>
6:48 am - Wednesday December 7, 2022

ጀግንነት መግደል ማለት ብቻ አይደለም!  ስለ ወገን  መሞትም ጭምር ነው!!! (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

ጀግንነት መግደል ማለት ብቻ አይደለም!
 ስለ ወገን  መሞትም ጭምር ነው!!!
ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን
* Dhiisa anatu demma
ዳሂሳ አነቱ ዴማ – 
፩ –
ቅልጥ ያለ ጦርነት እየተካሄደ ነው፡፡ የሞት ሽረት ፍልሚያ፡፡ ከፊት ለፊት ሰማይ ጠቀስ ተራዎዎች የጥይት እሳት ይንተከተክባቸዋል፡፡ ቦንብ ይነድባቸዋል፡፡ መድፍና ታንክ እንደ መብረቅ ያጓራባቸዋል፡፡ ከወዲያም ከወዲህም የጥይት እሳት ይወረወራል፡፡ ተራራዎቹን ለማስለቀቅ ነው መራር ፍልሚያው፡፡ ከዚያም ከዚህም በፅናት መተጋተጉ ቀጥሏል፡፡ ከሰዓታት በኋላ ለአንዱ ጓድ መሪ ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጠው፡፡
፪ –
ወለም ዘለም የለም፡፡ ወታደር ነህ፡፡ ሙት ከተባልክ ትሞታለህ፡፡ አልሞትም ብሎ ነገር የለም፡፡ አድርግ ማለት አድርግ ነው፡፡ ጓድ መሪውም የደረሰውን ትዕዛዝ መፈፀም አለበት፡፡ “ጓድ” ማለት ዘጠኝ ወታደሮችን ይይዛል፡፡ በስሩ ያሉትን ስምንቱን ወታደሮች ያስተባብራል፤ ይመራል፤ ያዛል፡፡ ለጓድ መሪው የተሰጠው ትዕዛዝ (ግዳጅ) እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ በሰማይ ጠቀሶቹ ተራሮች መሀል አንድ ቀጭን ሸጥ አለች፡፡ ያቺ ሸጥ በፈንጂ ታጥራለች፡፡ “በፈንጂው ላይ ተራምደህ እለፍ” የሚል ትዕዛዝ ነው የደረሰው፡፡ ይህ ትዕዛዝ መፈፀም አለበት፡፡ ግድ ነው፡፡
፫ –
ጓዶቹን አያቸው፡፡ እንደ እናት ልጅ የሚተያዩ ናቸው፤ ብዙ ችግር አብረው ያሳለፉ ናቸው፡፡ ከሰዓታት በፊት አብረው ተመግበው ነበር፡፡ አንሶላ ቢጤ ትከሻቸው ላይ ጣል አድርገው ጎን ለጎን ጋደም ብለው ነው አውግተው ነበር፡፡ ከሰዓታት በፊት የአንድ ኮዳ ውሃ አብረው ጠጥተው ነበር፡፡ አሁን ግን … ከእነዚህ እንደወንድም ከሚያያቸው ስምንት ጓዶቹ መሃል አንዱን መርጦ ወደ መስዋዕትነት የመላክ ግዴታ ወደቀበት፡፡ በእርግጥ አለቃቸው ነው፡፡ አንዱን “ሂድ በፈንጂው ላይ ተራመድ” ማለት ይችላል፡፡ ግን ማንን ሂድ ይበል? ጨነቀው፡፡ የበላይ ትዕዛዝ ደግሞ መፈፀም አለበት፡፡ ለደቂቃዎች ያህል አሰበ፡፡ አሰበና ……እንዲህ አለ፡-
Dhiisa anatu demma
(Dhiiሳ አነቱ ዴማ)
፬ –
