>

የሠራዊት ፍቅሬና የሶምሶን ማሞ አስገራሚ ክህደትና ድርቅና!!! (አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

የሠራዊት ፍቅሬና የሶምሶን ማሞ አስገራሚ ክህደትና ድርቅና!!!
አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
በዚህ ሳምንት ከወያኔ አጋፋሪዎች ሁለቱ ማለትም ሠራዊት ፍቅሬና ሶምሶን ማሞ በሁለት የተለያዩ የቴሌቪዥን (የምርዓየ ሁነት) ጣቢያዎች ቃለመጠይቅ ተደርጎላቸው ነበር፡፡ ሠራዊት በኤል ቲቪ ቤቲ ሾው ሳምሶን ደግሞ በፋና ጉባኤ ኪን ዝግጅት ላይ፡፡ እነኝህ ግለሰቦች ለተጠየቁት ጥያቄዎች የሚያቀርቧቸው መልሶች ድንቁርና የተሞላና የሚሠሩትን የማያውቁ ሆነው በማግኘቴ አንዳንድ ነገር ማለት ፈለኩ፡፡
ብዙ ነገሮች ነበሩ ለጊዜው በሁለት ነጥቦች ላይ እናተኩራለን፡፡ በሥርዓቱ ደጋፊነታቸውና በልዩ ተጠቃሚነታቸው፡፡
ሁለቱም አለፈ ወይም ተሸኘ በሚባለው የወያኔ አገዛዝ በሞያቸው የጥቅም ትስስር እንደነበራቸው ሲጠየቁ ሸምጥጠው በመካድ “አዎ ለማንኛውም ደንበኛ እንደምንሠራው ሥራዎችን እንሠራ ነበር ነገር ግን ልዩ የጥቅም ትስስር አልነበረንም፡፡ እንዲያውም ሥርዓቱ ያዘጋጃቸው የነበሩ ዝግጅቶችን ስንመራና ስናስተዋውቅ አብዛኛውን ያለ ክፍያ ነው፡፡ ከተከፈለንም በጣም አነስተኛ ከአበል ክፍያ ባልበለጠ ክፍያ ነበር እንሠራ የነበረው!” ብለው መልስ ሰጥተዋል፡፡
ይታያቹህ! እንደዛሬው የተለያዩ የግል የቴሌቪዥን (የምርዓየ ሁነት) ጣቢያዎች ባልነበሩበትና የሀገራችን ብቸኛው የኢትዮጵያ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያ በነበረበት ሰዓት ከአገዛዙ በተላለፈ ትዕዛዝ ኢፍትሐዊና ሕገወጥ በሆነ አሠራር የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራዲዮ (ምርዓየሁነትና ነጋሪተወግ) ጣቢያ የእነኝህን አራት አምስት ጥቅመኛ ግለሰቦችን ስም ብቻ እየጠቀሰ “ከነሱ ውጭ የሚመጣ ማንኛውም ማስታወቂያን አናስተናግድም!” እያለ በነጻ ውድድር ሊመራ የሚገባውን የገበያ ሥርዓት በመተላለፍ ብቸኛ ተጠቃሚዎች ተደርገው በማስታወቂያ ሥራ የናጠጡ ሀብታሞች እንዲሆኑ በተደረገበት ሁኔታ ያለ አንዳች እፍረት “ልዩ ተጠቃሚ አልነበርንም እንዲያውም በነጻ ነበር እንሠራ የነበረው!” ማለታቸው አይገርምም???
