>

ኤርትራዊያን በመቀሌ ---የጋዜጠኛው የጉዞ ማስታወሻ  (ነቢያት አማረ - ኢትዮጲስ ጋዜጣ)

 
ኤርትራዊያን በመቀሌ —የጋዜጠኛው የጉዞ ማስታወሻ
 ነቢያት አማረ
(ከኢትዮጲስ ጋዜጣ)
አዲስ አበባ መስከረም 20 ቀን ምሽት ሁለት ሰአት ላይ ነበር የመቀሌ በረራችን፡፡ እኔና የምሰራበት ቴሌቪዥን ጣቢያ ካሜራ ባለሙያ ከበረራችን አንድ ሰአት አስቀድመን ቦሌ አየር ማረፊያ ደርሰናል፡፡ አውሮፕላኑ ላይም ስንሳፈር ሰአታችንን እንደጠበቅን ነበር፡፡ ነገር ግን፣ አየር ማረፊያው በአየር ትራፊክ በመጨናነቁ የተነሳ፣ ከበረራ መነሻችን ለ 30 ደቂቃዎች ያክል ለመዘግየት ተገደድን፡፡ በመቶ ሺህ ብሮች የሚገመቱ ሁለት ካሜራዎችን ይዘን፣ እኔና ባልደረባዬ በምሽት መቀሌ መብረራችን ትኬቱ ተቆረጠ ከተባለበት ቀን ጀምሮ ሲያሳስበኝ ነበር የቆየው፡፡ የድርጅታችንን የፋይናንስ ክፍል ሀላፊ፣ ካልጠፋ የበረራ ሰአት የምሽት ትኬት በመቁረጡ ለስንተኛ ጊዜ ደግሜ ረገምኩት፡፡
ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቅኩ ወዲህ ላለፉት 10 አመታት መቀሌን ረግጬ አላውቅም፡፡ ከተማዋ በእጅጉ ተቀይራ እንደምትጠብቀኝና ግር እንደሚለኝ ገምቻለሁ፡፡ የበረራችን እለት፣ በሰው አጠያይቄ፣ መቀሌ በምትገኝ አንዲት ሴት  የሆቴል መኝታ እንዲያዝልን ማድረግ ብችልም፣ የበረራው ሰአት መዘግየቱ፣ እንዲሁም የመቀሌ አየር ማረፊያ ከከተማው ያለው ርቀት ትውስ ሲለኝ፣ ውድ ካሜራ ይዞና ሰው አስከትሎ በምሽት ክፍለሀገር መብረሩ አሳስቦኛል፡፡ ይህን መሰል ሀሳብ ሳሰላስል፣ የበረራ መነሻው ሰአት ደርሶ አውሮፕላኑ 2 ሰአት ከ 30 ደቂቃ አካባቢ ሰማዩን መቅዘፍ ጀመረ፡፡
አዲስ አበባን በቀን ከሰማይ ላይ የማየት እድል ደጋግሞ ቢገጥመኝም፣ በምሽት ከአውሮፕላን ላይ ሳያት የመጀመሪያዬ ነበር፡፡ “በመብራት የተንቆጠቆጠች ምድር” ስል ውበቷን አደነቅኩኝ፡፡ አውሮፕላኑ ዞሮ ከፍታውን በደንብ ጨምሮ መስመሩን ይዞ እስኪበር ድረስ፣ ጭለማ ከዋጠው ሰማይ ላይ ቁልቁል በመብራት የፈካ የአዲስ አበባን ገጽታ ሳደንቅ ቆየሁ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የከተማውን ሰማይ ለቀን ወደሰሜን መክነፍ ቀጠልን፡፡ ከዛ በኋላ የነበረው የአንድ ሰአት በረራ፣ አንድ ሁለት ጊዜ አነስተኛ ብርሀን የሚታይባቸውን መሬቶች ከመመልከት በቀር፣ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የተደረገ ጉዞ ነበር፡፡
