>
6:01 pm - Wednesday November 30, 2022

የቤተ-መንግስቱ የመምህራን ውይይት!!!  (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

የቤተ-መንግስቱ የመምህራን ውይይት!!!
ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅ
 መንደርደሪያ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ከሶስት ሺህ በላይ መምህራን ጋር እንደሚወያዩ እየተነገረ ነው። መረጃው ትክክል ከሆነ በትምህርቱ ዘርፍ ሊደረግ ለታሰበው ለውጥ ከፍተኛ ጉልበት የሚሰጥ ይሆናል። እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ እነዚህ ከመላው ኢትዮጵያ መምህራንን ወክለው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚመካከሩ የትምህርት አመራሮች እና መምህራን ትኩረታቸው ምን ይሁን? በምን ጉዳይ ላይ ምክረ ሃሳብ ይለዋወጡ? የሚለው ነው።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚደረገው ውይይት እንደ ከዚህ ቀደም በተግባር እንዳየናቸው በአጉል አሽኩልሌ፣ ማሽቃበጥ እና ሙገሳ ላይ የሚያተኩር ከሆነ አካሄዱ አደገኛ ይሆናል። እንደዚህ አይነት አካሄድ ቅጥፈት እና የውሸት ድራማ መተወን ለቀድሞ የስርአት ባለቤቶቹም አልጠቀመም። ለመምህራንም አልጠቀመም። ውጤቱም ቢሆን አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ከመሆን አይዘልም። ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ህዝብ ምሁራን በሚያሳዩት አድርባይነት በመመልከት ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል። እናም ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
 ይሄ ማለት ግን የሚደረገው ውይይት አሉታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኩር ማለት አይደለም። እንደውም በእኔ እምነት ከለውጥ ሃይሉ ጋር የሚደረግ ምክክር ሂሳዊ ድጋፍ ( Critical Support) ላይ አጽንኦት ቢሰጥ የተሻለ ይመስለኛል። በቁጥር አነስተኛ የሆነውን የለውጥ አመራር መደገፍ የሚቻለው የተገኙት ድሎች በፀረ ለውጥ ሃይሎች እንዳይነጠቁ፣ የአገራችን ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የሚያደርግ ሲሆን ብቻ ነው። እናም የሚደረገው ውይይት “በህገ መንግስት ይከበር!” ጭንብል የተሸፈነውን ዘረኛ እና አምባገነን ሃይል በሚደግፍ መልኩ መሆን የለበትም።
ለማንም ግልጥ እንደሆነው የተሻለ ስርአት ለማምጣት በሚደረጉ ትግሎች ውስጥ መሪ ሐሳቦችን የማመንጨት ሐላፊነት የምሁራን ነው። ማመንጨት ብቻ ሳይሆን ትግበራውን የሚመሩት እና የሚያስፈፅሙትም ምሁራን ናቸው። መምህራን ደግሞ ከየትኛውም ምሁራን በላይ ትውልድ የመቅረፅ ሀላፊነት የወደቀባቸው በመሆኑ በልዩ ሁኔታ ይታያሉ። እናም መምህራን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚኖራቸው ውይይት መሰረታዊ ጉዳዮችን ያነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። በእኔ እምነት የውይይቱ ማእከልና ማጠንጠኛ አዲስ በተቀረፀው “የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ” ቢሆን ተመራጭ ይሆናል።
       አንድ: – የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ
 
 ይህ በትምህርት ሚኒስቴር የበላይ አስተባባሪነት የተዘጋጀው የትምህርት እና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ላይ በሺዎች የሚጠጉ ሙያተኞች በመምከር ላይ መሆናቸው ይታወቃል።የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ (Road Map) የአገራችንን የመካከለኛ ገቢ ራዕይ ለማሳካት የሚያስፈልገውን ብቁ የሰው ኃይል በብቃትና በብዛት እንዴት በማፍራት የአገራችንን ሁለንተናዊ ልማት እና የዲሞክራሲ ግንባታ ስራዎች መደገፍ እንዲቻል ከአለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር በማስተሳሰር የተዘጋጀ መሆኑን በዶክመንቱ ላይ አመላክቷል።