ሳያፍሩና ሳይፈሩ እንዲህ ማለታቸው አንደኛ እነኝህ ግለሰቦች የለየላቸው ሕሊናቢስ መሆናቸውንና ለሕዝብ ያላቸውን ከፍተኛ ንቀት ነው ያሳየኝ፡፡
ሌላው የቀረበላቸው ጥያቄ የአገዛዙ ደጋፊ እንደሆኑና በዚህ ይጸጸቱ እንደሆን ተጠይቀው የመለሱት መልስ ነው፡፡ በቅድሚያ የሠራዊትን መልስ እንመልከት፡፡ ሠራዊት በሞያው ሥራውን ይሠራ እንደነበረ እንጅ ደጋፊም አባልም እንዳልነበረ መልሷል፡፡
ይታያቹህ! ይሄ ሰው የኪነት ባለሞያዎችን አስተባብሮ አንባገነኑን ጭራቅ የወያኔን መሪ መለስ ዜናዊን “የምትሠራው ሥራ ግሩም ነው! በርታ! ግፋበት!!!” ብሎ የወርቅ ብዕር ሽልማት እየሸለመ ሲያበረታታና ሲያጀግን ከርሞ “ደጋፊ አይደለሁም!” ብሎ እርፍ፡፡
ቆይ ደንቆሮው ሠራዊት ፍቅሬ ሆይ! ጓዶችህን አስተባብረህ ጨፍጫፊውን፣ ወንበዴውን፣ ጠባቡን፣ አንባገነኑን የወያኔ መሪ የወርቅ ብዕር ስትሸልም መደገፍህ፣ ማጀገንህ፣ ማበረታታትህ ካልሆነ ምን ማለትህ ነበረ ታዲያ ባክህ??? የሽልማት ትርጉሙ ምንድን ነው ደንቆሮው??? በግል የሥራ ቦታህ የመለስን ፎቶ (ምሥለ አካል) በትልቁ በመስታይት አስገብተህ ግድግዳህን ስታለብሰው ምን ማድረግህ ነበረ የኛ ብልጣብልጥ???
ይገርማቹሃል ይሄ ሰው ከዚህም በላይ ከሌሎች ሆድ አደር ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ከያኔ ተብየዎች ጋራ ለሕወሓት 40ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ደደቢት በረሃ ድረስ ወርዶ ከወያኔ ጋር ሲቀማጠል ከሰነበተ በኋላ በጉብኝታቸው መጨረሻ ላይ “ከአሁን በኋላ በሚፈለግብን ጉዳይ ሁሉ ከሕወሓት ጎን እንደምንቆም እናረጋግጣለን!” የሚል ገዥ ነጥብ ያለበት ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ ተፈራርመው በማውጣት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዜና ዘገባ አስታውቀው ወያኔም ይሄንን ነውረኛ ድርጊታቸውን ለሕዝብ ግንኙነት ፍጆታው ከተጠቀመበት በኋላና እነሱም ለሕወሓት ህልውናና ደኅንነት በርትተው ሲሠሩ ከከረሙ በኋላ አሁን “ደጋፊም ምንም አይደለሁም!” ማለትን ምን ይሉታል???
ነው ወይስ ሕዝቡን ምንም ነገር ማስታወስ የማይችል አድርጎ ከመቁጠር “እንደፈለኩ ብናገር ማን ምን ያመጣል!” ከሚል የመጣ የንቀት አመለካከት ነው??? እዚያ ደደቢት በረሃ ከሔዱትና ያንን የጋራ የአቋም መግለጫ ካወጡት ውስጥ በመግለጫቸው ላይ ፊርማውን ያላሠፈረና ከተመለሱም በኋላ “መግለጫው እኔን አይመለከተኝም አልፈረምኩም!” ሲል የተሰማ አንድም ሰው አልነበረም፡፡
እንደምታውቁት እነኝህን ኅሊና ቢስ ሆድ አደር ግለሰቦችን አገዛዙ የተበላሸበትን የሕዝብ ግንኙነት ለማቅናት ለማስተካከል ፍጆታ መጠቀሚያ ሲያደርጋቸው እንደኖረና እነሱም ወደውና ፈቅደው መጠቀሚያ ሆነው ሲያገለግሉት፣ ለዚህም እንደሚጠቀምባቸው እያወቁ መጠቀሚያ ሲሆኑ ከከረሙ፣ በዚህ ወራዳና ነውረኛ ተግባራቸውም ሕዝብን ሲያበግኑ፣ ሲያበሽቁ፣ ሲያሳርሩ፣ ሲያቃጥሉ፣ ሲያደብኑ ከከረሙ በኋላ አሁን “ደጋፊም አባልም አልነበርኩም!” ብሎ ማለት ሕዝብን ማሰብ እንደማይችል አድርጎ መናቅ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ይባላል??? አሁን እነዚህ ይቅርታ ይገባቸዋል???
