>
2:56 am - Saturday December 10, 2022

ፖለቲካ ያጋለጠው የሞራል ውድቀት!!! (በፈቃዱ ዘ ኃይሉ)

ፖለቲካ ያጋለጠው የሞራል ውድቀት!!!
በፈቃዱ ዘ ኃይሉ
የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ መሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ  ለሠላማዊ ትግል ወደ ኢትዮጵያ ከመመለሳቸው ጥቂት ቀናት በፊት ‘አዲስ ስታንዳርድ’ ለተባለ መገናኛ ዘዴ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተዋስዖ (‘ዲስኮርስ’) እምብዛም ተነስቶ የማያውቅ ጉዳይ አንስተው ነበር፤«ከሁሉም በላይ የሚያሳስበኝ ማኅበረሰቡ የሞራል ኮምፓሱን ማጣቱ ነው» በማለት። ባለፉት የፖለቲካ ለውጥ ወራት በኢትዮጵያ የታዩት ክስተቶች  ማኅበራዊ የሞራል ውድቀት መኖሩን በአንድም፣ በሌላም መንገድ የሚያረጋግጡ ናቸው ማለት ይቻላል።
የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ከሕግ እና ፖሊስ ይልቅ እርስ በርሱ ባለው አዎንታዊ መስተጋብር ደኅንነቱን አስጠብቆ ይኖር ነበር ማለት ይቻላል። በተለምዶ «እሴቶቻችን ናቸው» የሚባሉት አብሮ መኖር፣ መከባበር እና መቻቻል ተሸርሽረው መጥፋታቸውን ግን አላስተዋልንም ነበር፤ ይህንን መራራ ሐቅ እያጋለጠ ያለው የፖለቲካ ሒደቱ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‘ጨቋኝ ነው፤ ይውረድ’ እየተባለ የነበረው መንግሥት ፀባዩን ከሞላ ጎደል ሲቀይር፥ እዚህም እዚያም የሚፈነዳው ግጭት ወይም ጥቂቶች ሌሎች ላይ የሚሰነዝሩት ጥቃት መላ አገሪቱን ተቆጣጥሯል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው የሚፈናቀሉት ለዐሥርት ዓመታት አብረዋቸው ሲኖሩ የነበሩ ጎረቤቶቻቸውን ‘ውጡልን’ በማለታቸው ነው። በወሬ እና አሉባልታ ላይ ብቻ ተመሥርቶ በየከተማው እና መንደሩ የዜጎች ሕይወት ይጠፋል፣ ንብረት ይወድማል። ዜናው በየዕለቱ ሊባል በሚችል ደረጃ ከመደመጡ የተነሳ እንደ መደበኛ የሕይወት ገጠመኝ የሚቆጠርበት ደረጃ ላይ ነን ማለት ማጋነን አይሆንም።
ይህንን መሰሉ ገጠመኝ በዋና ከተማዋ አጠገብ ቡራዩ፣ በሻሸመኔ፣ በበለሳ፣ በአሶሳ፣ በሐዋሳ፣ በጂግጂጋ ወዘተ. ታይቷል። ነዋሪዎች ጎረቤቶቻቸውን አጥቅተዋል፣ አፈናቅለዋል፤ አረጋውያን በወጣቶች ተረግጠዋል። አሁንም ተመሳሳይ ድርጊቶች በየቦታው እየተፈፀሙ ነው። ይባስ ብሎ የፖለቲካ ተዋስዖውም ይህንኑ ያበረታታል። ‘እነ እከሌ ይውጡልን፣ እነ እከሌን ማየት አንፈልግም’ የፖለቲካ «አዋቂነት» መለኪያ ተደርጎ ተወስዷል። ‘ኧረ ይሄ አካሔድ አግባብ አይደለም’ ብሎ ማለት ሞኝነት ይመስላል።
የአፈና ፖለቲካ ጦስ
 
‘ይሄ ሁሉ ማኅበራዊ ገመና እንዴት ባንዴ ፈነዳ? እስከዛሬስ የት ተደብቆ ነበር?’ ሊባል ይችላል። ላለፉት ዓመታት መንግሥት የሕዝብን አመኔታ አጥቶ፣ ሕዝብም የመንግሥት አመኔታ አጥቶ – ሁለቱም በዓይነ ቁራኛ ሲተያዩ ነበር። በተለይ መንግሥት የማያምነውን ሕዝብ ለመቆጣጠር የተከተለው የአፈና ስርዓት ዜጎች የሚወያዩበትን መገናኛ ዘዴዎችን፣ የሲቪል ማኅበራትን እና ቤተ እምነቶችን ሳይቀር በመቆጣጠር ወይም በመዝጋት ዜጎች ችግሮቻቸውን በነጻ ውይይት ለመረዳትም፣ ለመፍታትም እንዳይችሉ በመደረጉ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ቂም እና በቀል እንዲቋጥሩ አድርጓል። በመንግሥት ሥም ጥቃት የሚያደርሰው ያለወቃሽ፣ የሚዘርፈውም ያለተቋዳሽ ሲያጠቁ እና ሲዘርፉ፥ ቀሪው ኗሪ ደግሞ ቂም እየቋጠረ ኖሮ ትንሽ ነጻነት ሲያገኝ ብሶቱ ፈንድቶ ይኸው አሁን መቆጣጠር የማይቻል መስሏል።
በቅርቡ በቴሌቪዥን ያየናቸው ግዙፍ የአገር ሀብት ዝርፊያ እና የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች፣ ታሪኮች ተሰውረው የከረሙት ከመንግሥት ብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች እንጂ ከብዙኃን ዜጎች አይደለም። በነዚህ ችግሮች ላይ መወያየት ሳይቻል፣ የሞራል እና ሥነ ምግባር ትምህርት ቤቶች የሚባሉት ቤተ እምነቶች እንኳን እያወቁ ነገር ግን « ስህተት ነው’ ብለው ለማውገዝ ሳይደፍሩ ይልቁንም የመንግሥትን የልማት ዕቅድ እና ስኬት ሲያስተጋቡ በኖሩበት እና የዝርፊያው ተቋዳሽ ለመሆን በተሻሙበት አገር የሞራል ውድቀት የሚጠበቅ ነው።
በጦርነት እና ግጭት እንዲሁም በአምባገነንነት ውስጥ የኖሩ አገራት ወደ ነጻ ስርዓት ከመሸጋገራቸው በፊት በግጭት ወቅት የፈረሰውን ሞራል መልሶ መገንባት ፈተናቸው ነው። ኢትዮጵያ፣ በ1983 የደርግ ስርዓት ወድቆ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲቆጣጠር፥ በየመንደሩ ይታይ የነበረው ዓይን ያወጣ ዝርፊያና ቅሚያ ገመና ገላጭ ነበር። አሁንም ያንኑ ታሪካችንን በሌላ ገጽ እየደገምነው እና እያስቀጠልነው እስከሚመስል ድረስ በተለይ በማኅበራዊ ግጭት እና ፍርደ ገምድልነት ተቻችሎ እና ተከባብሮ መኖር የከበደበት፣ ዝርፊያና ስርቆት የማይታፈርበት ፈታኝ የታሪክ ጫፍ ላይ ደርሰናል።
የፖለቲካ ስርዓት ሽግግሩ ማኅበራዊ የሞራል እና ሥነ ምግባር ውሉን እንዳይስት ወይም ከሳተበት እንዲመለስ ማድረግ ራሱን የቻለ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ የቤት ሥራ ነው።
Filed in: Amharic