>

ከሶማሌ ክልል አልፎ ኢትዮጵያን ይታደጓታል ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው መሪ!!! (ሞሀመድ ጀማል አህመድ)

ከሶማሌ ክልል አልፎ ኢትዮጵያን ይታደጓታል ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው መሪ!!!
ሞሀመድ ጀማል አህመድ
ህወሃት/ኢህአደግ በትውልድ ላይ ከሰራቸው ወንጀሎች አንዱ ታዳጊ ክልል ብሎ የመደባቸውን ክልሎች መሪ አልባ አድርጎ እንደፈለገ መቦጥቦጡ ነበር። ሱማሊ፣ ቤንሻጉል ጉምዝ፣ አፋርና ጋምቤላ ክልሎች ላለፉት 27 አመታት የፈለጋቸውን የሚሰሩበት የህውሃት የጉልማ መሬት ነበሩ። ህወሃት እነዚህ ክልሎች እንዲያድጉና እንድለሙ ፈጽሞ አይፈልግም ነበር። ህዝቡም ከሙስና ጋር እንድለማመድና ጥገኛ ሁኖ እንድኖር፣ሀገራዊ ፍቅር እንዳይኖረውና ሞጋች ዜጋ እንዳይሆን በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ተሰርቷል። እነዚህ ህዝቦች በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ የሰጧቸውን ብቻ እየተቀበሉ በታዛቢነት እንደቀመጡና የፖለቲካ ልምድ በገዛ ክልላቸው ጭምር እንዳይኖራቸው ተደርጓል፡ በነዚህ በክልሎች ለህዝብ የሚቆረቆር መሪ እንዳይወጣ ተሰርቷል። ለይስሙላ ያክል የተቀመጡት የክልሎቹ አመራሮች ስራቸው ለካድሪዎቹ ታዛዥ መሆንና ጥቅማጥቅሞችን ማመቻቸት እንጅ ስለክላላቸው ጉዳይ መወሰንም ሆነ መናገር አይችሉም ነበር። በተለይ በሶማሊ ክልል ይህ ችግር በጣም የገዘፈና የከፋ ነበር:: የሶማሊ ህዝብ በረሃብና በውሃ ጥም እያለቀ አብዲኢሌ የክልሉን በጀት እህውሃት አመራሮችና ጀኔራሎች ጋር ቢራ ይራጭበት ዘመናዊ መኪና ይቀያይርበት ነበር። እውነቱን ለመናገር በኢህአደግ የተጨቆነውን ያክል የሶማሊ ህዝብ በየትኛውም ስርዓት የተጨቆነ አይመስለኝም። ከዛሬ 6 ወር ገደማ የሶማሊ ክልልን ድባብ ያየ አብዲሌ እንደ ነብይ እንጅ እንደ መሪ የሚያየው ሰው የለም ነበር። ቤቱን ቆልፎ እንኳን አምኖ የአብዴሌን ስም በክፉ ቀርቶ በደግ ለማንሳት የሚደፍር ሰው የለም ነበር። ያው ቀኑ ሲደርስ ከልኩ አያልፍም ቃልቲ ተወረወረ እንጅ።
አብዱሌ በተነሳ ማግስት አያይዞት እሄደው እሳት ውስጥ ነበር እንግድህ ያንን ነዲድ እሳት አጥፋ ተብሎ የተወረወረው ያሁኑ የሶማሊ ክልሉ ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ። ሙስጠፌ ጅግጅጋ ሲገባ ባንድ በኩል አበሻው(ሶማሊ ያልሆነው ለማለት ነው)ና ሱማሌው ተኮራርፎ በጥርጣሬ ይተያይ ነበር። በሌላ በኩል የአብዱሌ ደጋፊና ተቃዋሚ ሶማሌዎች ተፋጠዋል። በዛላይ የሶማሌ የጎሳ ስርዓት በጣም ውስብስብ ነው። ምን አለፋችሁ ጅግጅጋ ሰላም ሁና መልሶ ሰው ተረጋግቶ ይኖርባታል ብሎ ማሰብ ከባድ ነበር፣ ሁሉም ጓዙን ሸክፎ ነበር ለመሰደድ። በመሆኑም ሙስጠፌ ባንድ በኩል ሱማሊና ሱማሌ ያልሆኑት የክልሉ ነዋሪዎች መካከል የተፈጠረውን ክፍተት መፍታት ሲጠበቅበት በሌላ በኩል የአብዱሊን ደጋፊና ተቃዋሚ ሶማሊዎችን ማስማማት ነበረት። በተጨማሪም ከአብዱሌ ጋር ጥቅም ሲጋሩ የነበሩ ከውስጥም ከውጭም ያሉ አካላት የሙስጠፌ ትልቅ ፈተና ነበሩ። አብዱሌ ዘመናዊ መሳሪያ ከናፍንጫው ያስታቀውና የአብዱሌ የግል ወታደር የነበረው የክልሉ ልዩ ፓሊስም ከነሙሉ ትጥቁ በአለቃቸው በአብዱሌ መያዝና በጥቅማቸው መቋረጥ አኩርፈው አቆፍረው የሚሆነውን እየተጠባበቁ ነበር። ሌላም ሌላም 27 አመት በክልሉ ላይ የተሸረቡ ብዙ ሴራዎች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ችግሮች ናቸው እንግድህ ዲያስፎራውን ፕሬዝዳንት አፍጠው የጠበቁት።
ነገር ግን ይህንን ሁሉ ውስብስብ ችግር ለመፍታት ቀናቶች ብቻ ናቸው የፈጁበት። ልክ 8 ቀን ሳይሞላው የክልሉን ሰላም መመለስ ብቻ ሳይሆን በክልሉ አድስ ተስፋ መታየት ጀመረ። እሰቡ ሶማሌ ክልል ማለት እጅግ በጣም ውስብስብ የጎሳ ስርዓት ያለበት፣ ከመንግስት አልባዋ ሶማሊያ ጋር በጣም ረጅም ድንበር የሚጋራ በጣም ሰፊ ክልል ነው። የዚህን ክልል ሰላም ማስጠበቅ በጣም ትልቅ ተራማጅ መሆንን ብቻ ሳይሆን ትግስትንና ልዩ የማስተዳደር ብቃትንም ይጠይቃል። ምናልባት እንደ አብዱሌ የክልሉን ህዝብ እንደፈለጉ እየገደሉ ለክልሉ ልማት ሳይጨነቁ ለመግዛት ከሆነ ክልሉን ለማስተዳደር ደደብ መሆን ብቻ በቂ ነው። እንደ ሙጠፌ ግን የህዝቦችን መብት ጠብቆ፣ ለክልሉ ልማት እየታተሩ ስርዓት አልባ በሆነች ሀገር ውሰጥ መንግስት አልባ የሆነች ሀግር ጎረቢት ሁኖ የተበጠበጠውን ሰላም ባንድ ግዜ መልሶ የሶማሊን ክልል ማስተዳደር ትልቅ የአመራር ጥበብና ተሰጥኦን ይጠይቃል።
ሙስጠፌ ዛሬ ከሶማሌ ክልል አልፎ ኢትዮጵያን ይታደጓታል ተብሎ ተስፋ ከተጣለባቸው መሪዎች አንዱ ነው። ሙስጠፌ በሀገሪቱ ፓለቲካ ከወደ ምስራቅ ሳይታሰብ ድንገት ብቅ ያለ ክስተት ነው!
Filed in: Amharic