ሳምሶን ማሞ ደሞ “የነበረው ሥርዓት ደጋፊ ነህ ተብለህ ትታማለህ!” ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ ጭራሽ ምን አለ መሰላቹህ “መብቴ ነው! እኔ እንደሌሎቹ ዛሬ ሕወሓት ሔዷል ብየ 360 ዲግሪ ተገልብጨ ሕወሓት እንዲህ ነው ተደምሬያለሁ ምናምን አልልም….!” ብሎ እርፍ!!! ለነገሩ ከሠራዊት ፍቅሬ እፍረተቢስ ክህደትና ድርቅና ይሄኛው የሚሻል ይመስለኛል፡፡
ነገር ግን ይሄ የሶምሶን ምላሽ ሲበዛ ድንቁርና የተሞላና የሚያስከፍለውን ዋጋ ያልተረዳ እብሪት የተሞላበት መልስ ነው፡፡ ሲጀመር ወያኔን መደገፍ ወንጀል እንጅ መብት አይደለም!!!
እርግጥ ነው ማንም ሰው በነጻ የማሰብ ነጻነትንና የመሰለውን የመደገፍ ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) እና ሰብአዊ መብት አለው፡፡ ይሄ ማለት ግን ማንም ሰው የወንጀል ተግባርን የማሰብና የመፈጸም፣ ወንጀለኛን መደገፍ ማገዝና መተባበር መብት አለው ማለት አይደለም፡፡ ደንቆሮው ሳምሶንና ቢጤዎቹ ሊረዱት ያልቻሉት ይሄንን ነው፡፡
ወያኔ ወንጀለኛ፣ ግፈኛ፣ ሰው በላ፣ ወንበዴ፣ አረመኔ የጥፋት ኃይል ነው፡፡ እንደ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ጽ/ቤት የመሳሰሉት አንጋፋ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የወያኔን አንባገነን አገዛዝ በሰው ልጅ ላይ ከሚፈጸሙ የወንጀል ዓይነቶች በመጨረሻው የወንጀል ዓይነት ማለትም በዘር ማጥፋት ጥቃት ሲከሱት፣ ሲያወግዙት፣ ሲኮንኑት፣ ሲቃወሙት መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
በመሆኑም ይሄንን በረሃ እያለ ጀምሮ የዘር ማጥፋትን በአማራ ላይ ለመፈጸም በማኒፌስቶው (በአቅደ ዓላማው) ቀርጾ የአማራን ዘር እንደሚያጠፋ በይፋ ተናግሮ በመምጣት በግልጽና በስውር በሚፈጽመው አረመኔያዊ ጥቃት ሕዝብን ሲፈጅ ዘር ሲያጠፋ የቆየንና አሁንም ያለን አረመኔ የጥፋት ኃይል፣ በሶማሌና በአኙዋክ ከፍተኛ የጦር ወንጀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸመን አረመኔ የጥፋት ኃይል፣ ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ አሳር ሲያበላ የኖረን የወንበዴ ቡድን መደገፍ የትኛውም ዓለም አቀፍ ሕግ ቢሆን “የሚያስጠይቅ የሚያስቀጣ አደገኛ ወንጀል ነው!” ይላል እንጅ “ለዜጎች የተፈቀደ መብት ነው!” የሚል አንድም ሕግ በዓለማችን የለም፡፡ እነ ሳምሶን እንዴት ቢያስቡ ይሄንን ሰውበላ፣ አረመኔ፣ ግፈኛና ዘራፊ የወንበዴን ቡድን መደገፍ “መብቴ ነው!” ሊል እንደቻለ ሊገባኝ አልቻለም፡፡
በሌላም በኩል ወያኔ ማለት፦
* የሀገርንና የሕዝቧን አንድነት አጥፍቶ ሀገርን ለመበታተን ሌት ተቀን የሚያሴር፣
* ከዚህም አልፎ ለርካሽ ቡድናዊ ጥቅሙ ሲል ሕዝብን ከሕዝብ ጋራ በማጋጨት እስከወዲያኛው እንዳይስማሙ አድርጎ በሚፈጥረው ሐሰተኛ ታሪክ ተቂያቂመው እየተባሉ እንዲኖሩ ለማድረግ የሚጥር የሚሠራና ወደፊትም እሱ የማይገዛበት ሁኔታ ቢፈጠር ሀገሪቱን ልትፈራርስ በምትችልበት ሁኔታ ላይ ያስቀመጠ በሽተኛ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” ባይ ወንበዴ የጥፋት ኃይል፣