በአንድ ወቅት ከጠፈር ላይ በምሽት የተነሳ የአለም ሀገራትን ፎቶ የያዘ ዘገባን ማንበቤ ትዝ አለኝ፡፡ የናሳ ምሁራን ያወጡትን ጥናት መሰረት አድርጎ የቀረበው ዘገባው፣ የአለማችን ሀገሮች በምሽት ከሰማይ ላይ ሲታዩ የሚያንጸባርቁት የመብራት መጠን፣ የኢኮኖሚ እድገታቸውን ይገልጻል የሚል መደምደሚያን የሚያቀርብ ነበር፡፡ የሰሜን አሜሪካና አውሮፓ ሀገራት ጥቅጥቅ ባለ ሰፊ የብርሀን ነጸብራቅ ፈክተው ይታያሉ፤ ይህ ደግሞ የኢኮኖሚ ብልጽግናቸውን ይገልጻል ይላል ትንተናው፡፡ እስያ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አውስትራሊያና ራሺያ አካባቢም፣ የተጋነነ ባይሆንም፣ በብርሀን ፈክቶ በፎቶው ላይ ቀርቧል፡፡
ላቲን አሜሪካና አፍሪካ ግን፣ በአመዛኙ በድቅድቅ ጨለማ የተዋጡ ነበሩ፡፡ በተለይ የአፍሪካ ካርታን ለታዘበ፣ መላው አህጉሩ በድቅድቅ ጨለማ ተውጦ፣ ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ጫፉ ብቻ ነበር መጠቆም የሚቻል መብራት የሚታይበት፡፡ ሰሜናዊ ጫፉ አካባቢ በብርሀን ደምቀው ከሚታዩ ሀገራት ደግሞ ግብጽ አንዷ ነበረች፡፡ ከታች በቀጭኑ ጀምሮ ወደላይ እየሰፋ በመሄድ ከሜዲትራኒያን ባህር ጋር እስኪገጥም የሚዘልቀው፣ የግብጽ የመብራት ሸማ በጣም ነበር ያስቀናኝ፡፡ እነሱ ውሀውን ከኛ እየወሰዱ፣ ከጠፈር ላይ የሚታይ በመብራት የተንቆጠቆጠ ከተማ ይሰራሉ፡፡ እኛ ግን፣ ከአዲስ አበባ መቀሌ እስክንደርስ በድቅድቅ ጨለማ የተዋጠ ምድር እያየን፤ በድቅድቅ ሰማይ ላይ ነው የምንበረው በማለት ለውስጤ ነገርኩት፡፡
ያነበብኩትን ዘገባ ሀሳብ ዳግም እያላመጥኩ፣ ወዲህም በድቅድቅ ጨለማ የተዋጠው የሀገሬ ምድር፣ መቼ ይሆን የሚያልፍለትና በመብራት የሚንቆጠቆጠው? እያልኩ በሀሳብ ስናጥ በረራችን እየተገባደደ ሄደ፡፡ ሜቴክ የተባለ ድርጅት ህልማችንን ባያጨነግፈው፣ የህዳሴ ግድባችን ልክ እንደግብጾች ከጠፈር ሲታዩ የሚያስቀኑ በመብራት የፈኩ ከተሞች ይሰራልን ነበር የሚል ሀሳብ ሽው ብሎብኝ ሁሉ ነበር፡፡
እንዲህ የባጥ የቆጡን ሳወጣና ሳወርድ መቀሌ ከተማ ሰማይ ላይ ለማረፍ ስናኮበኩብ ራሴን አገኘሁት፡፡ ከአንድ ሰአት የድቅድቅ ጨለማ በረራ በኋላ፣ በመብራት የተንቆጠቆጠ ሰፋ ያለ ምድር መመልከት ቻልን፡፡ የመቀሌ የምሽት ገጽታ ከአዲስ አበባ ጋር የሚፎካከር ባይሆንም፣ በመብራት የደመቀ ደስ የሚል ውበት ነበረው፡፡
መቀሌ – አሉላ አባነጋ
አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ አርፈን እቃችንን ሸክፈን ታክሲ ስንይዝ፣ ሰአቱ ለአራት ሰአት 20 ደቂቃዎች የቀሩት ይል ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ አንጻር በቅናሽ አገኘን ብለን እንደ እድል በመቁጠር፣ “ከተማ ድረስ 200 ብር ክፈሉ” ባለን ታክሲ ተሳፈርን፡፡ የሚገርመው ግን፣ ባለኮንትራቱ ታክሲ እኛን ብቻ አልነበረም የሚጭነው፡፡ ዴክሷ መኪና፣ ያሳፈረችንን ሰው ብዛት አምስት ስታደርስ ነበር መጓዝ የጀመረችው፡፡ ኮንትራት ታክሲ እንዲህ ነው እንዴ፣ ብለን ብንጠይቅ፣ ተመላሽ ስለሌለ ለእያንዳንዱ ሰው መቶ ብር በማስከፈል፣ ሙሉ ቢያጆ ጭኖ መጓዝ የተለመደ አሰራር መሆኑ ስለተነገረን፣ ተጣበን መጓዝ ነበረብን፡፡ የተያዘልንን ሆቴል ስም ነግረን፣ በተለምዶ ቀበሌ 16 እየተባለ ከሚጠራው የምሽት ክበቦች በደራበት ሰፈር ካለው ማረፊያችን ደረስን፡፡ በማግስቱ የሚጠብቀንን ከባድ ስራ እያሰብን በቀጥታ ወደማረፊያችን አመራን፡፡
ማደሪያችን የሚገኝበት የመቀሌው ቀበሌ 16 አካባቢ በመጠጥ ቤቶች ሁካታ፣ በቡና ቤቶች ዳንኪራ የተሞላና ውክቢያ የበዛበት የንግድ ሰፈር ነው፡፡ ማልደን ተነስተን ቁርስ መብያ ቦታ ስንፈላልግ፣ ዋና ስራችንን የምንጀምርበት  ሰአት እስኪደርስ አካባቢውን ለመቃኘት ምቹ ጊዜ አገኘን፡፡ ስንዘዋወርም የተመለከትነው ነገር አይን የሚስብ ነበር፡፡ የቀበሌ 16 ገጽታ፣ ድሬደዋ ከተማን በደንብ ለሚያቅ፣ ከዝነኛው የከዚራ ሰፈር ጋር ሊመሳሰልበት ይችላል፡፡ ሰፈሩ፣ ደስ የሚል የኮብል ስቶን መንገዶች እና የድንጋይ ቤቶች ያሉበት አካባቢ ነው፡፡
“ምስጣ ጂገን”
ነዋሪዎቹ ሰፈሩን “ምስጣ ጀገን” ወይም “የጀግኖች ድድ ማስጫ” እያሉ እንደሚጠሩት ገልጸውልናል፡፡ በሰፈሩ የሚታየው የቡና ቤት ብዛት ለመቁጠር የሚያዳግት ነው፡፡ በድንጋይ ቤቶቹ ቨረንዳ፣ ወይም በየዛፍ ጥላው ስር ተቀምጦ የጀበና ቡና እና ቢራ የሚጠጣው የሰው ብዛትም ያስገርማል፡፡ ዛፍ ጥላ ስር ተደርድሮ ቡናና ቢራ እየጠጣ ሲያወካ የሚውለው የመቀሌ ወጣት ብዙ ከመሆኑ የተነሳ፣ ወጣቱ ሁሉ ስራ ፈቶ እዚህ ምን ይሰራል? የሚያሰኝ ነው፡፡ ቡና በጀበና የሚያፈሉት፣ ቢራ የሚያሳልፉትና በየንግድ ቤቱ በራፍ የሚታዩት ሴቶች ቁንጅና፣ የመቀሌን ወንድ ከያለበት የሚያጠራራ ነበር፡፡ የምስጣ ጀገን ውበት የሞላበት ትእይንት፣ የከተማውን ወጣት ስራ አስፈትቶ ድዱን እያሰጣ እንዲውል የሚያስገድድ ሀይል እንዳለው የነገሩን ብዙ ናቸው፡፡
የመቀሌው የጀግኖች መሰጫ ቀበሌ 16 ብዙ ትእይንት የሚታይበት ሰፈር ነው፡፡ የሞቀ ሁካታና ግርግር፣ የዛፎቹ ጥላ፣ የአካባቢው ጽዳት፣ የቤቶቹና የመንገዶቹ አገነባብ በሙሉ ማራኪ ብቻ ሳይሆን ለከተማዋም ልዩ ውበት የሚያጎናጽፍ ነበር፡፡ ሆኖም፣ በርካታ ወጣት በየመንገዱ ግራና ቀኝ ተኮልኩሎ ቡና እያንቃረረ ማየቱ ብዙ ጥያቄ በአይምሯችን እንዲመላለስ መጋበዙ አይቀርም፡፡ የምስጣ ጀገን ድባብ ግን፣ በቀን ብቻ ሳይሆን በምሽትም እንዲሁ የደራ ነበር፡፡ በዛ ሰፈር ሲመሽ የጀበና ቡና መሸጫዎች፣ የሸቀጥ ሱቆችና ሌሎች ንግዶች ይዘጉ ይሆናል፡፡ የዳንኪራ ቤቶቹና ግሮሰሪዎቹ ግን፣ 24 ሰአታት ደምቀውና በወጣቶች ተሞልተው ነበር የተመለከትነው፡፡