የጥናቱ አጠቃላይ ሂደት በትምህርት ዘርፍ የተጠኑ ልዩ ልዩ ጥናቶችን፣ ሪፓርቶችን፣ መጠይቆችን፣ ውይይቶችንና ሌሎች የመረጃ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም እንደተከናወነ ዶክመንቱ አመላክቷል። በአጠቃላይም ከ15ሺህ በላይ ለፌዴራል እስከ ወረዳ የተመደቡ ፓለቲከኞች፣ የዩንቨርስቲ አመራሮች፣ የትምህርት አመራሮች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ የንግድ ምክር ቤት አባላትና ሌሎች ያገባኛል ባዬች መረጃ በመስጠት መሳተፋቸው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም የአለም አቀፍ ልምዶችን ለማካተት ለኢትዮጵያ የወደፊት መንገድ ሞዴል ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉትን ቬትናም እና ማሌዢያ የፍኖተ ካርታ ብሉ ፕሪንት ለጥናቱ ግብአት ተወስዷል።
ፍኖተ ካርታው በቀጣይ በሚዘጋጁ ተከታታይ መድረኮች አስተያየት ተሰጥቶበት የመጨረሻውን ቅርፅ እንዲይዝ በማድረግ ለትግበራ ዝግጁ እንደሚሆን ተነግሯል። በተለይም ከያዝነው አዲስ አመት የመጀመሪያ ወር ጀምሮ በጥናቱ ላይ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ወላጆችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሰፋ ያለ ውይይት እንደሚያደርጉና ሰነዱን እንደሚያዳብሩ አልፎ ሄዶም እንደሚያሻሽሉ አዲሱ መንግስት ቃል ገብቷል። በተገባው ቃል መሰረት በየደረጃው ምክክር እየተደረገበት መሆኑን ለማየት ተችሏል።
ይሄ የዶክተር አቢይ የለውጥ መንግስት ውሳኔ ትክክለኛ እና ወቅታዊ ነው።አካሄዱ ከዚህ ቀደም የነበረውን በግድ የመጫን እና የማሰረፅ (ኢንዶክትሪኔሽን) አካሄድ ያስቀረ ነው። እንደ ለውጥ ሃይል መስራት ያለበትን በመስራቱ ምስጋና ሊቀርብለት ይገባል።
 የትምህርት ስርአት የአገሪቷን ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ሁኔታዎች የሚወስን በመሆኑ ቀድሞ እንደነበረው ከላይ ወደ ታች የመጫን ማእከላዊ አሰራር ሊፈፀም አይችልም። የትምህርት ተደራሽነትን፣ ጥራትን፣ ተገቢነትን፣ ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ ካለ ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎና ባለቤትነት የሚሞከር አይደለም። የትምህርት ስርአቱን እንደ ዋና ማስፈፀሚያ ወስዶ አንድ የኢኮኖሚና የፓለቲካ ማህበረሰብ ብሎም ኢትዪጵያን ወደ መካከለኛ ገቢ የመውሰድ ራዕይ ሊሳካ የሚችለው የትምህርት አመራሩን እና አደረጃጀቱን በወሳኝነት በሕዝብ ተሳትፎ የሚመራበት ስርአት መዘርጋት ከተቻለ ብቻ ነው።
በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመምህራን ጋር የሚያደርጉት ምክክር ይህን ፍኖተ ካርታ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። ላለፋት ሩብ ክፍለ -ዘመን በኢትዮጵያ ምድር የተተገበረው የትምህርት ስርአት ችግሮች በፍኖተ ካርታው ላይ በዝርዝር ሰፍረዋል።
ሁለት: – ፓሊሲና ፍኖተ ካርታን ለይቶ መወያየት
በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታውን እና የትምህርት ፓሊሲውን አንድ እና አንድ አድርጐ የማየት ዝንባሌዎች እየታዩ ነው። ለዚህም ይመስላል የጥናት ቡድኑ መሰረታዊ የቃላት ፍቺ በማለት ሁለቱን ፅንሰ ሃሳቦች ወደ መፍታት የሄደው። እርግጥም ፍኖተ ካርታንና ፓሊሲን ተመሳሳይ ትርጉም መስጠት ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ሊወስደን ይችላል።
 ተደጋግሞ እንደተገለፀው ፍኖተ ካርታ (Road Map) ማለት አንድን ግብ ውጤታማ ለማድረግ የምንከተለው አቅጣጫ ወይም መንገድ ነው። ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ይህ አዲስ የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ የኢትዮጵያ መንግስት በራዕይ ደረጃ የቀረፀውን ወደ መካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የሚያስፈልገውን ብቁ የሰው ሃይል እንዴት ማፍራት እንደሚችል የሚጠቁም እና አቅጣጫ የሚያሳይ ነው።
ፓሊሲ ደግሞ መንግስታት በረጅም ጊዜ ሊያሷኳቸው የሚፈልጉትን ራዕይ ፣ አላማዎች፣ ግቦች፣ ስትራቴጂዎችና ማስፈፀሚያ ስልቶች የሚቀርፁት ነው። ለምሳሌ በሰነዱ እንደተቀመጠው “ የትምህርት እና ሥልጠና ፓሊሲ” ማለት ጠቅለል ያለና የትምህርት ፍልስፍና ያለው በረጅም ጊዜ ልናሳካቸው የሚገቡ ግቦችንና አላማዎች እንዲሁም እነዚህን ግቦችና አላማዎች የሚፈፀሙበትን ስልቶች የሚያመላክት የመንግስት ሰነድ ነው። በውስጡም አገሪቱ የምትመራበትን የትምህርት ፍልስፍና፣ የትምህርት መዋቅር፣ የመምህራን ምልመላ፣ ምደባ፣ ዝውውር፣ የትምህርት አመራር… ወዘተ የያዘ ነው።
 በመሆኑም ፍኖተ ካርታ ለፓሊሲ ማሻሻያ ወይም ለውጥ ግብአት ሆኖ የሚያገለግል እንጂ በራሱ ፓሊሲ አይደለም። በሌላ አነጋገር ፍኖተ ካርታ መንገድ ወይም አቅጣጫ የሚጠቁም እንጂ በፓሊሲ ውስጥ የሚካተቱ ዝርዝር ግቦችና አላማዎች እንዲሁም እነዚህን ግቦችና አላማዎች የሚፈፀሙበትን ስልቶች የሚያሳይ እቅድ አይደለም። ስለዚህም መምህራን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚያደርጉት ውይይት በቅድሚያ በፍኖተ ካርታው ላይ ተመርኩዘው ለቀጣይ የትምህርትና ስልጠና ፓሊሲን በሚለውጥ መልኩ መቃኘት ያስፈልጋል።
 
ሶስት: –  የትምህርት እና ስልጠና ችግሮች
አስቀድሜ እንደገለጥኩት ይህ የትምህርት እና ስልጠና ችግሮችን ለመቅረፍ የተዘጋጀ ፍኖተ ካርታ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለመጠቆም የሚያስችሉ ቁምነገሮችን አንስቷል። ከእነዚህም ውስጥ የትምህርት ፍትሐዊነት እና ተደራሽነት፣ የተማሪዎች ንጥር እና ጥቅል ተሳትፎ፣ አገራችን ከአለም አቀፍ እና ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች ጋር የሚታየው ልዩነት በሰፊው ተዘርዝሯል። በመሆኑም መምህራን በሰነዱ የቀረቡ ችግሮችን አንድ በአንድ ነቅሰው በማውጣት ውይይት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ለአብነት ያህል ራሴን እንደ አንድ በውይይቱ የሚሳተፍ መምህር ባስብ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አነሳለው።
#ጥያቄ አንድ: – የቅድመ መደበኛ ትምህርት የነገውን አገር ተረካቢ ዜጋ በአካልና በአእምሮ በማዳበር አጠቃላይ ስብእና የሚቀረፅበት ነው። ነገር ግን የዚህ አፈፃፀም ሲታይ በክልሎች መካከል ያለው ልዩነት እጅግ የከፋና ፍትሐዊነት የማይታይበት ነው። በምሳሌ ለማሳየት ከ2005 -2009 ዓም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ጥቅል ተሳትፎ በአንደኛ ደረጃ ትግራይ (93 በመቶ)፣ ሁለተኛ አዲስ አበባ (92 በመቶ) ሲሆን የመጨረሻ መጀመሪያው ሱማሌ(7 በመቶ) እና አፋር(12 በመቶ) ነው። እናም ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ ልዩነቱ ለምን የሰማይ እና ምድር (በትግራይ 93፣ በሱማሌ 7) ያህል ሆነ? ፍትሐዊ መሆን ለምን አቃተው? የሚለው ይሆናል።
#ጥያቄ ሁለት: – የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በአብዛኞቹ አገሮች የሚሰጠው አራት አመት ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ሁለት አመት ብቻ ሆኗል። የኢትዮጵያ ወጣቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በለጋ እድሜያቸው ማለትም በ16 አመታቸው ስለሚያጠናቅቁ ለስራ ዝግጁ የሚሆኑበት እድሜ አይደለም።ይሄ ወቀሳ ፓሊሲው መተግበር ከጀመረ ቀን አንስቶ በማህበረሰቡ የሚነሳ ነው። ለዚህ ትውልድ የሚገድል ፓሊሲ ተጠያቂው ማነው?