* ቀደም ሲልም ለሕልውናዋ ተነግሮ የማያልቅ መራር መሥዋዕትነት የተከፈለላትን ሀገር ገንጥሎ የሚያስረክብና ለርካሽ ቡድናዊ ጥቅሙ ሀገሪቱን እየቆረሰ ለማንም ባዕዳን የሚሸቃቅጥ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” ባይ የአህዮች የጥፋት ኃይል፣
* ዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) መብታቸውን ስለጠየቁ ብቻ በዜጎች ላይ እጅግ አረመኔያዊ ኢሰብአዊ ሰቆቃ (ቶርቸር) ግፍ የሚፈጽምን አረመኔ የግፍ አገዛዝ፣
* “የአማራንና ኦርቶዶክስን አከርካሪ እንዳያንሰራራ አድርገን ሰብረናል!” በማለት በአማራ ሕዝብ ላይ ከሚፈጽመው የዘርማጥፋት ወንጀል በተጨማሪ ለዚህች ሀገር ሁለንተና የማይተካ አስተዋጽኦ ያበረከችውን የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን መጫወቻ መቀለጃ አድርጎ ያዋረደ፣ የሰበረና እያጠፋት ያለን የአጋንንት ውላጆች የጥፋት ኃይል ነው ወያኔ ማለት፡፡
በመሆኑም ይሄንን የወረደ፣ አረመኔ፣ ግፈኛ፣ ወንበዴ፣ ለሕዝብና ለሀገር ቀንደኛ ጠላት የሆነን የጥፋት ኃይል መደገፍ “የሚያስጠይቅ የሚያስቀጣ አደገኛ ወንጀል እንጅ ለዜጎች የተፈቀደ መብት አይደለም፡፡ በዓለማችን አንድም ሕግ እንዲህ ዓይነት መብት የሚሰጥ ሕግ የለምና፡፡ ከዚህም በላይ ወያኔን መደገፍ ማገዝ መርዳት በነፍስም የሚያስኮንን፣ የገሃነም ፍርድ የሚያሰጥ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ ከፀረ ቤተክርስቲያን የአጋንንት ቡድን ጋር መተባበር ነውና፡፡
በመሆኑም እነኝህ አራት አምስት የወያኔ ቅጥረኛ ግለሰቦች ንብረት ያፈሩትና የናጠጡ ሀብታም ለመሆን የበቁት ይሄንን ግፈኛና አንባገነን ዘራፊ አገዛዝ ከሕዝብና ከሀገር ጥቅም በተጻራሪ በማገልገላቸው ወይም ከአገዛዙ ጋር በመሞዳሞዳቸው (በሙስና) በኢፍትሐዊና ሕገወጥ መንገድ ያፈሩ በመሆናቸው ንብረታቸው በሙሉ መወረስ አለበት!!!
ንብረታቸው ብቻ ሳይሆን እነሱም ራሳቸው ኪነትን ለአረመኔያዊ የወንበዴ ቡድን እጅ መንሻ አድርገው በማቅረብ በዜጎች ላይ ተነግሮ የማያልቅ አረመኔያዊ ግፍ የፈጸመውንና፣ በሕገወጥ የንግድ ድርጅቶቹ ሀገርንና ሕዝብን ሲዘርፍ ሲያራቁት እራሱን ሲያሳድግ፣ ሲገነባና ሲያበለጽግ የኖረውን አረመኔውን፣ ወንበዴውንና ዘራፊውን የጥፋት ቡድን ዲሞክራሲንና ሰብአዊ መብትን ያሰፈነ፣ ሀገርን በልማት ያሳደገ የገነባ አስመስለው የሌለውን ገጽታ እንዳለው እያደረጉ ለሕዝብ በመለፈፍ አገዛዙ በሕይዎት ቆይቶ ይሄንን ሁሉ ግፍ በሕዝብና በሀገር ላይ እንዲፈጽም ያስቻሉ በመሆናቸው ሕግ ፊት ቀርበው መቀጣት አለባቸው!!!
ይህ ሕጋዊ እርምጃ በእነኝህ ቅጥረኛ ግለሰቦች ላይ ዛሬ ባይፈጸም ነገ እንደማይቀርላቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ በመሆኑም በእብሪትና በንቀት እንዳበጣቹህ አትቀሩም በሉልኝ እነኝህን ቅጥረኞች!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
Filed in: Amharic