>
5:13 pm - Sunday April 18, 5143

ኦነግ ከሚባል የህውሓት የባህሪ ወንድም ጋር ሽምግልናም ሆነ ድርድር ፋይዳ የለውም!!! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

ኦነግ ከሚባል የህውሓት የባህሪ ወንድም ጋር ሽምግልናም ሆነ ድርድር ፋይዳ የለውም!!!
ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ
Sometimes in April የሚለውን ፊልም ከደርዘን በላይ አይቼዋለሁ። ከዚህ ቀደም ፊልሙን መሰረት አድርጌ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስን ያሳተፈ ” መታወቂያ” በሚል ርዕስ ዘጋቢ ፊልም ሰርቼበታለሁ። እንደማስታውሰው ሻለቃ ዳዊት የዘር ፓለቲካን፣ የሩዋንዳን የዘር ፍጅት መንስኤ እና ውጤት ሲተነትኑት ከፊልሙ ባልተናነሰ ነበር።  እንዳየሁት ከሆነ በማንኛውም መልኩ የሚራመድ የዘር ፓለቲካ የሚያስከትለው መዘዝ ለመረዳት እንደ ሻለቃው የተግባር ምሳሌ የሚሆኑ ጥቂቶች ናቸው።
ዛሬም ሳይቸግረኝ በእኩለ ለሊት Sometimes in April እየተመለከትኩ ነው። ውስጤ ግን መረጋጋት አልቻለም። ኦነግ የሚባል የህውሓት የባህሪ ወንድም እያደረገ ያለውን የአስተዳደር ማፍረስ፣ የጅምላ ማፈናቀል እና ግድያ፣ የሚሊሺያና ሰራዊት ምልመላ፣ ስልጠና፣ የግዛት ማስፋፋት ፣… ወዘተ በአጭሩ መቅጨት ካልተቻለ በአገሬ ኢትዮጵያ ምድርም ” Sometimes in April” ሚያዝያ ሳያልቅ ሊከሰት ይችላል።
በፌዴራል መንግስት ያለው የለውጥ ሃይል ሽማግሌ፣ የሀይማኖት አባት ፣ አባገዳ በማሰማራት ኦነግን መለማመጥ ትቶ የማያዳግም እርምጃውን ዛሬ መውሰድ መጀመር አለበት። ነገ ሳይሆን ዛሬ። አለበለዚያ እስከ ሚያዝያ መጀመሪያ የኦነግ ታጣቂ ሰራዊት 100ሺህ ይደርሳል። የግዛት ማስፋፋቱም በእጥፍ ይጨምራል። ማፈናቀሉን እና በዘር እየለዩ (ለዘብተኛ ኦሮሞዎችን ጨምሮ) መጨፍጨፉን አጠናክሮ ይቀጥላል።
በመሆኑም ለለውጥ ሀይሉ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” እንዳይሆንበት ወገቡን ጠበቅ አድርጐ እርምጃ መውሰድ ይጀምር። በምንም መልኩ ቢሆን ከኦነግ ጋር የሚደረግ ሽምግልናም ሆነ ድርድር የኦነግን ሀይል ለማስፋት ጊዜ ከመግዛት ውጪ የሚፈይደው አንዳችም ነገር የለም።
ማሳሰቢያ ይህ ከላይ የተገለፀው አቋም የእኔ የኤርሚያስ ለገሰ እንጂ ከምሰራበት ተቋምም ሆነ ሌላ ድርጅት ጋር የተያያዘ አይደለም።
Filed in: Amharic