀርበው ፍትህ እንዲያገኙ አያደረግም። ዜጎች በአሰሪዎቻቸውና በስራ ላይ እንዳሉ ጉዳት ሲደርስባቸው በቂ ህክምና እንዲደረግላቸውም ሆነ ለተጎዱበት ካሳ እንደዲያገኙ አይደረግም። ይህ ሁሉ ቀርቶ ምንዱባን ጉስቁል አህቶች ቁስል ጉዳታቸው ይዘው ፍትህ ርትዕ ተነፍጓቸው የወላጅ ዘመድ እዳ ሊሆኑ ወደ ሃገር በግፍ ይሸኛሉ። ከሁሉም የሚያሳዝነው ይህ የሚሆነው በሳውዲ አረቢያ የሚገኙት የጅዳ ቆንስል እና የሪያድ ኢንባሲ ዲፕሎማቶች ባሉበት ሰማይ ስር መሆኑ ነው !

ተወካዮቻችን በኮንትራት ስራ ስም ሰራተኛና አሰሪን ያዋውላሉ። ሰራተኛው የሚጠበቅበትና አሰሪው ሊያከብር የሚገባው በውሉ በግልጽ ተቀምጧል። የአሰሪው መብት በሰራተኛው ባይጣስም አሰሪው የሰራተኛውን መብት እንዳሻው ይጥሰዋል። ሃላፊዎቻችን ይህ ሲሆን አሰሪው ማክበር ያለበትን ግዴታ በትክክል መወጣቱን ተቆጣጥረው መብታችን ስለማያስከብሩ በደል በዝቷል። ሃላፊዎቻችን የዜጎችን መብት ለማስከበር መቆጣጠሩ ቀርቶ አቤቱታ ሲደርሳቸው መፍትሔ አያመጡም። የዜጋቸው የተጎጅ የተተለተለ ገላን እንደ ተጨባጭ መረጃ ቀርቦላቸው እንኳ የሚወስዱት እርምጃ ባለመኖሩ በተለይም የኮንትራት ሰራተኞች ሰቆቃ የሚያቆም አልሆነም።

የመንግስት ተወካዮች ሰራተኛና አሰሪን ለማዋዋላቸው ውለታ የወሰዱትን ጠቀም ያለ ገንዘብ ያህል እንኳ ለዜጎቻቸው መብት አይተጉም። ይህ በመሆኑ በእህቶቻችን ላይ ግፍ ይፈጸምባቸዋል ፣ ፍትህ ርትዕን ይጎልባቸዋል፣ ይህ ሁሉ ሆኖ በደላቸው ተሸፋፍኖ ወደ ሃገር ቤተሰቦቻቸው ሳይወዱ በግድ ይሸኛሉ ! መብታቸውን የሚያስከብርላቸው እያጡ ሰብዕናቸው እየተዳጠ የሚላስ የሚቀመስ ወደ ሌለው ቤተሰብ ይላካሉ ! ተመልከቱት ግፉን !

ወላጅ ሲጨንቅ ሲጠበው ስሟን ማንቴስ ብሎና እድሜዋን ቆልሎ ወደ አረብ ሃገር የላካት ልጁን በደል ተፈጽሞባት ” አተርፍ ባይ አጉዳይ” ሆና ትመላስለታለች። “ወርቅ” ልታፍስ የሄደች ልጁ ከአረብ ሃገር ስትመለስ በቂ ጥሪት ቋጥራ ፣ የአራጣ ብድሯን ልትከፍል ፣ አምራ ፣ ደምቃ ፣ ተውባና ተሸቆጥቁጣ መሆኑ አይደለም። መሔዷን እንጅ መመለሷን በማታውቅበት ደረጃ እንጅ … ወላጅ የልጁን የነተበ ሬሳ በቃሬዛ ፣ የተጎዳውን የስንኩል ልጁን ገላ ከእነ ትኩስ ቁስሉ ይቀበል ዘንድ ግድ ብሎታል። እየሆነ ያለው ይህ ነው !

የሚያመው እንቅልፍ የሚነሳው ድምጻቸውን የሚሰማው ጠፍቶ እስከ ወዲያኛው የሚሸኙትን የአገብ ሃገር ግፉአን ስደተኞች አሳዛኝ ፍጻሜ ነው። በዚህ መንገድ የተሸኙትን ይቁጠረው ከማለት ባለፈ ብዙ ማለት አልችልም 

እንዲህ ሆነ ስንል መረጃ ስናቀብል ” የተዛባ መረጃ ነው! ” ማለት የሚቀናቸውን የመንግስት ሃላፊዎች እና አደግዳጊ ጭፍን ካድሬዎች ግን ያሻችሁን አድርጉኝ እውነቱን እነግራችኋለሁ ! በጸጸይ ልትነዱ ፣ ልታዝኑ እና ልታፍሩ ይገባል !

ሞሚናን አዲስ አበባ ባልቻ ሆስፒታል በማስገባት ፣ መረጃውን በማህበራዊ ድህ ገጾች በማሰራጨት ለረዳችሁ ፣ ሞሚና በደል ለማያምኑት የምስክርነት ቃል ለሰጣችሁ ሁሉ አክብሮት አለኝ ! እግዚአብሔር ውለታችሁን ይክፈለው! እነሆ ዝናንተ ከጸጸት ትድናላችሁ ! ልድገመው በጸጸት የሚነዱት ግን ይንደዱ …

የዛሬ የሞሚናና የወላጆቿ እጣ ከላይ ከጠቀስኩት ውስጥ አንዱን እውነታ ቁልጭ አድርጎ ያሳይ ይመስለኛል። ብቻ በግፍም ቢሆን ከቤተሰብ ከሃገሯ ሰው ጋር መቀላቀሏ መልካም ነው እንበለው። ዛሬ የሞሚናን አሰቃቂ ምስል ለጥፊ እያሳቀቅኩ ሞሚና ምንም ከሌላቸው ካጡ ከነጡ ወላጆችዋ እጅ ወድቃለችና ልንደግፋት ግድ ይለናል አልላችሁም። የእህታችን አበሳ እንዲህ በተጨባጭ እያየንና እየሰማን ለነፍሳችን ስንል ከንፈራችን ከመምጠጥ ባለፈ የሚታይ የሚጨበጥ የድጋፍ እርዳታ ልናደርግላት ይገባል !

ባይደላኝ ባይሞላልኝም ፣ እኔም እንደ ዜጋ ድጋፉን ከራሴ እንደምጀምር ግን አትጠራጠሩ !

የሞሚናን እንባ እኛ ካልጠረግነው ማን ይጥረገው?

ቸር ያሰማን !

ነቢዩ ሲራክ

ሞሚናን ለመርዳት የተከፈተው የባንክ ሂሳብ ይህ ነው…

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር 1000086268877
የቻሉትን ይለግሱ! 
Filed in: Amharic