#ጥያቄ ሶስት : – የአገራችን ኢትዮጵያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎ ከአለም አቀፍ እና ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ተሳትፎ ጋር ሲነፃፀር የሚያስደነግጥ ደረጃ ላይ ያለ ነው። በቅርቡ በወጣው GMR ሪፓርት የአገሮች አማካይ የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ንጥር ተሳትፎ 84% ፣ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው 81%፣ ሲሆን ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች የሁለተኛ ደረጃ አማካይ ተሳትፎ 64 በመቶ ደርሷል። ከዚህ አኳያ የአገራችን ኢትዮጵያን ስንመለከተው 24 በመቶ ብቻ ነው። በቁጥርም ብናሰላው ከ5 ሚሊዬን በላይ ወጣቶች የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማግኘት ሲገባቸው ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም። ለምን? ይሄን ሐላፊነት የሚወስደው ማነው? እስከ ዛሬ የአፍሪካ ነብር ሆነናል እየተባለ ለተሰበከው ነጭ ፕሮፐጋንዳ ምን ምላሽ ይሰጣል?
#ጥያቄ አራት -: በአገራችን ኢትዮጵያ ያለው የተማሪዎች የትምህርት ማቋረጥ እጅግ አሳሳቢ መሆኑ መረጃዎቹ ያመለክታሉ። በአንደኛ ደረጃ ለትምህርት ተመዝግቦ የሚጀምረው 4ሚሊዬን አካባቢ ሲሆን 12ኛ ክፍል የሚደርሰው ከ250ሺህ በታች ነው። የ1ኛ ክፍልንና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ስናነጻጽር የ1ኛ ክፍል ተማሪዎችን 32% ብቻ 8ኛ ክፍል እናገኛቸዋለን። እንዲዚህ አይነት የትምህርት ማቋረጥ እንዴት ሊከሰት ቻለ? ተማሪዎች ትምህርታቸውን በማቋረጣቸው ምክንያት የሚከሰተውን የሃብት ብክነት፣ ማህበራዊ ቀውሶች እንዴት ይታያሉ?
#ጥያቄ አምስት -: የትምህርትና ስልጠና ችግሮችን እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የጠቆመው ቡድን አሁን በስራ ላይ ያለውን የትምህርት ስርአት ጥራት እና አግባብነት በተመለከተ “ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ምላሽ የማይሰጥና መስተካከል ያለበት ስርአተ ትምህርት” በማለት ፈርጆታል። ከዚህ በተጨማሪም በስራ ላይ ያለው ስርአተ ትምህርት የአገር ፍቅርን፣ የመቻቻልና አብሮ መኖርን፣ በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ለውጥ ባለማምጣቱ ግለኝነት እያየለ፣ ዘረኝነት እየገነገነ  የትምህርት ስርአት ቁልፍ መሳሪያ የሆነው ሥርአተ ትምህርት በዚህ ደረጃ ከተመደበ የለውጥ ሃይሉ ስርአተ ትምህርቱን ስር ነቀል በሆነ መንገድ ለመቀየር ምን ያህል ቁርጠኝነት አለው?
#ጥያቄ ስድስት -: የትምህርት ተቋማትንና የትምህርት አመራርን ከፓለቲካ ፓርቲ ስራ እና ምደባ የሚከለክል ህግ እንዲወጣ ለምን አይደረግም?ማንኛውም አይነት የፓለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴ በትምህርት ቤቶች እንዳይኖር ጥብቅ ደንብና መመሪያ እንዲወጣ አይደረግም? …ወዘተ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ጐልተው መነሳት ይኖርባቸዋል።
ማጠቃለያ
 የጥናት ቡድኑ እንደገለጠው በትምህርት ስርአቱ ውስጥ ያለው አማራጭ ሁለት ነው። አንደኛው አማራጭ ጥፍሩን በመከርከም ፣ ምንቃሩን በመሳል ኑሮውንና እድሜውን እንደሚያራዝመው ንስር አሞራ በጥገናዊ ለውጥ መቀጠል። ወይም መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት ለአገራችን ኢትዮጵያ የምናልመውን እድገትና ብልፅግና የሚያመጣ አቅጣጫ መከተል። ውሳኔውን በቀጣይ ወራት የምናየው ይሆናል።
Filed in: Amharic