ያሬድ መንግስቴ
የዳውድ ኢብሳ ኦነግና የህወሓት የጦርነትና የዘረፋ ትዕይንት ስመለከት ከአራት መቶ ዓመት በፊት የተደረገው የሰላሳ ዓመት ጦርነት ታሪክ ትዝ አለኝ።ምንም እንኳን ዳውድ ኢብሳና ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሚኖሩ ቢሆኑም በውስጣቸው ያለው መንፈስና አስተሳሰብ የዛሬ አራት መቶ ዓመት በፊት አውሮፓዊያንን ያባላ የነበረው መንፈስና አስተሳሰብ በእነሱ ውስጥ ያለ ሆኖ ይታየኛል።በአውሮፓ ሰላሳ ዓመት ያስቆጠር ሲሆን በዳውድ ኢብሳና በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ግን ከሃምሳና ከአርባ ዓመት በላይ ፈጅቷል።ዳውድ ኢብሳ ከሃምሳ ዓመት ውጊያ በኋላ አሁንም ውጊያ ፤ዘረፋ፤ስልጣን እያለን ነው።ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አሁንም ከአርባ ዓመት በኋላ የውጊያው ልምድ አለን፤መሳሪያው አለን መዋጋት አለብን እያለን ነው።ሃያ ሰባት ዓመት ዘረፈ፤ገደለ፤ድንበር አስፋፋ፤ሕዝብን አፈናቀለ ግን አሁንም አልበቃኝምና እገላለሁ፤እዘርፋለሁ እያለን ነው።
ዳውድ ኢብሳና ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከአውሮፓዊያን የሰላሳ ዓመት ጦርነት አልፈው ክብረወሰን አስመዝግበዋል።በሌላ በኩል አሁንም ካልገደልን ፤ካልዘረፍን እያሉ የሚነግሩን በአስተሳሰባቸው ገና የዛሬ አራት መቶ ዓመት ያለው የአውሮፓውያን አስተሳሰብ በእነሱ ላይ የነገሰና ሃምሳ ዓመት ተዋግተውም አሁንም በዚሁ መንገድ እንቀጥላለን ሲሉን አእምሯቸው ምንም ነገር የማይቀበል፤ደንጋይ መሆኑን ነው።የአውሮፓ ስዎች ለሰላሳ ዓመታት ከተዋጉ በኋላ ውጊያ የትም ሊያደርሳቸው እንደማይችል ተገንዝበው የሰላም ድርድር አድርገው ዕረፍታቸውን ለሕዝባቸው አካፈሉ።ዳውድ ኢብሳና ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ግን መግደል ፤መዝረፍ፤በሬሳ መነገድ ብቻ የሚያዋጣ መስሏችው ፤ከዚህ ውጭ የሚታይ ነገር የሌላቸው ስለሆኑ የዛሬ አራት መቶ ዓመት የተፈጸመውን የታሪክ ክስተት በኦሮምያና በትግራይ ክልል ተቀምጠው በገንዘብ በገዟቸው ነፍሰ ገዳዮች እያሳዩን ነው።
የአውሮፓውያን የሰላሳ ዓመት ጦርነት በሃይማኖት፤በዘርና በንግሥና ፈላጎት፤በጥቅም ፍለጋ ነበር።በጊዜው የነበሩት የጦር አዝማቾች ላዘመቷቸው ወታደሮች መክፈል ሲሳናቸው ወታደሮቹ መዝረፍ ፤አስገድዶ መድፈር፤መንደር ማቃጠል ፤ሰዎችን ከቦታቸው ማፈናቀል ቀጠሉበት።ቢሆንም አንድ ቦታ ላይ ሲደርሱ እነሱም የነገሩን ውስብስብነት በመረዳትና ለማንም እንደማይጠቅም በመረዳት ሰላም መፍትሔ ነው ብለው ለሕዝባቸውም ለራሳቸውም ጥቅም መሳሪያቸውን ጥለው ወደ ሰላማዊ ኑሮ ተሰማሩ።
በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሚገኙት የጎበዝ አለቆችና የመግደል አባዜ የተጠናወታቸው ዳውድ ኢብሳና ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ሠራዊታቸውን እንዲገድል እንዲዘርፍ እንዲያፈናቅል አሰማሩት።ዳውድ ኢብሳ በኦሮምያ የሚገኙትን አስራ ሰባት ባንኮች እንዲዘርፉ፤ከሕዝቡ እንዲዘርፉ፤እንዲገድሉ፤እንዲያፈናቅሉ አደረጉ።ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ደግሞ በዘረፉት ገንዘብ፤በአገዛዝ ዘመናቸው ያሰለጠኗቸውን ነፍሰ ገዳይ ውሻዎች፤በልማት ስም ያሰማሯቸውን የራሳቸውን ዘር ግደል፤አፈናቅል ፤ቤቶችን አቃጥል ፤መንገድ ዝጋ፤ገንዘብ ከአገር አስወጣ እያሉ ነው።አውሮፓዊያን በዚያን ጊዜ አሁን በኢትዮጵያ የሚገኙትን የለውጥ ሐዋሪያት የመስሉ፤በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የቴክኖሎጂያ የአመራር ክህለቶች የተካኑ፤ሰው የሆኑ መሪዎች አላገኙም ነበር።በፍቅር ፤በሰላም፤በአንድነት፤በይቅርታ ተመለሱ የሚል መሪ አልነበራቸውም።ታዲያ እኒህ ለጉድ የጎለታቸው ሁለት መሪ ተብየዎች ምን እንሁን ብለው ነው አሁንም አውሬ መሆንን የመረጡት?
ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሃይማኖት አባቶች፤የአገር ሽማግሌዎች የሰላምን መልዕክት ሲያሰሟቸው፤በአንድነት በፍቅር መኖርን ሲነግሩቸው ጀሯቸውን አሳከካቸው።እኛ ምንጊዜውንም ቢሆን የሰላም ሰዎች ነን።ሰላም ወደሌለበት ቦታ ሄዳችሁ ብትናገሩ መልካም ነው።እኛ መስዋዕት ከፍለን ባመጣነው ለውጥ ልንመሰገን ሲገባን በደለኞች ሆነን ተቆጠርን፤እኛ እኮ መሣሪያ ማንሳት እንችላለን፤ልምዱም አለን እያለ ነው።ዶ/ር የሆነበት ምክኒያት፤በምን፤ከየት እንደሆነ ባላውቅም የተማረ የሃያ አንደኛው ዘመን አእምሮ ያለው ሰው ሆኖ አላየውም።የዛሬ አራት መቶ ዓመት በሰላሳ ዓመት ጦርነት የተሳተፉት አውሮፓውያን ዶ/ሮች አልነበሩም፤የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያበረከተውን ስጦታ አላገኙም፤እንዳሁኑ ዓለም አንድ የሆነችበትና በመገናኛ አንድ የሆነችበት ሁኔታ አልነበራቸውም ግን የጦርነት አስከፊነት ከሰላሳ ዓመት በኋላ ተገንዝበው ሰላም አደረጉ።
የሚገርመው ግን የዳውድ ኢብሳና የዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አማካሪዎች፤ግደሉ፤ዝረፉ፤አፈናቅሉ ፤በሬሳ ነግዱ የሚሏቸው አሜሪካና አውሮፓ የተቀመጡ፤አንዳንዶቹ በዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ ናቸው ይባላል።አንዳንዶቹ የታሪክ ተመራማሪዎች ናቸው ይባላሉ።የአውሮፓን የሰላሳ ዓመት የሕዝብ እልቂት ተምረውት እንደሆነ እገነዘባለሁ።የዳውድ ኢብሳንና የዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ድንፋታ ስሰማና ስመለከት የሰላሳ ዓመት የአውሮፓውያን ጦርነት ትርፍ ያስገኛልና ቀጥሉበት የሚሉ ይመስላል።ፕሮፌሶር ሕዝቅኤል ኢቢሳ፤ዶ/ር ጸጋየ አራርሳ ፤ፕሮፌሶር ተኮላ ሀጎስ፤ጆሃር መሀመድ፤አሉላ ስለሞን የዚህ የሰላሳ ዓመት የአውሮፓ ጦርነት ስልት አቀናባሪ ይመስላሉ።የሚገርመው ግን አውሮፓውያን ሰላሳ ላይ አቆሙ።የእኛ ዳውድ ኢብሳና ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ግን አይበቃንም ጊዜ ይሰጠን፤አብዝተን መዝረፍ አለብን፤አብዝተን መግደል አለብን፤ሰላሳ ዓመት ለእኛ ሁኔታ አይመጥንምና አንድ መቶ ዓመት ሙሉ መግደል ይገባናል የሚሉ ይመስላል።ዳውድ ኢብሳና ማህበርተኞቹ ሃምሳን አልፈው በርቀት መቶን እየተመለከቱ ነው።ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልና ዕቁብተኞቹ ከአርባ ቀጥለን ዓለም አቀፍ ክብረ ወሰን ለማግኘት መቶ ዓመት መድረስ አለብን እያሉን ነው።ስሙ ለጉድ የጎለታችሁ ጉደኞች ያረጀ ያፈጀው ቀመር አከተመ።ታሪክ በርካሽነታችሁ መዝግቧችኋል።ከእንግዲህ ከድሪቶ ቀመራችሁ ጋር በውርደት ጉድጓዳችሁ ትገባላችሁ።