>

ደግሞ ስለአየለ ጫሚሶም እናውራ እንዴ? (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

ደግሞ ስለአየለ ጫሚሶም እናውራ እንዴ?
ሞሀመድ አሊ መሀመድ
*:የዶ/ር አብይ መንግሥት አንገቴን የሚያስደፋኝ እነአየለ ጫሚሶን ከነፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር  እኩል ጠርቶ/ጋብዞ በሀገር ጉዳይ ላይ ሲያወያይ ነው። “ዕቃ ጠፋና አብረን በላን” የሚባለውኮ እንዲህ ያለው ነገር ሲያጋጥም ነው!!!
ለመሆኑ መቀሌ የተገኘው የህወሓትን ትንሳኤ ለማብሰር ነው? ወይስ ተዝካር ለማውጣት? ወይስ የበረከትን ድግስ ለማድመቅ? ወይስ ከቀድሞ አለቃው ጌታቸው አሰፋ ትዕዛዝ ለመቀበልና የሚሰጠውን ተልዕኮ በታማኝነትና በቁርጠኝነት ለማስፈፀም? አልቀረበትም!
“ሰው መሳይ በሸንጎ” ይላል አማራ ሲተርት። የዶ/ር አብይ መንግሥት አንገቴን የሚያስደፋኝ እነአየለ ጫሚሶን ከነፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር  እኩል ጠርቶ/ጋብዞ በሀገር ጉዳይ ላይ ሲያወያይ ነው። “ዕቃ ጠፋና አብረን በላን” የሚባለውኮ እንዲህ ያለው ነገር ሲያጋጥም ነው። እኔ መቼም አየለ ጫሚሶና መሰሎቹ ጋር ቁጭ ብዬ በሀገር ጉዳይ ላይ መወያዬት አልፈልግም; አልችልምም።
በዚሁ አጋጣሚ አንድ ነገር ላንሳ። ከዚህ ቀደም ከገዥው ፓርቲ ጋር በተጠራ ድርድር ላይ አየለ ጫሚሶ በመጠራቱ መድረኩን ረግጩ ወጥቼ ነበር። በወቅቱ የኢህአዴግ ዋነኛ ተደራዳሪ የነበረው በረከት ስምኦን “ከዚህ በኋላ ካንተ ጋር በዚህ ዓይነት መድረክ ሳይሆን የምንገናኘው በሌላ መንገድ ነው” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ሰንዝሮብኝ ነበር። እኔም አልተመለስኩለት; “እስከ አፍንጫው የታጠቀ ኃይል የያዘ መንግሥትን የሚመራ ከፍተኛ ባለሥልጣን በአንድ ሲቪል ዜጋ ላይ እንዲህ ዓይነት ዛቻና ማስፈራሪያ መሰንዘር ወንጀል ነው” በማለቴ በረከት በንዴት ቱግ ብሎ “ለመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን ድፍረት ከየት አመጣኸው?” ብሎ አፈጠጠብኝ። እንግዲህ የመጣው ይምጣ በሚል; “አንተ ነህ እንጅ ያሰለፍከውን ጦር ተማምነህ ለድርድር የመጣን ሰው የምታስፈራራው!” ብዬው ተነስቼ ወጣሁ። በመድረኩ እነፕ/ር በየነና መረራ ጉዲናም ታድመው ነበር።
በሚቀጥለው ቀን ጧት ፓርላማ ለስብሰባ ስሄድ በወቅቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የነበረው አቶ ሽፈራው ጃርሶ ቢሮ ትፈለጋለህ ተባልኩና ስሄድ የቅንጅት አባላት ዋና አስተባባሪ የነበሩት እቶ ተመስገን ዘውዴና ወዳጄ እንዳልካቸው ሞላ ቀድመው ተገኝተው ነበር። በዋናነት ግን በፓርላማው ውስጥ እንደንጉስ የሚታየው/የሚፈራው የህወሓቱ አስመላሽ ወ/ስላሴና ሌሎች የኢህአዴግ አመራሮች ነበሩ።
አቶ አስመላሽ ዙሪያ ጥምጥም መሄድ ሳያስፈልገው “አቶ መሐመድ ትናንት የነበረውን የድርድር መድረክ ረግጠህ መውጣትህ አልበቃ ብሎ በመንግሥት ላይ ተገቢ ያልሆነ ዛቻና ማስፈራሪያ ሰንዝረሃል። ስለሆነም መንግሥት በአንተ ላይ ተገቢውን እርምጃ ከመውሰዱ በፊት በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቅ ዕድሉን እንሰጥሃለን” አለኝ በቀጥታ። በወቅቱ ይህን ለመናገር እነ አቶ ተመስገንን ጨምሮ ሌሎች የኢህአዴግ አመራሮችን መሰብሰብ ለምን እንዳስፈለገ አልገባኝም። እኔ ግን በአቋሜ በመፅናት “የተናገርኩት ነገር ስህተት/ጥፋት ስላልሆነ ይቅርታ አልጠይቅም” ብዬ አሻፈረኝ አልኩ።