በመንገዶቹ ግራና ቀኝ ተቀምጦ ያየሁት ሰው ብዛት “ይህ ሁሉ ወጣት ያውም በስራ ሰአት እዚህ ምን ያደርጋል” እንድንል አደረገኝ፡፡ ወጣቱ በዛ ሰፈር ብሩንና ጊዜውን ሲከሰክስ ውሎ የሚያድረው ለምንድን ነው? ብዬም በውስጤ ጠየኩ፡፡ ሆኖም የማየው ትእይንት መቀሌ ከተማ ለወጣቶቿ የሚሆን በቂ የስራ እድል መፍጠር አለመቻሏን በደንብ ይናገር ነበር፡፡ የስራ እድሉ ቢቀር፣ የከተማ አስተዳደሩ፣ ቢያንስ ወጣቱ ከሱስና አልባሌ ነገሮች ርቆ የሚውልባቸው ማእከላትን መገንባት እንዴት ያቅተዋል? ለሚለው ጥያቄ ግን መልስ አጣሁለት፡፡ በየቡና ቤቱ ደጃፍ ተቀምጦ የሚውለው ይህ ወጣት፣ ስራ ወይም የተሻለ የመዋያ ስፍራ ቢያገኝ፣ የምስጣ ጀገን ምርኮኛ እንደማይሆን ለመረዳት ቀላል ነበር፡፡
ጂብሩክ የገቢያ ማዕከል
ረፋድ ላይ፣ መቀሌ የሄድንበትን ስራ ስንከውን አሳለፍን፡፡ አመሻሽ ላይ፣ እንዲሁም መቀሌ ባደርንባቸው ሶስት ተከታታይ ቀናት፣ የከተማውን ገበያ፣ የመኪኖች መናኸሪያና ሌሎች ቦታዎች በደንብ ለመቃኘት ምቹ እድል አገኘን፡፡ ጂብሩክ እየተባለ የሚጠራው የመቀሌ ዋና ገበያ ሁካታና ግርግር የደመቀ ነበር፡፡ በገበያው ስንዘዋወር በርካታ የኤርትራ ታርጋ የለጠፉ መኪኖች እቃ ሲጭኑ አይተናል፡፡ ጠጋ ብለን ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች፣ “እንደውም አሁን ንግዱ ቀዝቅዞ አያችሁት እንጂ፣ ገበያው በቅርብ ወራት የተሟሟቀ ነበር” ሲሉ ነገሩን፡፡
የመቀሌ ነዋሪዎች በተለይ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መከፈቱን ተከትሎ የከተማው ንግድና እንቅስቃሴ መጨመሩን ይመሰክራሉ፡፡ ኤርትራዊያኑ በተለይ ጤፍና ሌሎች እህሎችን፤ እንዲሁም፣ የኮንስትራክሽን እቃዎችን በሰፊው ሲሸምቱ ተመልክተናል፡፡ ኤርትራዊያኑ በራሳቸው መገበያያ ገንዘብ በናቅፋ የሚገበዩ ሲሆን፣ አንድ ናቅፋ 1 ብር ከ 50 ሳንቲም ሲመነዘር ተመልክተናል፡፡ የነዳጅ ምርቶችም ኤርትራዊያኑ በሰፊው ከሚሸምቷቸው ሸቀጦች አንዱ ነበር፡፡
የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መከፈትን ተከትሎ የሁለቱ ሀገር ዜጎች መገበያየት እንደጀመሩ ሰሞን፣ የመቀሌ ገበያ በእጅጉ ደርቶ ነበር፡፡ ኤርታረዊያኑ በገፍ ወደ መቀሌ መግባትና መሸመት ጀመሩ፡፡ የሆቴል አልጋዎችን ማግኘት እስኪያስቸግር ድረስ መቀሌ ብዙ እንግዶችን ተቀበለች፡፡ ኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች ወደ አስመራ ብዙ እቃ ጭነው ይመላለሱ ጀመር፡፡ አስመራ ላይ የኢትዮጵያዊያን ገበያ መመስረቱን ጭምር ሄደው የተመለሱ ሰዎች ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ በአንዴ የተሟሟቀው ይህ የንግድ ልውውጥ ግን፣ በዛው መቀጠል አለመቻሉን አንዳንዶች ይመሰክራሉ፡፡
