>

ኮማንዶዎች ከ5 እስከ 15 ዓመት በሚፈጅ ጽኑ እስራት ተቀጡ!!!

ኮማንዶዎች ከ5 እስከ 15 ዓመት በሚፈጅ ጽኑ እስራት ተቀጡ!!!
ሪፖርተር
መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ግዳጃቸውን አጠናቅቀው በመመለስ ላይ የነበሩና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ  (ዶ/ር) ጥያቄ እናቅርብ በማለት ቤተ መንግሥት ከገቡ የመከላከያ ኮማንዶ አባላት #በ66ቱ ላይ ከአምስት ዓመት እስከ 14 ዓመት የሚደርስ ቅጣት ተላለፈ፡፡ በቀሪዎቹ ላይ አስተዳደራዊ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡
ኮማንዶዎቹ የተከሰሱት በቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ሲሆን፣ ከ500 መቶ በላይ ታዳሚዎችና የመከላከያ ሚዲያ ባለበት በግልጽ መካሄዱልንና የመከላከያ ወታደራዊ ጠበቃ ቆሞላቸው ክሳቸውን መከታተላቸው ተገልጿል፡፡
ይህ የተገለጸው ዛሬ ቅዳሜ ታኅሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በመከላከያ ሚኒስቴር ቤላ ክላስተር የመከላከያ ወታደራዊ ፍትሕ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል መሸሻ አረዳ፣ የመከላከያ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ተከላካይ ጠበቃ ሻለቃ ደሳለኝ ዳካና የመከላከያ ወታደራዊ ዓቃቤ ሕግ ሻምበል ኃይለ ማርያም ማሞ በሰጡት መግለጫ ላይ ነው፡፡
የኮማዶዎቹ ድርጊት በሁሉም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ውስጥ ምሬትን እንደፈጠረ የገለጹት ኮሎኔል መሸሻ፣ በወታደራዊ ፖሊስ ምርመራ ተካሂዶ፣ በወታደራዊ ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶ፣ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ክሱ ታይቶና የወታደራዊ ጠበቃ ቆሞላቸው የተካሄደ የክስ ሒደት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የፍርድ ሒደቱ የተከናወነው በብላቴ ማሠልጠኛ ውስጥ ሲሆን፣ ተከሳሾቹም በታጠቅ ማረሚያ ቤት መታሰራቸውም ተገልጿል፡፡
በተከሳሾቹ ላይ የተመሠረተው ክስ እንደደረሳቸው ከተከሳሾቹ ጋር ተገናኝተው ክሱ እንዲደርሳቸውና እንዲረዱት መደረጉን የተናገሩት የመከላከያ ወታደራዊ ተከላካይ ጠበቃ ሻለቃ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ በተከሳሾቹ ጥፋተኝነትና በቅጣቱ ላይ ይግባኝ በማለት ወደ ወታደራዊ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ለመሄድ ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡
ወታደሮቹ የተመሠረተባቸው ክስ ወታደራዊ አመጽ በማነሳሳትና ትዕዛዝ ባለመቀበል መሆኑም ተነግሯል፡፡
ከነትጥቃቸው ቤተ መንግሥት በገቡ የመከላከያ ሠራዊት ኮማዶዎች ላይ የተላለፉ ቅጣቶች ዝርዝር፡ –
1ተከሳሽ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት
3 ተከሳሾች በ13 ዓመት ጽኑ እስራት
11 ተከሳሾች በ12 ዓመት ጽኑ እስራት
12 ተከሳሾች በ11 ዓመት ጽኑ እስራት
4 ተከሳሾች በ10 ዓመት ጽኑ እስራት
16 ተከሳሾች ከ9 ዓመት እስከ 9 ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት
2 ተከሳሾች በስምንት ዓመት ጽኑ እስራት
10 ተከሳሾች ከ7 ዓመት እስከ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት
ተከሳሾች ከስድስት ዓመት እስከ ስድስት ዓመት ከስምንት ወር
1 ተከሳሽ በአምስት ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጥተዋል፡፡
Filed in: Amharic