“ተውት እኔ እሄዳለሁ” ማለት ነው ትርጉሙ፡፡ እናም ሄደ፡፡ ፈንጂው ላይ ተንከባለለ፡፡ ተሰዋ፡፡ እሱ በጠረገው መንገድ ላይ ጓዶቹ ሾልከው ወደ ጠላት ወረዳ ገቡ፡፡ ተራራውን አልፈው ከጀርባ ተኩስ ከፈቱ፡፡ ጠላት (ሻዕቢያ) ተፍረከረከ፡፡ የሚፈለገው ከፍታ ነጥብ (ተራራ) ተያዘ፡፡ ድል ተገኘ፡፡ ይህ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ (እዚያው ቦታ ባይሆንም በቅርበት የነበርኩበትና በሁ.አ.ሠ ሬዲዮ በተደጋጋሚ የተወሳ ታሪክ ነው፡፡) ዛሬ፣ ለጓዶቹ በህይወት መኖር ሲል ቤዛ የሆነውን፣ “Dhiiሳ አነቱ ዴማ” ብሎ የተሰዋውን፣ ያንን የቁርጥ ቀን ጀግና አስታወስኩት፡- በሰማያዊ ፓርቲ ምክንያት፡፡
፭ –
አዎ፤ ጀግንነት መግደል ማለት ብቻ አይደለም፤ ጀግንነት መሞትም ጭምር ነው፡፡ የሌላው ሕይወት ይቀጥል ዘንድ መስዋዕት መሆን ነው እውነተኛ ጀግንነት፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በሙሉ ይህንን መሰል እውነተኛ ጀግንነት ነው የፈፀሙት፡፡ ለተሻለ ነገር መምጣት ራስን መስዋዕት ማድረግ የጀግንነት ሁሉ ጀግንነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ የሰማያዊ ፓርቲ የመክሰም ውሣኔ ቀላል ውሣኔ አይደለም፡፡ ከባድ ግን ዓይነተኛ ለውጥ የሚያመጣ ውሣኔ ነው፡፡ ሊደነቅ ሊወደስ የሚገባው ውሣኔ ነው፡፡
፮ –
የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለበርካታ ዓመታት “የፈንጂ አጥር” የገደባቸው ይመስሉኝ ነበር፡፡ በዚያ “ፈንጂ ላይ” መራመድ እና የመለያየትን አጥር መስበር አልቻሉም ነበር፡፡ የግል ጥቅማቸውን (ሃሳባቸውን) ብቻ እያሰቡ የብዙሃኑን የወደፊት ሕልውና አዳፍነው ነበር፡፡ እኔ ብቻ ማለትን ወደው፤ እኛ ማለትን ዘንግተው ነበር፡፡ ይህንን ለመስበር ቁርጥ ውሣኔ ማሳለፍ ያስፈልግ ነበር፡፡ በዚህ የለውጥ ቁርጥ ዘመን፣ ሰማያዊ ፓርቲዎች (Dhiiሳ አነቱ ዴማ) ለማለት ወሰኑ፡፡ ታላቅ የጀግንነት ተግባር ፈፀሙ፡፡ ለጋራ ቤታችን የመጀመሪዋን ምሶሶ ተከሉ፤ በመሞት ትንሣኤ እንዳለ አወጁ፡፡ የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ለዚህ ታላቅ መስዋዕትነታቸው ምስጋና ማቅረብ ነው፡፡
እናመሰግናለን!
——- በመጨረሻ ——-
በመጨረሻ “ሕዝብ ማለት” ከተሰኘው መድብሌ “ተጀመረ እንጂ አላለቀም” ከሚለው ግጥሜ ጥቂት ስንኞችን ልቀንጭብና ላሳርግ፡፡
“….. እውነት እውነት እልሃለሁ
የኦሪቱ የሙሴ ሕግ – በአዲስ ኪዳን ተሻሽሏል፣
የሶቅራጥስ ፍልስፍና – በፕሌቶ ተጠናክሯል፤
የኒውተንን ቀመር ሳይንስ – አንስታይን ሰልቆታል፤
የእነ እንትና ቀመር ደግሞ – በእነ እንትና ተመነድጓል
በአንዱ ራስ ላይ አንዱ በቅሏል!
በአንድ ነገር ፍፃሜ ስር – አዲስ ነገር ይወለዳል
ሕይወት እንዲህ ይቀጥላል!
.
ይኸው ነው፡፡ በሰማያዊ ፓርቲ መክሰም ውስጥም መልካም ነገር ይወለዳል፡፡ እናም – ስለ ከፈላችሁት መስዋዕትነት እናመሰግናለን!
Filed in: Amharic