ተዘዋውረን ያናገርናቸው ነጋዴዎች “ገበያው መልሶ ቀዘቀዘ” ነበር ያሉን፡፡ ወደ ኤርትራ የሚወስደው መንገድ የፈጠረው የትራፊክ መጨናነቅ፤ የኤርትራ መንግስት በዜጎቹ ላይ ድንገት የጣለው የገንዘብ ልውውጥ ገደብና  በሁለቱ ሀገራት መገበያያ ገንዘብ መካከል ያለው የምንዛሬ ልዩነት ተደራርበው ንግዱን እንዳቀዘቀዙት በርካቶች ነግረውናል፡፡ መቀሌ ከተማን ያነቃቃቀው ይህ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች ግብይት፣ ስርአት ባለው መንገድ ቢመራ ከአካባቢው አልፎ ለሀገር ጭምር ጠቃሚ መሆኑን ከሰማነውና ካየነው መታዘብ ችለናል፡፡
አስመራ አስመራ የሞላ!….”
ከገበያው መለስ፣ መቀሌ ከተማ መናኸሪያ ላይ ያየነው “አስመራ፣ አስመራ፣ አስመራ የሞላ፣ አስመራ በሚኒባስ” የሚል የረዳቶች ተሳፋሪ ጥሪ ልዩ ትኩረት የሚስብ ነበር፡፡ ከአስመራ የሚመለሰው፣ እንዲሁም ወደ አስመራ ለመሄድ የሚዘጋጀው ተሸከርካሪ የመቀሌን መናኸሪያ ግርግር ማድመቂያ ነበር፡፡ እቃውና ሰዉ ወደአስመራ ይሳፈራል፡፡ ለ 20 አመታት የዘለቀው የሁለቱ ሀገሮች ግጭት አልፎ፣ መቀሌ ከተማ መናኸሪያ ላይ “አስመራ በሞላ” የሚል የመኪኖች ጥሪን መስማት ብዙ ትርጉም ያለው ነገር ነበር፡፡
ኤርትራዊያን መናኸሪያ ወይ ገበያ ብቻም አይደለም መቀሌ ከተማ በሁሉም ቦታ  አሉ፡፡ እኛ ያረፍንበት ሆቴልን ጨምሮ፣ በሁሉም ስፍራ ኤርትራዊያን ሲንቀሳቀሱ ማየት የመቀሌ ከተማ አንድ ገጽታ ሆኗል፡፡ አንዳንድ የመቀሌ ልጆች፣ “ከእኛ የበለጠ ሰልጥነናል የሚሉት አስመራዎች፣ የኤቲኤም ገንዘብ መክፈያ ማሽንን አይተው የማያውቁ ነበሩ ለካ” የሚል ትረባ ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ሆኖም፣ የመቀሌ ልጆች ኤርትራዊያኑን በወንድምነት ለመቀበል የከበዳቸው አልነበሩም፡፡ በቆይታችን እንደታዘብነው፣ ኤርትራዊያኑ ምንም እንግድነት ሳይሰማቸውና እንደፈለጉ ሲንቀሳቀሱ ተመልክተናል፡፡
ስንብት