ምን ዓይነት እርምጃ ይወስዱ ይሆን እያልኩ ስጠብቅ አየለ ጫሚሶና ተከታዮቹ ተሰባስበው በETV መስኮት ብቅ አሉና “መሐመድ አሊ ከሶማሊያ አማፂያን/ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት እንዳለው እናውቃለን; በኤርትራ መንግሥት በኩል በየወሩ አሥር ሺህ ዶላር እየተላከለት የጥፋት ተልዕኮ ያስፈፅማል” ሲሉ በአደባባይ ወነጀሉኝ። አቶ ተመስገንም ሥማቸው ተጠቅሶ ስለነበር “በሀሰት ተወነጀልን” የሚል ክስ ይዘን አራዳ ፖሊስ መምሪያ ሄድን። የመምሪያው ኃላፊዎች (አዛዡን ጨምሮ) ሲነጋገሩ ቆዩና “ይኸ ጉዳይ ከእኛ አቅም በላይ ነው” ብለው አሰናበቱን።
ከዚያ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራን። በወቅቱ ም/ኮሚሽነር የነበረው አቶ ተስፋዬ መረሳ; “ይኸ ጉዳይ የናንተ (የቅንጅት) የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ እኛ ጣልቃ ገብተን ማጣራት አንችልም” የሚል ምላሽ ሰጠን። ከዚያ ወጣንና በፍትህ ሚኒስቴር የአዲስ አበባ ተጠሪ ጽ/ቤት በመሄድ “ፖሊስ ወንጀሉን እንዲያጣራ ይታዘዝልን” ብለን አመለከትን። እነሱም ዛሬ ነገ እያሉ ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ ሊሰጡን አልቻሉም።
በመሆኑም ቅሬታችንን ለፍትህ ሚኒስቴር አቀረብንና ም/ሚኒስትሩ ጋር ደረሰ። በወቅቱ ም/ምኒስትር ለነበሩት ዶ/ር ሀሽም ጉዳዩን ካስረዳናቸው በኋላ “ግድየለም; እኔ ራሴ በቀጥታ ጉዳዩ እንዲጣራ በየደረጃው ትዕዛዝ እሰጣለሁ” ብለው ቢሸኙንም ጉዳዩ አረም ተጭኖበት ቀረ። ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ብንመላለስም ወደ ዶ/ር ሀሽም ቢሮ የሚያስገባን ሰው አልተገኘም።እኛም ከዚህ በላይ ወዴት መሄድ ይቻላል? በሚል ተስፋ ቆርጠን ተውነው።
አየለ ጫሚሶ በተለይ እኔን የወነጀለኝ በጠቅላይ ሚ/ር ቢሮ በነመለስ ዜናዊ ፊት ጭምር ነበር። በወቅቱ ስለታሰሩት የቅንጅት መሪዎች ለመነጋገር ፍላጎት እንዳለን በአምባሳደሮች በኩል ገልፀን ነበር። በዚህም መሠረት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጠሩንና በጽ/ቤታቸው ተገኘን። ከእሳቸው ሌላ ሽፈራው ጃርሶና ብርሃኑ አደሎ ነበሩ። በኛ በኩል; ከአቶ ተመስገንና ከእኔ በተጨማሪ አየለ ጫሚሶና ሳሳሁልህ ከበደ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች በወቅቱ ከደህንነት ጋር እንደሚሠሩ ተባራሪ መረጃ ስለነበረን አብረውን እንዳይሄዱ በድምፅ ብልጫ ብናስወስንም አቶ አየለ “ከጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት በቀጥታ ስለተደወለልን አንቀርም” ብሎ ሳሳሁልህን አስከትሎ ሲሄድ በር ላይ ማንም ሳይከለክለው መግባት ችሎ ነበር።
ወደ ጠቅላይ ሚ/ር ቢሮ እንደገባን አቶ መለስ “እስቲ የመጣችሁበትን ጉዳይ አጠር አጠር እያደረጋችሁ አስረዱኝ”አሉ። በመጀመሪያ ዕድል የተሰጣቸው አቶ ተመስገን “በሀገራችን የተፈጠረውን ፖለቲካዊ አለመግባባትና አጠቃላይ ውጥረት ተቀራርቦ በመነጋገር መፍታት እንደሚያስፈልግ” አስረዱ። ቀጥሎ የመናገር ዕድል የተሰጠው አቶ አየለ ጫሚሶ የተናገረው ነገር ጨርሶ ያልጠበቅነውና አስደንጋጭ ነበር።
