>

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በ95 አመታቸው አረፉ!

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በ95 አመታቸው አረፉ!
ጌጡ ተመስገን
* ለ12 ዓመተታት ያህል ሀገራችንን በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል
 * ከሁለት ሳምንት በኋላ ታህሳስ 19 በመኖሪያ ቤታቸው 95ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን በደማቅ ስነ ስርዓት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነበር፡፡
* ዛሬ በሀርመኒ ሆቴል በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ቀጠሮ ነበራቸው
     ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ታህሳስ 19 ቀን በ1917 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ፤ በልጅነታቸውም የቤተክህነት ትምህርት ከተማሩ በኋላ፣ በ1926 ዓ.ም. በተፈሪ መኮንን ትምሕርት ቤት ገብተው እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ ዘመናዊ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡
መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ከመስከረም 28 ቀን 1994 ዓ/ ም ጀምሮ ለሁለት ዙር እስከ መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ/ም የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉ አዛውንትና ከዘውድ ስርዓት ጀምሮ በደርግ እና በኢሕአዴግ መንግሥት የሠሩ የቀድሞ ወታደር ናቸው። መቶ አለቃ ግርማ ኦሮሚኛ፣ አማርኛ፣ አፋርኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ጣሊያንኛ እና ፈረንሳይኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ።
ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በ1930-33 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያትም በአዲስ አበባ “ዘ ስኮላ ፕሪንሲፔ ፒዮሞንቴ” በተባለው የጣሊያኖች ትምሕርት ቤት ገብተው ጣልያንኛ ቋንቋ አጥንዋል፡፡
በ1942 እና 1944 ዓ.ም. መካከለል ባሉት ጊዜያት ደግሞ በዓለም ዓቀፍ የሲቪል ማኅበር ድጋፍ በሚሰው የማሠልጠኛ መርኃግብር ፣ ከሆላንድ አገር በአስተዳደር ሙያ፣ ከስውዲን አገር በአየር ትራፊክ አስተዳደር፣ እንዲሁም ከካናዳ አገር በአየር ትራፊክ መቆጣጠር የተለያዩ የምሥክር ወረቀቶችን አግኝተዋል፡፡
መንግሥታዊ፣ አስተዳደር ተሞክሮዎቻቸው
– በ1933 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች የሬዲዮ መገናኛ ክፍል ባልደረባ፣
– በ1936 ዓ.ም. ከገነት ውትድርና ማሠልጠኛ ት/ቤት የምክትል ሌፍተናንት ምሩቅ፣
– በ1938 ዓ.ም. የኢትዮጵያን አየር ኃይል በመቀላቀል ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ ኮርሶችን ተከታትለዋል፤
– በ1940 ዓ.ም. በ አየር መቃወሚያና በረራ መቆጣጠሪያ ማዕከል ረዳት መምህር፣
– በ1947 የኤርትራ ፌዴራላዊ መንግስት የሲቪል አቪዬሽን የበላይ አዛዥ፣
– በ1951 ዓ.ም. የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዳይሬክተር፣
– በ1953 ዓ.ም. የፓርላማ አባል፣
– ለሦስት ተከታታይ አመታት የፓርላማ ፕሬዝደንት፣
– በዓለም አቀፍ የፓርላማ ማኅበርም አገራቸው ኢትዮጵያ የፓርላማ መቀመጫ ታገኝ ዘንድ ከመስራታቸውም በላይ በስዊዘርላንድ፣ ዴንማርክና የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ኮንፈረንስ ተካፋይ ትሆን ዘንድ ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ፣ በ52ኛው ዓለማአቀፍ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ተቀዳሚ ፕሬዝደንት፣
– በ1967 ዓ.ም. የንግዱን ማኅበረሰብ በሲቪል ኮንሰልቲቭ ኮሚሽን እስከፈረሰበት ድረስ የውክልና አገልግሎት፣
– በ አይ ኤም ፒ ኢ ኤክስ አስመጪና ላኪ፣
– በ1969 ዓ.ም. በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የኤርትራን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በተቋቋመው የሰላም ኮሚሽነር ፕሮግራም ተቀዳሚ ኮሚሽነር፣
– በ1992 ዓ.ም. በተደረገው 2ኛ ዙር ምርጫ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ በቾ ወረዳ፣ በግል በመወዳደር የኢ. ፌ. ዲ. ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል፣
ከመንግሥት አስተዳደር ውጪ የሆኑ ተሞክሮዎቻቸው
– የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የቦርድ አባል፣
– በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ ንግድ ልዑክ ወኪል፣
– የጊቤ እርሻ ልማት ማኅበር መስራችና ዳይሬክተር፣
– የከፋ ቲምበር ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ መስራችና ዳይሬክተር፣
– ከ1982 ዓ.ም. በፊት ደግሞ በኤርትራ አገር የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ኤርትራ ቅርንጫፍ ፕሬዝዳንት፣
– የቼሻየር ሆም የቦርድ ፕሬዝዳንት፣
– የሊፕረዚ መቆጣጠሪያ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣
– በ1982 ዓ.ም. ከኤርትራ ሲመለሱም በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የቦርድ ዳይሬክተርና በዚሁ መስሪያ ቤት በዓለምአቀፍ ሎጅስቲክስ ዲፓርትመንት የበላይ ጠባቂ፣
– በ1983 ዓ.ም. ለም ኢትዮጵያ በተሰኘውና በአካባቢ ጥበቃ ላይ በሚሰራው ማኅበር የቦርድ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ፣
– ፕሬዝዳንቱ የኦሮሚኛ፣ አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ ጣልያንኛ፣ እንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ፣ በድምሩ የስድስት ቋንቋ ባለቤት ናቸው፡፡
– ፕሬዝዳንት ግርማ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ናቸው፡፡
Filed in: Amharic