በመቀሌ ከማንኛውም ሰው ጋር መወዳጀትና መግባባት ከባድ አይደለም፡፡ ህዝቡ ልክ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፍቅር ሰጥቶ መቀበል የሚችል ጨዋ ህዝብ ነው፡፡ በአጋጣሚ ከተቀራረቡት ሰው ጋር ማንኛውንም አይነት ጉዳይ አንስቶ ለመጨዋወትም አይከብድም፡፡ ይሁን እንጂ፣ ተቀራርበው ካወጉት ሰው ሁሉ  ተመሳሳይ ይዘት ያለው ጥያቄ መወርወሩ የማይቀር ነበር፡፡ “ትግራይን እንዴት አገኘሀት? መቀሌን እንዴት አየሻት? ህዝቡ ጥሩ አይደለም ወይ? ስለዚህ አካባቢ የሰማኸውና ያየኸው አይለያይም ወይ?” የሚሉ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎችን ከብዙ የመቀሌ ልጆች መስማት የተለመደ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜያት ከተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ አንጻር፣ የመቀሌ ልጆች የሚያነሱት ጥያቄ ምክንያቱን ለመረዳት የሚከብድ አልነበረም፡፡ “በትግራይ ላይ ሆን ተብሎ የጥላቻ ዘመቻ እየተደረገ ነው” የሚል የቅሬታ ስሜት ብዙ የመቀሌ ልጆች የሚጋሩት ስሜት ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ትግራይን እንዴት አገኘሀት? ብሎ በጨዋኛ ሀሳብ ለመለዋወጥ የሚጋብዝ እንጂ፣ የሚተናኮል ጠያቂ ፈጽሞ አልነበረም፡፡
በአንድ አጋጣሚ፣ ከአንድ ምግብ ቤት ምሳ እየተመገብን እንጀራ አንሶን ወጥ በዛብን፡፡ ጭማሪ እንጀራ ብለን መጣልንና ተመግበን ከጨረስን በኋላ፣ ሂሳብ እንተሳሰብ አልን፡፡ አስተናጋጁ ካመጣው ሂሳብ ላይ ‘የጭማሪ እንጀራውን ደመርከው ወይ?’ አልነው፡፡ “እዚህ እኮ ለጭማሪ እንጀራ አይከፈልም” ሲል ነበር አስደማሚ መልስ የሰጠን፡፡ ይህ አይነቱ የመቀሌ አቀባበል፣ ምቾት ሰጪ መስተንግዶ ብቻ ሳይሆን፣ ለከተማዋ ብሎም ለነዋሪዎቿ ልዩ ፍቅር የሚያሳድር አጋጣሚ ነበር፡፡
በዚህ መሰሉ ፍቅር ባልጎደለው መስተንግዶ ተቀብላ ያከረመችንን መቀሌን መልቀቂያ ምሽታችን ደረሰ፡፡ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ የደረስነው ግን፣ ከበረራ ቀጠሯችን ዘግይተን ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ አውሮፕላኑ አመለጠን፡፡ ለሊት በሚነሱ አውቶብሶች መንገዳችንን መጀመሩ አስፈላጊ ነበርና፣ ቻው ብለን ወደተሰናበትናት መቀሌ ከተማ መመለስ ተገደድን፡፡ የቆየንበት ሆቴል የመኝታ አስተናጋጅ ጋር ደውለን፣ አውሮፕላን እንዳመለጠን፣ ሆኖም በለሊት በሚነሳ አውቶብስ ልንጓዝ መወሰናችንን ነገርነው፡፡ “ምን ችግር አለ ታዲያ? የናንተን የሆቴል ክፍል አላከራየሁትም፤ የአውቶብሶች መነሻ ሰአት እስኪደርስ መጥታችሁ በነጻ እረፉ” ሲል ገላገለን፡፡ “እንደአቀባበሏ ሁሉ፣ አሸኛኘቷም ያማረ” ስንል መቀሌንና ልጆቿን እያደነቅን መነሻ ሰአታችን እስኪደርስ ጎናችንን አሳረፍን፡፡
Filed in: Amharic