>

ገላሳ ዲልቦ፡ ከልጅ ሚካኤል እምሩ ዘመነ መንግሥት  እስከ ዐብይ አሕመድ አገዛዝ ድረስ!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ገላሳ ዲልቦ፡ ከልጅ ሚካኤል እምሩ ዘመነ መንግሥት  እስከ ዐብይ አሕመድ አገዛዝ ድረስ! 
አቻምየለህ ታምሩ
ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ የገባው የኦነግ መሪ ገላሳ ዲልቦ ማተቡን ከመበጠሱ በፊት ወላጆቹ ያወጡለት ስም ዮሐንስ በንቲ  ይባል ነበር።
ዮሐንስ በንቲ በዘመነ ደርግ የልጅ ሚካኤል ካቢኔ ሳይፈርስ  ደርግና በዙሪያው የተጠመጠሙ የግራ ድርጅቶች  ያቋቋሙት ኅብረት  የሆነው  የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ፍሕፈት ቤት  ባለሥልጣን  የነበረ ሲሆን  ለሁለት አመት ተኩል  ያህል  አለቃው  የነበሩት አሰፋ ጫቦ ናቸው። አሰፋ ጫቦ በደርግ አስር አመታት ያህል  የመታሰራቸው ምክንያት ሲገልጹ ገላሳ ዲልቦና  ሌሎች አስር ጓደኞቹ ኦነግ ሆነው ሳለ  ሽፋን ሰጥተሀል ተብለው መሆኑን ነግረውናል።
ገላሳ በደርግ ውስጥ  ለሁለት አመት ተኩል  እንዳገለገለ ቀይ ሽብር ካበቃ በኋላ ጫካ በመውረድ ኦነግን ተቀላቀለ። ከተወሰነ ጊዜ የኦነግ ቆይታው  በኋላ ኦነጋውያን በደም ጥራትና በመንደር ልጅነት  ሲሻኮቱ ኦነግን በመለየት በደበላ ዲንሳ አማላጅነት ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም  ጋር ታርቆ ወደ ደርግ  እንደገና ገባ። ደርግን ለተወሰነ ጊዜ ካገለገለ በኋላ  ለመስክ ስራ ተልኮ በዋለበት ሳይመለስ ቀረ።
የውሀ ሽታ ሆኖ ከቆየ  በኋላ  ጫካ ወርዶ ጸጉሩን አንጨፍሮ፣ ጺሙን አሳድጎ የሚሳይ የገላሳ ፎቶ  ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ሰላዮች እጅ በመግባቱ  ገላሳ  ዲልቦ ወደ ትፋቱ  ወደ ኦነግ  መመለሱ  ታወቀ። ከተወሰኑ የጫካ  አመታት ቆይታ በኋላ ያገለግለው የነበረው የደርግ አገዛዝ  ተወግዶ ወያኔ ሻእብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ሲገባ  ገላሳም  የኦነግ መሪ ሆኖ ወያኔን ተከትሎ አዲስ አበባ ገባ። ገላሳና ድርጁቱ የወያኔ ቀኝ እጅ ሆነው ካገለገሉ በኋላ የሆነውን ሁሉ ብዙ ሰው ስለሚያውቀው ነጋሪ አያሻም።  እነ ገላሳ ወያኔ ከአገር ካባረራቸው በኋላ በውጭ አገር ሆነው ላለፉት 27 ዓመታት ሲታገሉ የኖሩት ከአገር ያባረራቸውን ወያኔን  ሳይሆን  በፈጠሩት ትርክት የሚጠሏቸውን ዳግማዊ ዐፄ  ምኒልክን ነበር።
ገላሳ ዲልቦ ዛሬ ሶስተኛ መንግሥቱ የሆነውን የዐቢይ አሕመድን ኢትዮጵያ ሲረግጥ ወያኔ ከአገር ሲያባርራቸው በወጣበት  ቦሌ ሲደርስ  ለጋዜጠኞች በሰጠው  መግለጫ «ይሄ ትልቅ መስዋትነት ተከፍሎ የተገኘውን ድል እና ኦሮሞን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ብሔሮች ያኮራ ለውጥ ወደኋላ እንዲመለስ አንፈልግም» ሲል  በአማርኛ ተናገሯል።  ይህ እንግዲህ ሌላ ማተብ ፍለጋ መሆኑ ነው። ገላሳ በሽግግሩ መንግሥት ተብዮው ጉባኤ  በአዳራሹ ውስጥ ለነበሩት ለነመለስ ዜናዊና ኢሳያስ አፈወርቂ ይናገር የነበረው በኦሮምኛ ሲሆን ንግግሩን  ወደ እንግሊዝኛ  ያስተረጉምና ለጉባኤው ያሰማ የነበረው ሌንጮ ለታ ነበር። ዛሬ  ግን  ግለሳ ያኔ እንግሊዝኛ ያስተረጉምለት የነበረው ሌንጮ ለታ አጠገቡ ስለሌለና  እሱም እንግሊዝኛውን ትቶ  በአገርኛው አማርኛ መናገር  በመጀመሩ እሱም  ያለአስተርጓሚ  ያውም ልቅም  ባለ አማርኛ ቅኔ አዘል መልዕክቱን ለታዳሚ ጋዜጠኞች አስተላልፏል። ለሰላሳ በላይ  አመታት  ያህል አማርኛ ሳይናገሮ ኖር  ሳይጠፋበት  መቅረቱ  ባስተርጓሚ ይነገር በነበረበት በዚያ በሽግግር ተብዮ ዘመን ሳይቀር  አማርኛ ክህሎቱ ምን ያህል የላቀ እንደነበር የሚያሳይ ነው 🙂
ገላሳ ዲልቦ  በየዘመኑ ወደ ሥልጣን በሚመጡ አገዛዞች ዙሪያ እየተጠመጠሙ ጠባብ ፍላጎታቸውን ከኢትዮጵያ ሕዝብ አንጻር የማስፈጽም የረጅም ጊዜ ልምድ ካላቸው ኦነጋውያን መካከል ቀዳሚው ነው። ወያኔና ደርግን ተጠምጥሞ አጋጣሚውን ሁሉ በመጠቀም  ጠባብ ፍላጎቱን  በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ አስፈጽሟል። አሁን ግን በፊት  አጋጣሚ የነበረው  ሰፊ በር ሆኖለታል! እንግዲህ  የሚሆነውን ወደፊት አብረን  እናያለን!
Filed in: Amharic