አየለ የተናገረውን በወቅቱ ከያዝኩት ማስታወሻ እንደወረደ ባቀርበው ይሻላል።
“ክቡር ጠ/ሚ/ር እኔ በኃ/ስላሴ ዘመን ተማሪ ነበርኩ። በደርግ ጊዜም የመንግሥት ሠራተኛ ነበርኩ። አሁንም ዕድሜ ሰጥቶኝ በኢህአዴግ ዘመን ከተቃዋሚዎች ጋር ተሰልፌያለሁ። እኔ በሦስት ሥርዓት የኖርኩ ሰው ነኝ። እንደ ኢህአዴግ ግን ለልማትና ለዴሞክራሲ የቆመ መንግሥት የለም። ተቃዋሚዎች ይኸን እውነት ሸምጥጠው ይክዳሉ። እናም በአመፅና በግርግር ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን መናድ ይፈልጋሉ። እኛም በውስጥ እየታገልናቸው ነው።
“ክቡር ጠ/ሚ/ር ከዋናዎቹ የቅንጅት መሪዎች መካከል ያልታሰሩት ዛሬም በመሐላችን ይገኛሉ። መንግሥት እነዚህን ለምን እንዳላሠራቸው አናውቅም። እነዚህ ሰዎች በኛም ላይ ሥጋት የሚፈጥሩ በመሆናቸው የናንተን ድጋፍ እንፈልጋለን። በእኛ በኩል ግን በቅርቡ ጉባኤ ጠርተን መንጥረን በማውጣት እናሳውቃችኋለን። ከዚያ መንግሥት የራሱን እርምጃ ይወስዳል ብለን እንጠብቃለን። አለበለዚያ ግን ውጥረቱ ሊረግብ አይችልም። እነዚህ ሰዎች ሀገሪቷን ለማተራመስ በሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ጭምር የሚረዱ ናቸው” ብሎ ጨረሰ።
ቀጥሎ የመናገር ዕድል የተሰጠኝ ለኔ ነበር። ቢሆንም ግን የአየለ ጫሚሶን ውንጀላ ማስተባበልና በመለስ ፊት መጨቃጨቅ አልፈለኩም። ከዚያ ይልቅ የሀገራችን ጉዳይ ሁላችንም የሚያሳስበንና የሚያገባን መሆኑን በማስረገጥ “እናንተ በሥልጣን ላይ ስለሆናችሁ ብቻ ሌላውን ወገን የሀገር ሥጋት አድርጎ መሳል ውጥረቱን ይበልጥ ሊያባብሰው ይችላል” እያልኩ ስናገር አቶ መለስ አቋረጡኝና
“አንተ ግን ራስህን increment እያደረገክ እንደሆነ ይገባሃል? በንግግርህ መሐል ደጋግመህ “የታሠሩት መሪዎቻችን” ትላለህ። የቅንጅት መሪዎችን ሰብስበን ያሠርናቸው በአመፅና በግርግር ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ስለያዝናቸው ነው። አንተም “መሪዎቼ ናቸው” ካልክ በነሱ ሀሳብ ትመራለህ; ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ተስማምተሃል ማለት ነው?” ሲሉ በአንክሮ ጠየቁኝ።
እኔም አልኩኝ; “ክቡር ጠ/ሚ/ር ‘የታሠሩት ሰዎች መሪዎቼ አይደሉም’ ብል እርስዎስ አይታዘቡኝም? ደግሞም ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ስለማሴራቸው በበኩሌ የማውቀው ነገር የለም። እኔ የማውቀው በተፈጠረው የፖለቲካ አለመግባባት መታሠራቸውን ነው። ዛሬም እዚህ የተገኘነው አለመግባባቱ በንግግር እንዲፈታና ውጥረቱ እንዲረግብ ነው” አልኩኝ።
በመጨረሻም ሳሁልህ ተናገረና ጠቅላይ ሚ/ሩ “ደግሞ ሌላ ጊዜ እንነጋገራለን” በሚል የማጠቃለያ ቃል አሰናበቱን። ስንወጣ እነአየለ ተነጥለው ከነብርሃኑ አደሎ ጋር ይነጋገሩ ነበር። ከዚያ በኋላ አየለ ጫሚሶ የፈጠረብኝ ራስ ምታትና ፈተና በፌስቡክ ገፅ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። አሜሪካ ኤምባሲ ድረስ ተጠርቼ በነቪኪ ሀልድስተን ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠኝ አስደርጓል። እኔም አየለ ጫሚሶ በሚታደምበት መድረክ ለመገኘት አሻፈረኝ ብዬ ቆይቻለሁ።
“ይኸ ሽንፊላ. ..” ይሉ ነበር አቶ ተመስገን።
Filed in: Amharic