>

ለተከበሩ አቶ ኢሣይያሥ አፈወርቂና ለዶክተር አቢይ አህመድ!!! (ከሻለቃ ላቀው መንግስቴ)

ለተከበሩ አቶ ኢሣይያሥ አፈወርቂና ለዶክተር አቢይ አህመድ!!!
ከሻለቃ ላቀው መንግስቴ
የአለምን ሕዝብ እጅግ ባሥደነቀ መልኩ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ከሁለት አሥርተ አመታት በላይ እንዲለያዩ የተደረጉ ወንድማማች ሕዝቦችን መልሠው እንዲገናኙ በታሪክ ትልቁን ድርሻ ተወጥታችሁዋል፡፡ያኔ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ሢደረግ ኮሪያ አብረው የዘመቱ አባቴና ጓደኞቹ ሢለያዩ አንገት ላንገት ተቃቅፈው የመጨረሻ ሥንብታቸውን በእንባ ምን ያህል እንደተራጩ ምንጊዜም አልረሣውም፡፡ዛሬ ኣባቴም ወደ ኤርትራም ያቀኑት አባቶቻችን እንደ እድል ሆኖ በህይወት አልተገናኙም፡፡
የኢትዮጵያ ሠራዊት አዘማመቱ በጊዜው ትክክልም ይሁን አይሁን ወደ ኤርትራ በመንግሥቱ ኃ/ማ ጊዜ የዘመተው ሁለቱ ሐገሮች ሣይነጣጠሉ በጋራ እንዲኖሩ ፡ሁለት ሐገሮች መሆናቸው ጉዳት እንጂ ጥቅም እንደሌለው በመታወቁ ብቻ ሣይሆን የደም ቁርኝታችንና ዝምድናችን ተለያይቶ ለመኖር ተፈጥሮአችንም ሥላልነበረ ነው፡፡ውድ መሪዎቻችን በተለይ ፕሬዝደንት ኢሣይያሥ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ሚሊኒየም አዳራሽ እርሦን ለመቀበል ያሣዮትን ፍቅር አይተው ሁለት እጅዎትን ደረትዎ ላይ አጣምረው በእምባ ቀረሽ ፀፀት ቅን በሆነ አባታዊ ፀፀት ምን ያህል እንደተረበሹ በአይናችን ያየንው የቅርብ ጊዜ እውነት ነው፡፡ኢትዮጵያውያን ወደ ኤርትራ ኤርትራውያን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በጀመሩ ጊዜ የነበረው አንገት ላንገት መተቃቀፍና መላቀሥ የአለምን ሕዝብ ሁሉ በእነኝህ ሁለት እህትማማችና ወንድማማች ሕዝቦች ላይ ምን ያህል በደል እንደተፈፀመ በአግራሞትና በሐዘን የተከታተለው ጉዳይ ነው፡፡
ኤርትራ ነፃ ልትወጣ በተቃረበችበት የመጨረሻ የውጊያ ቀናቶች ውሥጥ የኢትዮጵያ ሠራዊት አዛዦችም ሆኑ ተርታ ተዋጊው ሀይል የአሥመራ ከተማና በዙሪያ ያሉ ከተሞችና ሕዝቡ በምንም አይነት እንዳይጎዱ ከባድ መሣሪያም ከተማዋ ውሥጥ ጉዳት እንዳያደርሥ ቃል ተግባብቶ በነፍሥ ወከፍ መሣሪያ ብቻ ራሡን እየተከላከለ እድል የቀናው ወጥቶአል፡፡መሥዋእትነት የከፈሉትም አልፈዋል፡፡ውጊያው በተጠናቀቀም ጊዜ የተማረኩም በርካታ ናቸው፡፡በወጣትነታቸው ወደ ኤርትራ ዘምተው የነበሩ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወታደሮች እህል ውሀቸው ሆኖ ተጋብተው ልጆችን አፍርተው የደም ቁርኝቱን አጥብቀው የተፈጠረውን የመፈናቀል አደጋ እንደ ወታደር ከደረሠባቸው ጉዳት ሌላ ትዳራቸውን ልጆቻቸውን ጭምር አጥተው በናፍቆትና በሠቀቀን እምባቸውን ሢያፈሡ ኖረው የታደሉት ተገናኝተዋል፡፡ገና እየተፈላለጉም ያሉ ዜጎች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ዋናው የሀላችንንም ህሊና እረፍት እየነሣ ያለው ዋናው ጥያቄ የተከበሩ ፕሬዘደንት ኢሣይያሥ ኤርትራ ውሥጥ ታሥረው የሚገኙ የጦር እሥረኞች ጉዳይ መዘንጋታቸው አሣሣቢ መሆኑ ነው፡፡ዛሬ ማንኛውም የጦር እሥረኛ ቤተሠብ ከነገ ዛሬ ተፈተው ይመጣሉ በሚል አይኖች እየቃበዙ ነው፡፡እናቶች አባቶች፡የትዳር አጋሮች ልጆች ጭምር በናፍቆት በሚፈሡ እንባዎች ፊታቸው ላይ ማዲያት እየሠራ ውሉ ባልታወቀ ሁኔታ በር በረ እያዩ እሥር ላይ ያሉ የሠራዊት አባላት በአሣዛኝ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ወይ ሞታቸውን አለዛም አካላቸው ምንም ይሁን ምን ህይወታቸውን የሚሹ ሥጋዎቻቸው ብዙ ናቸው፡፡የታሠረ የጦር ሠው በምቾት ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡አይኖች በእንባ የማየታቸው ሀይል ድንግዝግዝ እየሆነ ነውና የሁለቱም ሐገር መሪዎቻችን እሥረኞች ወደ ሐገር ይገቡ ዘንድ አይኖች ከመታወራቸው በፊት ሠዎች በናፍቆት ወደ መቃብር ከመውረዳቸው በፊት ዶክተር አቢይም ፕሬዝደንት ኢሣይያሥም የሁለቱን ሐገር ሕዝቦች ደሥታ ሙሉ ያድርጉልን፡፡በእግዚአብሔር ሥም ይቅርታችሁ እንከን አይኑረው፡፡ፈጣሪ ጉዟችሁን የሠመረ ያድርገው፡፡አሜን፡፡፡፡፡
Filed in: Amharic