>
5:26 pm - Wednesday September 17, 3817

F-5E   ኤርክራፍት ለታማኝ በየነ!!! (ሀብታሙ አያሌው)

F-5E   ኤርክራፍት ለታማኝ በየነ!!!
ሀብታሙ አያሌው
ቅዳሜ ግሩም ምሽት ነበር፤ የሰው ልጅ መልካም ስራ ወደየትኛው የክብር ማማ እንደሚያደርስ ለማስተዋል እድል አግኝተንበታል። የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት ማህበር ለአርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ያላቸውን የክብር ከፍታ ለማሳየት F-5E  የተሰኘውን የጠላትን ሰፈር ያራደ  ኤር ክራፍት  (ታማኝ አንድ) በሚል መለያ ቁጥር አጅበው አበርክተውለታል።
ወራሪውን የሶማሌ ጦር ጭዳ ለማድረግ የጅጅጋን ሰማይ የሽርሽር መንገድ በማድረግ የሚታወቁት ኮለኔል ብርሃኑ ውቤነህ የዕለቱን የክብር ተሸላሚ ታማኝ በየነን እንደ አለቃ ወደላይ እያዩ በክብር ሲጨብጡት ትህትናቸው አግራሞት ቢፈጥርብኝ ጠጋ ብዬ  ስላለፈ ገድላቸው ጠየኩ።
ስለ ኮለኔል ብርሃኑ ውቤነህ ስሰማ የኮለኔል መንግስቱ ኋይለማርያም አንድ ንግግር ትዝ አለኝ። “በውኑ ይህ ህዝብ ያውቀናል ?  እኛስ እናውቀዋለን… ? ” ያሉበት የቁጭት ንግግር።
ኮለኔል ብርሃኑ ውቤነህ በሶማሊያ ወረራ ጊዜ የሐርጌሳን ራዳር በማቃጠል ጠላትን ሱሪ ካስወለቁ ጀግኖች አንዱ ናቸው። ኮለኔሉ  የኛዋ ተወዳጇ ድሬ የጠላት ታንክ በመሐል ከተማዋ እየተርመሰመሰ እንደ አቧራ ሊያጨሳት ከአፋፍ ሲደርስ  ድንገት በሰማዩ መንገድ በF5A ኤርክራፍት ደመናውን ቀዝፈው ጠላት ውሃ ውሃ እያለ እንዲያፈገፍግ ያደረጉ የጀግና ልክ መሆናቸውን ሰማሁ።
ወሬ ነጋሪዬ አንድ ጊዜ ወደ ታማኝ በየነ ሌላ ጊዜ ወደ ኮለኔል ብርሃኑ የሚንከባለለው የአይኔ ብሌን እንጂ ልቤ ከጀግንነት ተረኩ ጋር እንደነጎደ ሲረዳ ከኮለኔሉ ገድል ጥቂት ጨመረልኝ።  ኮለኔሉ ጠላትን ከጅጅጋ እያራወጡ ወደ መቋዲሾ ነፍሴ አውጪኝ ካሰኙ ጀግኖች አንዱ ነበሩ። ፈርቶ የሚሸሸው ኃይል እንዳያገግም ከሰማይ እሳት እያዘነቡ ታንክና ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ዶግ አመድ አድርገዋል። እልፍ አብራሪዎችን አሰልጥነው በብቃት አስመርቀዋል።
እኚህ ኮለኔል በሰሜን ውጊያ ሚግ 23 በማብረር የጠላትን ሰፈር በማራድ በርካታ ገድል አላቸው። ቅዳሜ ምሽት ቀይ ዳማ መልካቸው በፍፁማዊ ፈገግታ እንደታጀበ የዚህ ጀግና አየር ኋይል ገድል ፈፃሚዎች ማህበር አባላት ለአርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ክብር ከመቀመጫቸው ብድግ ሲሉ ኮለኔሉ ቀዳሚ ነበሩ። ጀግንነትም ማክበርም የሚያውቁ ደርባባ ሰው ናቸው።
አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ባደረገበት ወቅት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአየር ኃይል ማህበሩን ደብዳቤ በማቅረብ እነዚህ ስለ አገር ዋጋ የከፈሉ ጀግኖች በህወሓት ሰይጣናዊ ስሌት የደረሰባቸውን በደል ጠቅሶ አገራቸው እንድታከብራቸው እንደጠየቀ እና በአደባባይ ህዝብን ወክሎ ለደረሰው በደል ይቅርታ እንደጠየቃቸው እናስታውሳለን።
ታማኝ እንኳን ለዚህ አበቃህ !!
Filed in: Amharic